በአዲስ መልክ ብንጀምርስ?

Wednesday, 16 September 2015 14:06

እንኳን ከዘመን - ዘመን አሸጋገረን ወዳጆቼ!. . . ዕድሜና ጤናውን ሳይነፍገን፤ የጠየቅነውን ሳያሳጣን እንደለጠጥነው ዕቅድ ሳይሆን እንደአቅማችን በሰላም የምንኖርበት አዲስ ዓመት ያድርግልን። መቼም አዲስ ዓመት ሲመጣ በአዲስ መልክ የማይጀመር ነገር የለም። (ይብላኝ እንጂ ለአውራው ፓርቲያችን የእርሱ አዲስ ዓመት እንደው በየአምስት ዓመቱ ነው የሚከሰተው፤ ይህንን ሳስበው ጳጉሜ 6 ልደቱን የሚያከብር ሰው እና ኢህአዴግ ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋላ መገናኘታቸው ይደንቀኛል።)

ለማንኛውም “ለአሸናፊዎች ዛሬ የመጨረሻ ቀን ናት” እንዲሉ የሥነ-ልቦና ሊቃውንት፣ እኛም ዛሬን እንደመጨረሻ ቀን አድርገን ለሌሎች የሚተርፍ እና በበጎ የምንታወስበት ስራን ለመስራት ያብቃን አቦ!. . . በየተሰማራንበት የስራ መስክ ሁሉ በአዲስ መልክ፣ በአዲስ ብርታትና በአዲስ ጉልበት ስራችንን ሰርተን ለአዲስ ውጤት የማንተጋ ከሆነ ድምራችን ሁሉ ያው እንደአምናና ካቻምናው የወረደ መሆኑ አይቀርም።

ራሳችንን አበርትተን በአዲስ መልክ ስራ ጀምረናል፤ በአዲስ መልክ ፍቅር ጨምረን፤ በአዲስ መልክ ትዳር ጀምረናል፤ ዕድገት አሳይተናል ካላልን በስተቀር ህይወትን ባሉበት መርገጥ አሰልቺ ያደርጋታል። (አንዳንዶች አዲስ ዓመት ብሎ ነገር የለም የቁጥር ለውጥ እንጂ ይላሉ፤ ወዳጄ ቁጥርንስ ቢሆን ለመነቃቂያ ተጠቅመን “በአዲስ መልክ ኑሮ ጀምረናል” ብንል ምን ይለናል? እዚህች’ጋ ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል ዓለም ለብርቱዎች እንጂ ለሰነፎች ቦታ እንደሌላት “የዕውቀት ብልጭታ” በተሰኘው መጸሐፋቸው ውስጥ እንደሚከተለው ግጥም ይጠቃቅሳሉ።

ህይወት ጦርነት ነው ዋጋህን የሚያሳይ፣

መታገል ግድ ነው ስትኖር ባለም ላይ።

በገዛ -እጁ ወድቆ በቁሙ እየሞተ

መታገል ያልቻለ ልቡ እየታከተ

የሚያነሳው የለም በፍቅር በእርዳታ

በዚች በመሬት ላይ ፍጡር ካልበረታ

ጥንቱን አልተሰራም ለሰነፎች ቦታ።

በአዲሱ ዓመት ስንፍና ቦታ እንዳያሳጣን ተግተን መስራት ነው የሚያዋጣን ወዳጄ። የስራ ነገር ከተነሳ ላይቀር በሰራተኛና በአሰሪ መካከል የሚፈጠሩ ቀላል ነገር ግን አስቂኝ አለመግባባቶችን እስቲ እንጠቃቅስ። ሴትየዋ እችላለሁ ብላ በደላላ ተደራድራ የገባች ሰራተኛቸው ምንም ልትሰራባቸው ባለመቻሏ ቢያበሳጫቸው ጊዜ ያስጠሯታል። “ሰማሽ እሰራለሁ እንዳልሽ መስራት መቻል አለብሽ፤ አለበለዚያ ሌላ ሰራተኛ አመጣለሁ” ሲሏት ሠራተኛ ሆዬ ምን ብትል ጥሩ ነው፣ “እውነትዎን ነው እሜቴ ስራው እኮ መአት ነው ስራውን የምትችልና እኔንም የምታግዘኝ ሌላ ሰራተኛ ያስፈልገኛል” ብላላችሁ እርፍ።

አንዳንድ አሰሪ ደግሞ አለላችሁ እርሱ ግራ ተጋብቶ ሰራተኛውን ሁሉ ግራ የሚያጋባ፤ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ እኮ አንዳንድ መስሪያ ቤቶች ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ አሰሪዎች ሠራተኛውን ስራ ከማሰራት ይልቅ በእነርሱ ጉዳይ እንዲጠመድ በማድረግ ራሳቸው ለሰራተኛው ስራ የሚሆኑ ሊያጋጥሟችሁ ይችላሉ። ለምሳሌ የሚከተለውን ባለታሪክ ተመልከቱት። ሰውዬው በስራ ብዛት ራሱ ተካልቦ ሰራተኞቹንም የሚያካልብ የስራ ኃላፊ ነው። በተለይ የዚህ ፀሐፊ ስራዋ ሁሉ በትንሹም በትልቁም ነገር እየተጠራች ይህን ሰው ማስታወስ ብቻ ከሆነ ሰነባብቷል። ታዲያ አንድ ቀን ፀሐፊውን በአስቸኳይ እንድትመጣ ድምፁን ከፍ አድርጎ ከመጣራቱ ልጅት ቀልጠፍ ብላ ወደቢሮው ዘው አለች። “እባክሽ እስኪሪብቶዬን ጣኩት እስቲ ፈልጊልኝ፤ አሁን እኮ በእጄ ይዤው ነበር” ብሎ ነገሩን ሳይጨርስ በሳቅ እንደተሞላች “እስክሪብቶው እኮ ጆሮህ ላይ ነው አለቃዬ!” ፀሐፊው እንደወትሮዋ አስታወሰችው። ታዲያ አለቅዬው ቀጥሎ ምን ቢጠይቃት ጥሩ ነው? “በጣም ስራ ስለምቸኩል እስቲ ደግሞ አሁን ፈጠን ብለሽ በየትኛው ጆሮዬ በኩል እንዳስቀመጥኩት ንገሪኝ፤ ቶሎ በይ?” ቂ-ቂ-ቂ-! ይህቺ ናት ጨዋታ ማለት ይሄኔ ነው። አንዳንድ ሰው ግን አይገርማችሁም? በሆነ ባልሆነ የቤታቸውን ሰራተኛ ካላዋከቡ፤ ካላስጠነቀቁና ደሞዝ ካልቆረጡ ወይም ደግሞ ጮኸው ካልተቆጡ፤ ሰውን ካላጉላሉና በስብስባ ጎልተው ካልዋሉ የሰሩ የማይመስላቸው ስንት አይነት ኃላፊዎች አሉ መሠላችሁ?. . .

አንድዬ ብቻ በአዲሱ ዓመት ለከንቱ የምንዋከብ፤ ለከንቱ የምንደክም፤ ለከንቱ የምናሰራ፤ ለከንቱ የምንጠራ እንዳያደርገን አቦ። በአዲሱ ዓመት ጥረታችን የሰመረ፤ ትጋታችን የተሳካ፤ ህልማችን እውን የሆነ፤ ተስፋችን የተጨበጠ ይሆን ዘንድ ከአሁን ጀምሮ በአዲስ መንፈስ ስራችንን ብንጀምረውስ ጎበዝ!?. . . ቸር እንሰንብት።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
996 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 91 guests and no members online

Archive

« July 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
            1
2 3 4 5 6 7 8
9 10 11 12 13 14 15
16 17 18 19 20 21 22
23 24 25 26 27 28 29
30 31          

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us