“አልጠግብ ባይ. . .”

Wednesday, 19 August 2015 12:49

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!? . . . “ክረምትና ምን ነበር? ከተማ ይወዳሉ” የተባለው?. . . ይህውና አገሪቷ በወሳኝ መስኮቿ ዝናብ አጥሯት፤ ድርቅ ከቧት ሳለ ከተማው ግን በዝናብና በጎርፍ ሲታመስ ማየት ያስገርማል። ለማንኛውም አንድዬ የተሻለውን እርጥብ ቀን ያምጣልን አቦ።

እኔ የምለው ስለአንዳድ ስግብግብና በእጅጉ ራሳቸውን ስለሚወዱ ሰዎች አስባችሁ ታውቃላችሁ?. . . ዛሬ እነርሱን እያስታወስን ትዝብት አዘል ጨዋታችንን እንቀጥላለን። ይህ አሁን ቀጥዬ የምጠርቅላችሁ ታሪክ ከፈረንጆች ተረት የተጨለፈ ነው። ሰውዬው ሲበዛ ራስ ወዳድ ነው። ከስግብግብነቱ ብዛት የራሱን የማይሰጥ፤ የሰውን ግን በግፍ የሚነጥቅ ክፉ ሰው ነው። በሃጢያትም ቢሆን በሀብት ላይ ሀብት ለመጨመር የሚይታክተው፤ ብዙ አሽክሮችና ሰፊ መሬት ያለው ባለፀጋ ነው።

ከዕለታት በአንዱ ቀን ታዲያ እንዲህ ሆነ። በአነስተኛ ቦርሳ የያዘው 100 የወርቅ ሳንቲሞች ስብስብ ድንገት ጠፋ። አገር ይያዝልኝ ለማለት የቃጣው ይህ ስግብግብ ባለፀጋ፤ ሰራተኞቹን ጭምር አሰማርቶ ቀን ከሌት ያላስፈለገበት ቦታ አልነበረም። ያም ሆኖ ግን ጠፋ የተባው 100 የወርቅ ሳንቲሞችን የያዘው ቦርሳ ሊገኝ አልቻለም። በመጨረሻም ጓደኞቹንና ጎረቤቶቹን ሁሉ ሰብስቦ በአነስተኛ ቦርሳ ያጠራቀመው 100 የወርቅ ሳንቲሞች እንደጠፋውና ያገኘ ሰው ቢኖር የእርሱ መሆኑን አውቆ እንዲመልሱለት አጥብቆ አሳሰበ። ይህ በሆነ ከሁለት ቀን በኋላ ግን አንዲት የ10 ዓመት እድሜ ያላት የደሃ ገበሬ ልጅ ጠፋ የተባለውን ቦርሳ ከመንገድ አግኝታ ለአባቷ አስረከበችው። አባትም በቦርሳው ውስጥ ያሉት የወርቅ ሳንቲሞች 100 መሆናቸውን ቆጥሮ ሲያረጋግጥ፤ ባለቤትነቱ በእርሻ መሬቱ በጭሰኝነት የሚያገለግለው ስግብግብ ባለፀጋ እንደሆነ ተረዳ። ምንም እንኳን ይህ ሚስኪን ገበሬ ቤተሰቡ በችግር የሚማቅቁበት ደሃ ቢሆንም፤ ምንም እንኳን ቤተሰቡ በተቸገረበት ጊዜ ባለፀጋው ሰው ቅንጣት ታክል የመርዳት ፍላጎት እንደሌለው ቢያውቅም፤ ምንም እንኳን ድንገት ቤቱ የገባው የወርቅ ሳንቲም የቤተሰቡን ህይወት በእጅጉ እንደሚቀይር ቢያውቅም “ታማኝነት ከድሮም ጀምሮ በድህነት ውስጥ መታወቂያው ነበርና” የእርሱ ያልሆነውን ወርቅ ለጌታው ለመመለስ ተነሳ። በአዳፋ ልብሱ የሸሸገውን በወርቅ የታጨቀ ቦርሳ እንደያዘ በብስጭት ብዛት እንቅልፍና ሰላም ወደአጣው ጌታው እልፍኝ ገባ። የጠፋበትን የወርቅ ሳንቲሞች የያዘውን ቦርሳ የ10 ዓመቷ ልጁ አግኝታ እንዳመጣችለትና በውስጡም ያለው የወርቅ ሳንቲም 100 እንደሆነ ስለማረጋገጡ አስረድቶ ሰጠው።

የጠፋበትን የወርቅ ሳንቲም በማግኘቱ በእጅጉ የተደሰተው ስግብግቡ ባለፀጋ ሳንቲሞቹን አንድ በአንድ መቁጠር ሲጀምር፤ ምስኪኑ ድሃ ገበሬ ቆሞ እየታዘበው ምናልባትም ያስብ የነበረው ስለሚሰጠው የምስጋና ጉርሻ ይሆናል። ዳሩ ግን ያልጠበቀው ነገር ተከሰተ። ባለፀጋው ሰው ጠፋኝ ያለውና አሁን በእጁ ገብቶ የቆጠረው የወርቅ ሳንቲም 100 መሆኑን ቢያረጋግጥም የሰው ሃቅ ይጣፍጠዋልና “የጠፋብኝ 100 የወርቅ ሳንቲም ብቻ ሳይሆን 125 በመሆኑ ቀሪ 25 የወርቅ ሳንቲሞችን አጭብርብረኸኛል በሚል የሀሰት ክስ መሰረተበት። ድሃውን ገበሬ ችሎት አቁሞ ተጨማሪ 25 የወርቅ ሳንቲሞችን ለማግኘት ቋመጠ። በችሎቱ ተሰይመው የሁለቱንም ሰዎች አቤቱታና መልስ በሚገባ ሲሰሙ የቆዩት ዳኛ። ባለፀጋው አስቀድሞ ጠፋኝ ያለውን የወርቅ ሳንቲም መጠን በስውር አስመርምረው ከደረሱበት በኋላ የሚከተለውን ፍርድ ሰጡ፣ “አንተ ባለፀጋው ሰው ጠፋኝ ያልከው 125 የወርቅ ሳንቲሞች ሆኖ ሳለ የዚህ ደሃ ገበሬ ልጅ ያገኘችው 100 የወርቅ ሳንቲሞችን ብቻ ከሆነ ይህ ቦርሳ ያንተ አይደለም ማለት ነው። ስለሆነም በሌላ ጊዜ 125 የወርቅ ሳንቲሞችን አገኘሁ የሚል ሰው ሲመጣ ላንተ እንዲሰጥህ ይሁን። ነገር ግን ይህ 100 የወርቅ ሳንቲም የኔ ነው የሚል በበቂ ማስረጃ እስካልቀረበ ድረስ ሙሉ በሙሉ ለዚህ ደሃ ገበሬና ለልጁ የታማኝነታቸው በረከት እንዲሆን ፍርድ ቤቱ ወስኗል” ሲሉ መዝገቡን ዘጉ። ቂ-ቂ-ቂ ይህቺ  ናት ጨዋታ ማለት ይሄኔም አይደል?

ይህን ታሪክ ሳነብ ከተዘወተረው “አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል፣ የሰው ፈላጊ የራሱን ያጣል” ተረታችን በተጨማሪ አንዲት ልከኛ አስቂኝ ተረትና ምሳሌ ከች አለችልኝ፤ “አልጠግብ ባይ፤ ሲተፋ ያድራል” ደስ አትልም?. . .

ይልቅዬ ይህን ተረት መሰል ታሪክ አፄ ቴዎድሮስ ዘመንም ስለመፈፀሙ ማንበቤ ትዝ ይለኛል። ከዚህም ሌላ በአፄው ዘመን የሆነች ሌላ የስግብግብ ሰው ታሪክ ጳውሎስ ኞኞ እንደሚከተው አስፍሮት እናገኛለን። አንድ ቀን አፄ ቴዎድሮስ በፈረስ ላይ ተቀምጠው በገጠር ውስጥ ሲጓዙ አንድ ሰውዬ አገኛቸውና፣ “ጃንሆይ! ጃንሆይ!” እያለ ጮኸ። እሳቸውም ምን ሆነሃል? ተናገር!” አሉት። ሰውዬውም፣ በመንገድ ላይ ስሄድ 20 ብር ወድቆ አገኘሁ። ብሩ የማን እንደሆነ ስለማላውቅ ወደእርሰዎ አመጣሁት” አላቸው። አፄ ቴዎድሮስም፣ “የዋህ ሰው ነህ። ብር ጠፋብኝ የሚል ሰው እስኪመጣ ድረስ ብሩን አንተ ዘንድ አስቀምጠው። ስለታማኝነትህ ግን እኔ ሌላ ሃያ ብር እሰጥሃለሁ” አሉት። ሰውዬውም በስጦታው ተደስቶ ሄደ።

አንድ ሌላ ሰው ይህንን ወሬ ሰማና የቀበረውን አርባ ብር አውጥቶ አፄ ቴዎድሮስ ፊት አቀረበና “ጃንሆይ! ይህንን አርባ ብር መሬት ላይ ወድቆ አገኘሁት። የማን እንደሆነ ስለማላውቅ ወደ እርስዎ አመጣሁት” አላቸው። አፄ ቴዎድሮስም ሰውዬው አታላይነት ገብቷቸው፣ “ከመሬት አገኘሁት ያልከውን ብር ወስደህ ለእኔ ገንዘብ ያዥ ስጥ” አሉት። ሰውዬውም ገንዘቡን አስረክቦ እያዘነ ወደቤቱ ሄደ። ይሄን አበው፣ “አተርፍ ባይ አጉዳይ” ያሉት ተረት መዥረጥ አድርገው ይለጥፉበት ነበር። ለማንኛውም አንድዬ በየመስኩ ከሚያጋጥሙን “አልጠግብ ባዮች””. . . ይጠብቀን አቦ፤ ቸር እንሰንብት።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1179 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 970 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us