“ማየት ለብቻው ምንድነው?”

Wednesday, 30 September 2015 14:23

 

 

መቼም መስከረም በድርብርብ ወጪው በዝቶ ለብድር የሚያንደረድረን ወር ሆኗል። እንቁጣጣሽ፣ አረፋና መስቀል ተከታትለው እንዴት አለፉላችሁ ወዳጆቼ?!. . . ይመስገነው አንድዬንና ዓመቱ እምነት የበዛበት፤ መተሳሰብ የሰፈነበት፤ መግባባት ያለበትን ንፍገት የሚከስምበት እንዲሆንልን ተመኝቻለሁ።

ለዛሬ ትዝብት አዘል ጨዋታችን መንደርደሪያ ትሆነን ዘንድ ከሰሞኑ የሰማሁዋትን የየኔ ብጤ መለማመኛ ግጥም እነሆ፤

ዓይኔን ግንባር ያርገው፣ ብላችሁ አትማሉ

ይቸግር የለም ወይ፤ መሪ ማባበሉ።

ዓይኔን ግንባር ያርገው፤ ብሎ ይምላል ሰው

እንደኔ ጨለማን፣ አይቶ ያልቀመሰው።

በታክሲ ሰልፍ ላይ ሆኜ የኔብጤውን ተመላላሽ ስንኞች ባደመጥኩ ጊዜ ከዚህ ቀደም ያነበብኳቸው ሁለት ታሪኮች ታሰቡኝና “ግን - ግን ማየት ለብቻው ምንድነው?” ስል በቴዲ አፍሮ ላምባዲና ስልት ጠየኩ። . . . በአንዲት ከተማ ይኖር የነበረ አንድ ዓይነ ስውር ሰው ነበረ። ሰውዬው ምንም እንኳን ማየት የተሳነው ቢሆንም ዘወትር በምሽት ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀስ ግን ከእጁ የተለኮሰ ሻማ አይጠፋም ነበር። ታዲያ አንድ ምሽት እንደልማዱ በብርሃን የተጥለቀለቀ ፋኖሱን ይዞ ሲጓዝ በመንገድ ያልፉ የነበሩ ሶስት ጓደኛሞች በአግራሞት ተመለከቱት። እየቆየ ግን አግራሞታቸው ወደፌዝ ተቀየረ። እናም ወደዓይነ- ስውሩ ሰው ጠጋ ብለው፣ “ለመሆኑ አንተ ማየት የተሳነህ ሆነህ ሳለ ስለምንድነው ፋኖስ ለኩሰህ የምትዞረው?” ከጓደኛሞቹ አንደኛው ጠየቀ። “ጨለማ ስለሆነ ነዋ!” ሰውዬው መለሰላቸው። “አንተ ዓይነ-ስውር ነህ፤ ላንተ ጨለማና ብርሃን ምን ልዩነት አላቸው?” በማሽሟጠጥ የተሞላ ሌላ ጥያቄ ተወረወረለት። ይሄን ጊዜ ዓይነ -ስውሩ ሰው ብልህ ነበርና የጥያቄያቸው አካሄድ ስለገባው፣ “እንደናንተ አይነት ዓይን አለን ብለው የሚመፃደቁ ሰዎች እንዳይገጩኝ በመስጋት ነው ፋኖስ ይዤ የምዞረው” ብሎላችሁ እርፍ።. . . ይህቺ ናት ጨዋታ ማለት ይሄኔ ነው። እንዲህ ነው እንጂ ልክ ልካችንን መነጋገር። እውነት ግን ማየት ለብቻው ምንድነው ጎበዝ?

ስንትና ስንት ሃሳብ፣ ስንትና ስንት ሰው፣ ስንትና ስንት ቁምነገር በብርጭቆዎ አይናችን ብቻ እያየነው አለፈን መሰላችሁ። የሚታይ ነገር ሁሉ እውነት የማይታይ ነገር ሁሉ ሀሰት ሊባል አይችልም። ደግሞም አይተን ያላስተዋልናቸው፣ ወይም በማየታችን ብቻ ብልጣብልጥ ሆነን የሸነገልናቸው ስንት ጉዶች አሉን. . . በዚህች ታሪክ ውስጥ ፋኖስ ማለት ብዙ ነገር ማለት ነው። ፋኖስ ጨለማን በብርሃን የሚገልጥ ነው። ለኛም የዕውቀት ፋኖስ-ትምህርት ነው። የትዳር ፋኖስ ጋብቻ ነው። የስልጣን ፋኖስ ለምናገለግለው ህብረተሰብ በታማኝነት የምንሰጠው ተገቢ አገልግሎት ነው። የአዋቂነታችን ማሳያው ፋኖስ ደግሞ አስተዋይነታችን፣ አስተማሪነታችን፣ ቻይነታችንና ታጋሽነታችን ጭምር ነው። እናም በተንቀሳቀስንበት ሁሉ ማየት ለብቻ ምንድነው? እንዳንባል ለነገራችን ሁሉ “ፋኖስ” አያሳጣን።

አስተዋዮች እንደሚሉትም “ከዓይን ብርሃን- ልበብርሃን መሆን ይበልጣል” እውነት ነው። ከዚህ ቀደም አንደበተ ርዕቱ መጋቢ አዲስ እሸቱ ሲናገሩ እንደሰማሁት “ዓይነ-ስውር ማለት የሳሎኑ በርቶ የበረንዳው እንደጠፋበት ቤት አድርጋችሁ ቁጠሩት” ብለውናል ልክ ነው። አንዳንዶች ግን በብርጭቆ ዓይን ብቻ በመመልከታቸው አስተዋይነታቸውን ተነጥቀው ለስህተት ሲዳረጉ ብዙ ጊዜ አይተናል። እስቲ እዚህች’ጋ አንዲት አጭር ታሪክ እናስከትል።

ሴትየዋ ከጊዜ በኋላ ዓይነ-ስውር ይሆኑና ህክምና ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ በከተማው አለ የተባለ ዶክተር ተፈልጎ እንዲያክማቸው ይስማማሉ። በስምምነታቸውም መሰረት ዶክተሩ ሙሉ በሙሉ የማየት አቅማቸውን ሲመልስ ብቻ በርከት ያለ ክፍያ እንደሚፈጽምለት ውል ያሰራሉ። ዶክተሩ በሴትየዋ ቤት እየተመላለሰ ህክምናውን መስጠት ይጀምራል። ዳሩ ግን ዶክተሩ የእጅ አመል ያለበት ኖሮ፤ በሴትየዋ ውድ የሆኑ የቤት ዕቃዎች እንደ ልቡ ሳይሰረቅ አልቀረም። እናም ለህክምና ወደቤት ገብቶ በወጣ ቁጥር ከብቸኛዋ ሴትዮ ቤት አንድ ውድ ዕቃ ይዞ መውጣት የዘወትር ተግባሩ ሆነ። ምርጥና ውድ የሆኑ ከእንጨትና ከሸክላ የተሰሩ ጌጣጌጦችን፤ ሴትየዋ በስጦታ ያገኟቸውን የተለያዩ ዕቃዎችን የወሰደው ዶክተር ቲቪና ሬዲዮ አልቀረውም ነበር።

ከበርካታ ቀናት ህክምና በኋላ ግን ያው የእጅ አመል ያለበት ዶክተር የሴትየዋን የአይን ብርሃን መለሰው። አይናቸው እንዳየ በደስታ የፈነጠዙት ሴትየዋ የጎደሉትን የቤት ዕቃዎቻቸውን ፈልገው ባጡ ጊዜ፣ “ውድ ዶክተር ሙሉ በሙሉ ማየት አልቻልኩምና የተዋዋልነውን ሙሉ ገንዘብ ልከፍልህ አልችልም” አሉት። በሴትየዋ ሁኔታና ቃል - አባይነት የተበሳጨው ዶክተር ግን ጥርሱን ነክሶ፤ አንቀፅ ጠቅሶና ውሉን ይዞ ክስ በመመስረት ሴትየዋን ችሎት አቆማቸው።

ዳኛው ጉዳዩን መርምረው ሲያበቁ መጠየቅ ጀመሩ። “እዚህ ድረስ ሲመጡ ያለምንም ሰው መሪነት እንደመጡ ተመልክቻለሁ። በውላችሁ መሠረት ደግሞ ሙሉ በሙሉ ማየት ከቻሉ የተጠቀሰውን በርካታ ገንዘብ ሊከፍሉ ቃል ገብተዋል አይደል?” ዳኛው ሴትየዋን እያዩ ተናገሩ። “እውነት ነው ክብር ዳኛ ለመክፈል ተስማምቼ ነበር” መለሱ ሴትየዋ። “እንደማይዎ ዐይንዎ በደንብ ያያል ታዲያ ለምን ክፍያውን አይፈፅሙም?” ጠየቁ ዳኛው። “ክቡር ዳኛ ዶክተሩ እንደሚለው ገና ሙሉ በሙሉ ማየት አልቻልኩም። ማየቴን ለማረጋገጥ በቤቴ የነበሩትን ምርጥና ውድ ንብረቶቼን በቦታቸው እንዳሉ እርግጠኛ መሆን አለብኝ” ከማለታቸው ዳኛው የዶክተሩ ስራ ስለገባቸው የፍርዳቸውን አቅጣጫ በመቀየር ዶክተሩ ለሴትየዋ ካሳ እንዲከፍል አደረጉ ይባላል።

እናም አንዳንዴ ማየት ብቻውን ዋጋ የለውም፤ ማስተዋል ካልታከለበት በቀር፤ እንደግመዋለን ከዓይነ-ብርሃን ይልቅ ልበ ብርሃንነት ይበልጥብናል። አንድዬ ብቻ በአዲሱ ዓመት ደግደጉን የምንሰማበት፤ በጎበጎውን የምናይበትና መልካም መልካሙን የምናስተውልበት ያድርግልን አቦ፤ ቴዲ አፍሮ “ላምባዲና” ሙዚቃ የመጨረሻ ስንኞችን ለመሰነባበቻ እነሆ፡-

ያይኔ መቅረዙ ባዶ ነው፣

ማየት ለብቻው ምንድነው፤

ሳያይ ያመነ ሲጠራው፤

እይ ፍቅር መርጦ ሲያኮራው።    

ቸር እንሰንብት።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
1478 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 178 guests and no members online

Archive

« August 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
    1 2 3 4 5
6 7 8 9 10 11 12
13 14 15 16 17 18 19
20 21 22 23 24 25 26
27 28 29 30 31    

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us