ጋንዲና ፕሮፌሰሩ

Wednesday, 26 August 2015 13:52

እንደምን ሰንብታችኋል ወዳጆቼ!? . . . እነሆ እኛ ሳንለወጥ ዘመኑ ሊለወጥ ተቃረበም አይደል? እኔ የምለው ይኽውና የአለምዜና ሁሉ ስለነውጥ እንጂ ስለለውጥ ማውራት ያቆመ ይመስል ተሸበርን እኮ!. . . ብቻ አንድዬን የሌለንን እንጠይቀዋለን፤ ኑሮ ላናወጠንና አንድ ኪሎ ስጋ መግዛት ላስጨነቀን ለኛ ዕድገት የተባለውን ለውጥ ያሳየን፤ በጦርነት ለእነርሱ ለሚናወጡት ሰላሙን ያምጣላቸው አቦ።

መቼም ሰው የሌለውን ነገር ቢፈልግ ምንም አይደንቅም። የሌለን ነገር ስለመፈለግ ሳሰብ አንዲት ማህተመ ጋንዲ ፈፅሟታል ተብላ በኢንተርኔት የተለጠፈች ፅሁፍ ማንበቤን አስታወሳለሁ። ፅሁፏ ሰው የሌለውን እንጂ ያለውን ነገር በጥብቅ እንደማይፈልግ የምታሳይ ናት (ምናልባትም ሀበሻ “በእጅ ያለ ወርቅ እንደመዳብ ይቆጠራል” የሚለው ፍለጋው ሌላ ነገር ላይ ስለሚያተኮር ይሆናል) ከዚያም አልፎ ክብርና እብሪት የሚፋጠጡት በመሆኗ እነሆ፤

ይህ ታሪክ ተፈፅሟል የሚባለው ወጣቱ መሃተመ ጋንዲ በለንደን ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የህግ ተማሪ በነበረበት ወቅት ነው። ታዲያ የጋንዲ መምህራን ከነበሩት ሰዎች መካከል ፕሮፌሰር ፒተርስ አንዱ ነበሩ። እኚህ ፕሮፌሰር ወጣቱ ጋንዲ እንደሌሎች ተማሪዎቻቸው ስለማያጎበድድላቸውና በክፍል ውስጥም በተለያዩ ጥያቄዎች ስለሚያፋጥጣቸው አጥብቀው ይጠሉት ነበር።

አንድ ቀን እንዲህ ሆነ። በዩኒቨርስቲው ውስጥ ካለ አንድ የጋራ (የተማሪም የመምህራንም መሆኑ ነው) ካፍቴሪያ ፕሮፌሰሩ ምሳቸውን በመመገብ ላይ ሳሉ ወጣቱ ጋንዲ ካልጠፋ ቦታ የምሳ ሰሃኑን ይዞ ፕሮፌሰሩ አጠገብ ተቀመጠ። በዚህ ጊዜ ፕሮፌሰር ፒተርስ በግልምጫ አንስተው ካፈረጡት በኋላ፣ “ስማ ልጅ ጋንዲ አሳማና እርግብ አንድ ላይ መመገብ እንደማይችሉ የገባህ አልመሰለኝም” አሉት በንቀት አነጋገር፤ ይሄን ጊዜ ጋንዲ ምን ቢል ጥሩ ነው? እውነት” ብለዋል ጌታዬ! እርግቧ መብረር ሳያዋጣት አይቀርም” ይህን ተናግሮ ፍጥነት በመነሳት ቦታ ቀይሮ ተቀመጠ።

ፕሮፌሰሩ በንዴት ቢጦፉም በወቅቱ ምንም ማድረግ አልተቻላቸውምና በፈተና እንዴት አድርገው በውጤቱ ላይ ሊበቀሉት እንደሚችሉ ያወጠነጥኑ ነበር። ጋንዲም ነገራቸው ከወዲሁ ገብቶት ኖሮ የፕሮፌሰሩን ፈተና በጥንቃቄ ሰርቶ አስረከበ። በፈተናው መልሶች ላይ ምንም አይነት ክፍተትም ሆነ ስህተት ያላገኙበት ፕሮፌሰር በቀጣዩ ቀን ክፍል እንደገቡ በተማሪዎች ፊት ወጣቱ ጋንዲን ሊያስቁበት በማሰብ፣ “ጋንዲ ለምሳሌ እንበልና በመንገድ ስትሄድ ሁለት ቦርሳዎችን ብታገኝ፤ በአንደኛው ውስጥ ገንዘብ በሌላኛው ውስጥ ደግሞ ጥበብ መኖሩን ብታውቅና መውሰድ የምትችለው አንዱን ቦርሳ ብቻ ቢሆን የቱን ትመርጣህ?” ሲሉ አመክንዮ አዘል መልስ የሚፈልግ ጥያቄያቸውን ሰነዘሩለት። ወጣቱ ጋንዲ ግን ያለምንም ማመንታት ፈጠን ብሎ፣ “እኔ የምመርጠው ቦርሳ ገንዘብ የያዘውን ነው” አለ። ይሄኔ ፕሮፌሰሩ ነገር እንደተሳካለት ሰው ፈገግ ብለው፣ “እኔ ብሆን ግን የምመርጠው በጥበብ የተሞላውን ቦርሳ ነው።” ከማለታቸው ጋንዲ ፈጠን ብሎ፣ “እውነት ነው ፕሮፌሰር! ሁላችንም ቢሆን የሌለንን ነገር መምረጣችንና ለማግኘት መፈለጋችን ሳይታለም የተፈታ ነው” ብሎላችሁ እርፍ። ቂ-ቂ-ቂ ይህች ናት ጨዋታ ማለት ይሄኔ ነው።

በጋንዲ ስምና ወርቅ አዘል ምላሽ የተበሳጨት ፕሮፌሰር በፈተና ወረቀቱ ላይ በደማቁ “ደደብ!” የሚል ቃል ብቻ ጽፈው ወረቀቱን ሰጡት፣ ዳሩ ግን የፈተናውን ውጤት መፃፍ ዘንግተው ኖሮ ጋንዲ ቢሯቸው ድረስ በመሄድ፣ “በእውነቱ ፕሮፌሰር እርስዎ የሚያስቡትን ነገር ፅፈውልኛል። እኔ የምፈልገውን ውጤት ግን አልፃፉልኝምና። እባክዎ ውጤቴን ይፃፉልኝ” አለ ይባላል።

ይህ ወግ ሰው ምን ያህል በራሱ ጎል ላይ እንደሚያስቆጥር ብቻ ሳይሆን፤ “ጥሩ ሰው ሲበላሽ ቅራሪ የለውም” ያሉትን ተረት የሚያስታውስ ነው። እውነቱን ለመናገር በመግቢያችን እንዳልነው ሰው የሌለውን ቢፈልግ ብርቅ አይደለም። አንድዬ ብቻ በራሳችን ጎል ላይ ከማስቆጠር ይሰውረን። “ዶሮ ብታልም ጥሬዋን” እንዲል የአገራችን ሰው፤ የምንቀጣውን ብቻ ስናልም እንዳንቀጣ፣ የምናሳፍረውን ብቻ ስናስብ እንዳናፍር፤ የምናዋርደውን ብቻ ሳናስብ ራሳችን እንዳንዋረድ መጠንቀቁ አይከፋም።

ለዚያም ይመስለኛል ቅዱስ መፅሐፍ “ማንም የቆመ ቢመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” ያለው። ከመሰነባበታችን በፊት ግን በቅርቡ ከታተመው የታምራት መቻል “እንደባቢሎኖች” ከተሰኘች የግጥም ስብስብ መካከል “ጀግንነት ቅሚያ!” የምትለዋን ልጋብዛችሁ፤

ጀግንነት ቅሚያ

ትህትና ገዝቶት፣ ሳይናገር ሰሪ

በመሆኑ ብቻ፤ ሌላው ግን መንዛሪ

እነሆ ይታያል.  . .

ማድነቅ እንኳን ከብዶት፤ እንኳንስ ሊፈጥር

ደርሶ በሰው ፀሐይ፤ ሊፈካበት ሲጥር።

ልቦናው ሲያውቀው፤ የመሆንን እውነት

ይገኛል፤

ካልዋለበት ሜዳ፤ ሲቀማ ጀግንነት።

ቸር እንሰንብት።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
2068 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 907 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us