“ትንሿ ቀዳዳ. . .”

Wednesday, 02 September 2015 12:44

እንደምን ሰንብታችኋል ወዳጆቼ!?. . . እኔ የምለው ምንም አያመጣም፤ ከምንም አንቆጥረውም፤ ምንም አቅም የለውም ያልነው ነገር ሁሉ አናታችን ላይ ወጥቶ እኛኑ “ጉድ” እያደረገን “አቤት” ያስብለን ጀመር አይደል?.. . የምሬን እኮ ነው፤ ንቀነው፣ ቀሰብተነውና ሸፋፍነነው ያለፍነው የአንድ ሰሞን ነገር ኋላ ላይ በሬ ሰርቆ ሲታሰር “ምነው እናቴ በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ” አይነት ያስብለን ጀምሯል።

አንዲት ፈረንጆች የሚጠቅሷት አባባል አለች፤ “ትንሿ ቀዳዳ ትልቁን መርከብ ታሰምጣለች” ይላሉ። እውነት ነው እኛ እንደጉንዳን ያሳነስነው ነገር ድንገት እንደነብር ሲገጥመን ምን ይባላል?. . . እኛ እንደጉድጓድ ያሰብናት ነገር እንደገደል ሆና ከጠበቀችን ምን ዋጋ አለን? ያቀለልነው ነገር ሁሉ ሰፍቶ “አወይ!” ሲያሰኘን “ትንሿ ቀዳዳ ትልቁን መርከብ ታሰምጣለች” ይሏትን ጥቅስ ከመጥቀስ የሚሻል ምን ነገር አለን?

ፈረንጆች ብቻ ሳይሆኑ አበውም የሚተርቷት ወርቅ የሆነች ተረት አለች። “ቁጭ ብለው የሰቀሉት ቆመውም ለሚውረድ ይከብዳል” . . . እውነት ነው፤ እንደነገሩ ወርወር ያደረግነው ነገር ኋላ ላይ ላውርድህ ቢሉት ሊያዋርደን ይችላል።

ለማንኛውም ለዛሬ ትዝብት አዘል ጭውውታችን ማሳመሪያም ሆነ ማስመሪያ ትሆነን ዘንድ ከኦሮሞ ተረት አንዱን እንደሚከተለው እንምዘዝ።

በአንድ መንደሩ ይኖሩ የነበሩ ብልህና የተከበሩ አዛውንት ነበሩ። ታዲያ የእኚህ አዛውንት ጎረቤቶች ንብረት የሆኑ ሁለት ውሾች ሲጣሉ ያዩና፣ “እባካችሁ እነዚህን ሁለት ውሾች ገላግሏቸው፤ ካለበለዚያ ልጆቹም መጣላት ይጀምራሉ” አሉ። በዚህ ጊዜ በአቅራቢያቸው የነበሩ ሰዎች የሰውዬውን ተግሳፅ ሰምተው፤ ስቀው በማለፋቸው ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አንዱ ልጅ ከአንደኛው ቤት ወጥቶ ሁለቱ ውሾች ሲጣሉ በማየቱ የራሱን ውሻ ትቶ የጎረቤቱን ውሻ በዱላ መታው። በዚህ ቅጽበት የተመቺው ውሻ ባለቤት ልጅ ከቤቱ በመውጣት ላይ ስለነበረ ባየው ነገር ተናዶ፣ “ምን ምትደፍረኝ ነው ውሻዬን የምትመታው?” በሚል የፀብ መነሻ ሁለቱ ልጆች መደባደብ ጀመሩ።

ይህን የተመለከቱት ደካማው አዛውንት አሁንም ከተቀመጡበት ሳይነሱ፣ “እባካችሁ እነዚህን ልጆች ገላግሏቸው፤ አለበለዚያ እናቶቻቸው መደባደባቸው አይቀርም” ሲሉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ተናገሩ። ዳሩ ግን በዙሪያቸው የነበሩ ሰዎች ሰምተውና ስቀው ዝም አሉ። በዚህ ጊዜ አንደኛዋ እናት ከቤት ወጥታ ልጇን የሚደበድበውን ልጅ መታችው። ይህ ሲሆን የተመቺውም እናት አይታ ኖሮ “ምን ሲደረግ ነው ልጄን ባልወለድሽው አንጀትሽ የምትመቺው” ስትል ሁለቱ እናቶች እርስ -በእርስ መደባደብ ጀመሩ።

አሁንም ብልሁና አስተዋዩ አዛውንት የሰዎቹን ሁኔታ እየተመለከተ፣ “እባካችሁ እነዚህ ሴቶች ገላግሏቸው፤ አለበለዚያ ባሎቻቸው ይደባደባሉ” አሉ። በዚህ አፍታ ሚስቱ እየተደበደበችበት ያው ባል ከቤቱ ወጥቶ ደብዳቢዋን ሴት ይነርታት ገባ። ይሄኔ ሚስቱ በሌላ ወንድ (በጎረቤቱ) ስትደበደብበት የደረሰው ባል “ምን ብትደፍረኝ ነው ሚስቴን የምትመታት” ሲል ጎረቤቱን በዱላ መከትከት ተጀመረ።

ይህን ያስተዋሉት አዛውንቱ፣ “እባካችሁ እነዚህን ሰዎች አገልግሏቸው፤ አለበለዚያ ጎሳዎቻቸው መጣላታቸው አይቀርም” ከማለታቸው በጎረቤታሞቹ ፀብ ምክንያት ብዙም ሳይቆይ በሁለቱ ጎሳዎች መካከል ግጭት ተቀስቀሰ። በዚህም በግጭቱ ከእያንዳንዱ ጎሳ ስምንት- ስምንት ሰዎች ሞቱ። ከዚያም የአገር ሽማግሌዎች ተጠርተው ግጭቱን በሰላም እንዲቋጩት ተደረገ። በዚህ ጊዜ ታዲያ በሀገሬው ባህል መሰረት ከአንደኛው ጎሳ ለተገደለ አንድ ሰው ከሌላኛው ጎሳ በካሳ መልክ አንድ ሰው መገደል አለበት አልያም 100 ከብት መስጠት ነበረበት።

ይህ በመሆኑ የአገር ሽማግሌዎቹ “ጉማ” በሚባለው ባህላዊ የፍትህ ስርዓት ላይ ተቀምጠው ለእያንዳንዱ ለተገደለው ሰው መቶ ከብቶችን ካሳ መስጠት ካለባቸው፤ ከእያንዳንዱ ወገን (ጎሳ) 800 ከብቶችን ለካሳ በመፈለጋቸው በአጠቃላይ 16ሺህ ከብቶች ይሆናሉ። ይህ ማለት ደግሞ ያሉት ከብቶች በሙሉ በካሳ መልክ ማለቃቸው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በየጎሳዎቹ 8 ሰዎች ከእያንዳንዱ ወገን መገደል ካለባቸው 16 ተጨማሪ ሟቾች ሊኖሩ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ከቀደሙት ጋር በድምሩ 32 ሰዎችን ማጣት ሊሆን ነው ይህ ለሁላችንም ትልቅ ሀዘን የሚፈጥር ስለሆነ፤ ምን ይደረግ? ብለው ሲመካከሩ፤ የቀድሞው ብልህና አስተዋዩ አዛውንት የሚከተለውን የመፍትሄ ሃሳብ ሰጠ። “መፍትሄ የሚሆነው ሜታ ተብሎ የሚጠራውን ከብር የተሰራ የአንገት ጌጥ ከሁለቱም ወገን ወስዳችሁ ወንዝ ውስት በመጣል ከልባችሁ ይቅር መባባል ብቻ ነው”። ይህም የአዛውንቱ ምክረ-ሃሳብ ተቀባይነት እኝቶ በስተመጨረሻ ሰላም ወረደ ይባላል።

እናላችሁ፤ በውሻ የተጀመረ ፀብ ቀስ በቀስ ሰፍቶ ለጎሳ ግጭት ምክንያት ሲሆን፤ “ትንሿ ቀዳዳ ትልቁን መርከብ ታሰምጣለች” ይሉት ምሳሌን አያሳይም?... ትንሽ ነው ያልነው ክፍተት ጓደኝነትን ሊያበላሽ እንደሚችል፤ ቀላል ነው ያልነው ነገር ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍለን የምታሳይ ታሪክ ትመስላለች። አንድዬ ብቻ አቅለነው ከሚያቀለን ጉድና መከራ ይጠብቀን። ቸር እንሰንብት።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1056 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 418 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us