“ባቡሩ መጨረሻ ነኝ!”

Wednesday, 23 September 2015 13:48

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!? . . . እህሳ “እልም አለ ባቡሩ” ይሉት ዘፈን በአዲስ መልክ መመለስ ያለበት አይመስላችሁም? እኔ የምለው ድሮ ባቡሩን በተመለከተ ቅኔ ተዘርፎብን እንደነበር ታውቃላችሁ፤

ባቡርና አውሮፕላን መኪና የላችሁ

የሀገሬ ልጆች ካውሮፓ ሩቅ ናችሁ።

. . . እንጃልን እንግዲህ መጀመሪውን አይተነዋል፤ መጨረሻውን ግን እንጃልን። . . . እኔ የምለው እሁድ በባቡር ላይ የተያየነው ሰዎች ለመጀመሪያ እና ለመጨረሻ ጊዜ መሳፈራችን ይሆን እንዴ? በቃ እኮ የባቡሩ መጨናነቅ ባስዬን በስንት ጠዓሙ እንድንል አሰኝቶን ነበር እኮ። (እስቲ እዚህች’ጋ ድምፃችንን ዝቅ አድርገን እናሽሟጥ፤ አንዳንድ ተሳፋሪዎች ቻይናውያን በሚያሸከረክሩት ባቡር ውስጥ በመሳፈራቸው መጨረሻው ቤጂንግ መስሏቸው ነበር ምናምን የሚባለው ሃሜት እውነት ነው እንዴ? ቂ-ቂ-ቂ!)

የምር ግን እንደው በግብር ይውጣ የምንሰራው ነገር እኮ መገለጫው በምንሳፈረው ባቡር ብቻ አይመስለኝም። ልክ ሰውዬው “የት ነዎት?” ሲባሉ፣ “ባቡሩ የደረሰበት መጨረሻ እወርዳለሁ” እንዳሉት ሁሉ፤ አቅደንና አልመን ከመጓዝ ይልቅ “እሱ አንድዬ ያለበት ይሁን” በሚል መንፈሳዊነት ድንኳን ስር ተጠልለን፣ ለመድረሻችን ዕቅድ ማውጣት ካቃተንማ መላው ጠፍቶብናል!. . . ከነአባባሉስ “ሰው ያስባል አምላክ ይፈፅማል” ይባል የለ እናስብ እንጂ ጎበዝ። እዚህች’ጋ የሀገራችን ሰው የተቀኛትን ቅኔ ጣል አደርግና ከባቡር ትረካችን ወራጅ አለ እንላለን።

ወረር ያለ ሽበት በጣሙን ያልነጣ፣

አበጥረው ፀጉር ራሴ ሳላጣ

እንዴት እባላለሁ ይህ ሰው መላጣ።

(በነገራችን ላይ ቅኔው የገባው ሰው መላውን ወዲህ ይበልልን)

ለማንኛውም ስለመጀመሪያው ሲባል መልካሙን ተመኝተን አልፈነዋል። እኛን የሚናፍቀን ቀጣዩና መጨረሻው ነው። የመጨረሻ ነገር ከተነሳ ላይቀር በመጀመሪያው ዕለት ባቡር ተሳፍሮ የገባ ሰው ሁሉ ትኬት ሲቆርጥ ምን እያለ እንደነበር ታዝባችሁልኛል? ትኬት ቆራጭ፣ “የት ነዎት?” ተሳፋሪ፣ “ባቡሩ መጨረሻው ነኝ” አንድዬ ብቻ የራሱን መድረሻ ሳይሆን የባቡሩን መጨረሻ አስቦ ከሚሳፈር ሰው ይሰውረን።

አንዳንድ ነገሮችም መጨረሻውን ያሳየኝ ወይም መጨረሻውን ያሰማኝ የሚያስብሉን አይነት ነው። እስቲ ደግሞ ከባቡሩ ወርደን ወደመኪናው እንመለስ። መቼም ይህ ዓመት አደጋን “ሀ” ብለን የሰማንበት ሆኗል። ለማንኛውም ትዝብታችንን በጨዋታ ለማዋዛት ያህል መንገድ ቀመስ ወጎችን እንጠቃቅሳለን።

ሰውየው መኪናውን በፍጥነት ወደቤቱ እያሽከረከረ ነው። የመኪናው ፍጥነት ከተፈቀደለት በላይ መሆኑን ቢገንዘብም ማንም አያየኝም በሚል ፈሊጥ ግልቢያውን ቀጠለ። ድንገት ግን በኋላ መመልከቻ መስታወቱ (ስፖኪዮ) ውስጥ የፖሊስ መኪና እየተከተለው እንደሆነ አየ። ይሁን እንጂ ፍጥነቱን ከመቀነስ ወይም ከመቆም ይልቅ፤ “ይሄንን ሰውዬማ ማምለጥ አለብኝ” በሚል ይበልጥ ፍጥነቱን ጨምሮ ተፈተለከ። የፖሊሱ መኪናም ፍጥነት መጨመሩ አልቀረም። በሰዓት 60፣70፣80፣90 ኪሎ ሜትር አልፎ 100 ሲገባ ሰውዬው መኪና ከፖሊሱ መኪና መብለጥ ስላልቻለች ተደረሰበት። ትራፊክ ፖሊሱ እጁን ከጎኑ ከሻጠው ሽጉጥ ላይ እንዳስቀመጠ ወደሾፌሩ ተጠጋ። ትራፊክ ፖሊሱ ብቻውን መሆኑን ያረጋገጠው ሾፌሩ መጀመሪያ ድንጋጤ ቀጥሎ ፀፀት ተሰማው። ፖሊሱም ወደመስኮቱ ቀረብ ብሎ፣ “መጀመሪያ መንጃ ፈቃድህን አሳየኝ ቀጥሎ ደግሞ ከልብህ ይቅርታ ከጠየከኝ እለቅሃለሁ” አለው። በፖሊሱ ንግግር የተገረመው ሾፌሩ መንጃ ፈቃዱን አውጥቶ እየሰጠው፣ “ከሳምንት በፊት ሚስቴ እኔን ጥላ ያንተን በመሰለ መኪና ውስጥ ከትራፊክ ፖሊስ ጋር ስትሄድ አይቻታለሁ። ቅድምም በኋላ መመልከቻ መስታወቱ ውስጥ ስመለከት ያ ፖሊስ ስለመሰልከኝ እንጂ ፍጥነቴን አልጨምርም ነበር” ሲል መለሰ። ፖሊሱ ግን በሰውዬው ንግግር ግራ ተጋብቶ፣ “ለመሆኑ ሚስትህን የወሰደው ትራፊክ ፖሊስ ብሆንስ ‘ሚስቴን አምጣ!’ ብለህ እንደመጋፈጥ እንዴት ፍጥነትህን ጨምረህ ትሸሸኛለህ?” ሲል ጠየቀው። በዚህ ጊዜ የሾፌሩ መልስ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? “ጌታዬ ሰውዬው ሚስቴን መልሶ የሚሰጠኝ ስለመሰለኝ እኮ ነው ለማምለጥ የሞከርኩት” ብሎላችሁ እርፍ። ይህቺ ናት ጨዋታ ማለት ይሄኔ ነው። ሚስቱን ግን ምን ያህል ቢጠላት ነው እንዲህ የሆነባት በናታችሁ?

ቀልዱስ ቀልድ ነው፤ ይሄ የመኪናና የፍጥነት ነገር ከተነሳ አይቀር አንድ ሌላ ወግ እንካችሁ፤ ነገርዬዋ የፈረንጆቹ ዋዘኛ ቀልድ ናት። ሰውዬው ከሶስት ጓደኞቹ ጋር ሆኖ መኪናውን በማሽከርከር ላይ ነበር። ድንገት ግን የሰውዬው ፍጥነትና የመኪና አነዳዱ ያላማረው ትራፊክ ፖሊስ መኪናውን እንዲያቆም አዞት ቆመ። መኪናውን የሚያሽከረክረው ሰው በሁኔታው ቢደናገጥም በስካር የደከሙት ሶስቱ ጓደኞቹ ከኋላው መተኛታቸውን አይቶ ተረጋጋ። ትራፊክ ፖሊሱ አሽከርካሪውን መንጃ ፍቃድ ከመጠየቁ ከእንቅልፉ የነቃው የመጀመሪያው ሰው፣ “አይ አንተ ሰውዬ ያለመንጃ ፈቃድ እያሽከረከርክ አስያዝከን አይደል” ሲል ጉድ አፈላ። ይባስ ብሎ ደግሞ ሁለተኛው ጓደኛቸው ከእንቅልፉ እንደባነነ ትራፊኩን በማየቱ፣ “ጠጥተህ ስታሽከረክር ተያዝክ አይደል?” ሲል አንጓጠጠው። ከሁሉም የባሰው ግን የሶስተኛው ጓደኛቸው ንግግር ነበር። “እኔ በፊትም በተሰረቀ መኪና የትም እንደማንደርስ ነግሬያችሁ ነበር፤ አልሰማ አላችሁኝ እንጂ!” ብሎላችሁ እርፍ። (መጨረሻውን አሳየኝ ማለት እንዲህ ነው፤ በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ ቂ-ቂ-ቂ)

አንድዬ ብቻ ከራሱም ከሰውም ካልተግባባ ሰው ጋር ከመዋልና ከመስራት ይሰውረን አቦ። “የት ናችሁ?” ስንባል ባቡሩ መጨረሻ ድረስ ይሁንልኝ ከማለት ይልቅ መድረሻችንን በውል አውቀን የምንንቀሳቀስበት ዘመን ይሁንል። መድረሻችን የኛ ግብ እንጂ የባቡሩ ግንብ እንዳይሆን ይመከራል። ዘንድሮ ጉዱን ልየውና መጨረሻውን ልየው እያልን ከመግባት ሰውሮ በእቅድ የምንገባበትና የምንወጣበት የዘመን ጉዞ እንዲያደርግልን ተመኘሁ። ቸር እንሰንብት።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
1114 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1034 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us