“እንቁ” እና “ጣጣ”

Wednesday, 09 September 2015 14:17

እህሳ ይህቺ ደመወዝ አልባ ወርሃ-ጳጉሜ እንዴት ይዛችኋለች ጐበዝ! መቼም ዓመት በዓል ሲደርስ ጭንቅ-ጥብቡ እንደጉድ ነው። በተለይ “እንቁጣጣሽ”!... እኔ የምለው [አንዳንድ] የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደሚሉት “እንቁጣጣሽ” ማለት “እንቁውን” ለእነሱ፤ “ጣጣውን” ደግሞ ለእኛ እንደማለት ነው እንዴ?... ልክ ነዋ! እኛ እኮ በዓል አክባሪ ሳንሆን በዓል አድማቂዎች እና አድናቂዎች ብቻ ከሆንን ሰነባበትን።

 

በዓል ሲመጣ ከዶሮ አቅም እንኳን “ዶሮ ድሮና ዘንድሮ” የሚያሰኝ ታሪክ የሚፃፍላት ዓይነት ጉደኛ ለውጥ ማሳየት ከጀመረች ቆይታለች። ድሮ-ድሮ ዶሮን አስሮ ወደ ጓሮ ነበር። ዘንድሮ ልጄ ከዶሮ አቅም የሳሎን ውሻ ይመስል ሶፋ ላይ ልናስቀምጥ ምንም ላይቀረን እኮ ነው።

 

እኔ የምለው ኑሮ እንዲህ ከዓመት ዓመት በሮኬት ፍጥነት እየተወነጨፈ የእኛ ነገር ምን ሊውጠው ይሆን? እስቲ እዚህች’ጋ ስለ ዶሮ ከተነሳ አይቀር አንዲት ጨዋታ ልጥቀስ፤ እንዲሁ የበዓል ሰሞን መሆኑ ነው። ሴትየዋ ወደ አንድ ዘመናዊ ሱፐርማርኬት ይገቡና ረከስ ያለ ዋጋ ያለውን ዶሮ ስለመፈለጋቸው ይጠይቃሉ። የጠየቁት አልጠፋም የሽያጭ ባለሙያው መኖሩን ነግሯቸው ወደ ውስጥ በመግባት በላስቲክ የተጠቀለለች ዶሮ ይዞ መጣ።

 

ታዲያ ሴትየዋ በላስቲክ የመጣላቸውን የዶሮ ብጥስጣሽ (የዶሮ ብልት ማለቱ አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነው) ቆጥረው ሲያበቁ ድንገት አንድ እግር እንደሌላት (እንደጐደላት) አስተዋሉና፣ “ይህቺ ዶሮ’ኮ አንድ እግር የላትም” ሲሉ ወደ ሻጩ እየተመለከቱ ጠየቁት። ሻጩም ፌዘኛ ኖሮ ምን ቢላቸው ጥሩ ነው? “እማማ ዶሮዋን የሚፈልጓት ሊበሏት ነው ወይስ ሊያስደንሷት?” ብሎላችሁ እርፍ። ይህቺ ናት ጨዋታ አትሉልኝም። (እኛ ግን እንላለን የሚሰጥ ካገኘን አንድ ዶሮ አይደለም አንድ እግርም (ታፋም) ቢሆን እንቀበላለን፤ አራት ነጥብ)

 

እናላችሁ የእኛም ነገር “ሊበሏት ነው ወይስ ሊያስደንሷት?” እያሰኘ እንዲህ ግራ ሆኖ “የትራጃይ-ኮሜዲ” አይነት ተቃርኖ የሚታይበት ኑሮ ከሆነ ሰነባብቷል። ታዘቡኝ በቅርቡ “ዶሮን ድሮ እንደማውቃት” የተሰኘ መጽሐፍ ለገበያ ውሎ ታነባላችሁ።

 

ከሰሞኑ ነው አሉ፤ ሁለት ሴቶች ከገበያ መልስ መንገድ ላይ ተገናኝተው ይጠያየቃሉ። “አንቺዬ ገበያው እንዴት ነው?” ጠየቀች ወደ ገበያው የምትሄደው ሴት። “ኧረ ተይኝ እቴ ሁሉም ነገር ብሶበታል። ሽንኩርቱ ብትይ በርበሬው፣ ዘይቱ ሁሉም ተወዷል እህሉማ አይጣል ነው፤ በአጠቃላይ ሁሉም ነገር ተወዷል!” እርር-ድብን ያለችው ገበያተኛ መለሰች። በዚህ ጊዜ ተስፋ ሳትቆርጥ ወደ ገበያ የምትሄደው ሴት ሌላ ጥያቄ ሰነዘረች፤ “ለመሆኑ እነበሬስ ዋጋቸው እንዴት ነው?” የተሰጣት ምላሽ ምን ይመስላችኋል፤ “እነበሬ ሰማይ፣ እነፍየል ሰማይ፣ እነበግና እነዶሮም  ዋጋቸው ሰማይ ነክቷል። ተይኝ ባክሽ ዘንድሮ ሁሉም ነገር ውድ ሆኗል?” አለቻት። “የሁሉም ዋጋ ሰማይ ሲወጣ ታዲያ ምን ይሆን የወረደው?” ጠየቀች የቀድሞዋ፤ “የወረደውማ በአንድዬ አምሳል የተፈጠረው ሰው ብቻ ነው” ብላላችሁ እርፍ፤ ይህቺ ነገር ቅኔ መሆኗ ነው እንዴ?... አንድዬ ብቻ ከሰው ተርታ አውጥቶ ከሚያራክስ ኑሮ ይሰውረን አቦ። እዚህች’ጋ ደግሞ እንደሚከተለው ቅኔ እንዘርፋለን፤

 

ተቸግሬያለሁ በዓል ደርሶብኝ፣

እባክህ አምላኬ አሳልፍልኝ።

 

 

ለማንኛውም እንደሩጫውና እንደኳስ ሁሉ የበዓሉንም ነገር ከሀብታሞቹ (ከባለ ዕንቁዎቹ) መንደር በቀጥታ ይተላለፍልንና አንደኛችንን ከቤታችን ሳንወጣ የምንከታተልበት ፕሮግራም ይዘጋጅልን (ቂ.ቂ.ቂ!)… እንቁጣጣሽ ለእነሱ ሲሆን፤ “እንቁ!”፤ ለእኛ ሲሆን ደግሞ “ጣጣው” ብቻ ነው የቀረን ማለት ይሄኔ ነው።

 

ከመሰነባበታችን በፊት የምትከተለዋን የአባቶች ጨዋታ ጠቅሰን እናሳርግ፤ በአንድ መንደር የእሳት ቃጠሎ በድንገት ይነሳና “የሰው ያለህ፤ ኸረ የሰው ያለህ!...” የሚል ጩኸት ያስተጋባል። ታዲያ በመንደሩ አቅራቢያ የሚኖር አንድ ዓይነ-ስውር ጩኸቱንና አባባሉን ሰምቶ ባለቤቱን ወደ ስፍራው ውሰጂኝ ሲል ይማፀናል። “ደግሞ አንተ ምን ታደርጋለህ?” ስትል በንቀት መለሰችለት። “የሰው ያለህ! እየተባለማ ሰምቼ አልቀመጥም ውሰጂኝ” ብሎ ስለጨቀጨቃት ሳይመስላት ፈቃዱን ለመሙላት ስትል ብቻ ይዛው ትወጣለች።

 

ከስፍራው ሲደርሱ ቃጠሎው አይሎ ኖሮ ጥሪው ተቀይሮ፣ “የጎበዝ ያለህ! ኸረ የጎበዝ ያለህ!...” የሚል ጩኸት ያስተጋባ ጀመር። ይሄኔ ዓይነ-ስውሩ ወደባለቤቱ ጠጋ ብሎ “አሁን መልሺኝ” አላት ይባላል። ይኸውና በዓል ሲመጣ እኛም “ከሰው ያለህ!” ወረድ የሚያደርገን የጥሪ ለውጥ ይመጣና “የጎበዝ ያለህ!” ይሆንብን ይዟል።… ለማንኛውም አንድዬ አዲሱን ዓመት ስንጠራ እንደ አቅማችን “አቤት!” የምንልበት ያድርግልን። ከመሞት መሰንበት ደግ ነውና ቸር እንሰንብት፤ ለሁላችሁም መልካም አዲስ ዓመት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1857 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 915 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us