“ከማማረር መማር ይሻለናል”

Wednesday, 07 October 2015 14:00

 

እህሳ የናፈቅናትን መስከረም እነሆ አገባደድናትም አይደል? ተመስገን ነው። ሰራተኛ በአዲስ በጀት ስራውን፤ ተማሪ ዕውቀት ቀሰማውን በአዲስ መንፈስና በአዲስ የጋራ ልብስ ጀምሯል። የትምህርት ነገር ከተነሳ አይቀር ይህቺን ጨዋታ እንካችሁ፤ ተማሪና መምህር በክፍል ውስጥ ተፋጠዋል።  ፊዜክስ መምህር ናቸው። ፊዚክስ ክፍለ ጊዜን ፈካ ለማድረግ አስበው፣ “አያችሁ ተማሪዎች በአንድ ወቅት አይዛክ ኒውተን የተባለው እውቅ ፊዚክሺያን ዛፍ ጥላ ስር ተቀምጦ ሳለ የአፕል ፍሬ ከቅርንጫፏ ተቀንጥሳ አናቱ ላይ ስላረፈች ነው፤ የስበት ህግ ቀመር የተገለፀለት። ይህ ታዲያ አያስደንቅም?” ብለው እንደዋዛ ጥያቄ ሰነዘሩ። ከተማሪዎቻቸው መካከል አንደኛው ድምፁን ከፍ አድርጎ ምን ቢል ጥሩ ነው? “እውነት በጣም ያስደንቃል መምህር፤ ነገር ግን እርሱም ልክ እንደኛ ክፍል ውስጥ መፅሐፍ ላይ እንዳፈጠጠ ቢቀመጥ ኖሮ ይህ “የስበት ሕግ” አይከሰትለትም ነበር” ብሎላችሁ በሾርኒ የክፍል ውስጥ ትምህርት እንደደበረው ንግር. . . ቂ-ቂ-ቂ!

ጎበዝ ትምህርት ለአንድ ህብረተሰብ የጀርባ አጥንት እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህንንም በግልጽና ውብ በሆነ ቋንቋ ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል “የቅኔ ውበት” በተሰኘ መፅሐፋቸው መግቢያ ላይ እንደሚከተለው አስፍረውት ይገኛል።

የድንቁርና ሌት ጨለማ አለፈ

የማስተዋል ንጋት ብርሃን ተነጠፈ

ድካምና ሙያ ዕውቀትና ጥበብ

ወጣ እንደጨረቃ ተዘራ እንደኮከብ

ካራቱ ማዕዘን እየለየ ቦታ

በምስራቅ በምዕራብ ተገኘ ብልጭታ

ደመናውን ቀዶ ማስተዋል ፈለቀ

ትምህርት ተፋፋመ ተስፋፋ ደመቀ።

አለን ያልነው ሀብት ንብረት ሁሉ ድንገት ሳይታሰብ ብን ብሎ በሚጠፋበት በዚህ ዘመን ትምህርትን የመሰለ ብቸኛ መመኪያ ከወዴት ይገኛል ጎበዝ!. . . “እውቀትና ጥበብ የግል የዘላለም ሀብት ናቸው” ያለው ማን ነበር? ለምን ቢባል ዕውቀትና ጥበባችንን ማንም ሊነጥቀን አይችልምና።

ንብና እርግብ ተገናኝተው እየተጨዋወቱ ነው። እርግብ ሆዬ በማፅናናት መንፈስ ሆና፣ “እኔ የምልሽ ወይዘሪት ንብ እንዲህ ታትረሽ እየሰራሽና ማር እያመረትሽ የሰው ልጅ ግን ያንቺን ማር እየሰረቀ እየበላና እየሸጠ ሲኖር ባንቺ ልፋት ሲከብር አያሳዝንሽም?” ወፍ ጠየቀቻት። ይሄኔ ወይዘሪት ንብ ምን ብትመልስ ጥሩ ነው “በፍፁም አላዝንም፤ ምክንያቱም የሰው ልጅ የሚሰርቀኝ ማሬን እንጂ የማር አሰራር ጥበቤን አይደለም” ብላላችሁ እርፍ፤ ይህቺ ናት ጨዋታ እንዲህ ልክ- ልካችንን እንነጋገር እንጂ (በነገራችን ላይ ንቢቱን ወስዳችሁ በምስሏ ከሚመራን መንግሥት ጋር እያምታታችሁ ለማንበብ የምትሞክሩ አንባቢያን ካላችሁ፣ እኔ የለሁበትም ከደሙ ንፁህ ነኝ ልክ እንደ ጲላጦስ?) ቂ-ቂ-ቂ!

ለማንኛውም ተምሮ የሚለወጥ አእምሮን አንድዬ አይንሳን። በሆነው ባልሆነው ባልገባን ነገር ከመማረር ተምሮ መመራመር ይበጀናል ጎበዝ! ቻይናውያንስ “አንድን ሰው ለመርዳት ከፈለግህ አሳ እያወጣህ ብቻ አትስጠው፤ ይልቅስ አሳ እንዴት እንደሚወጣ አስተምረው። ከዚያ በኋላ እንዴት እንደሚኖርና እንደሚበላ ያውቅበታል” የሚሉት ወደው መሰላችሁ?

በነገራችን ላይ መማር በትምህርት ቤት ብቻ የተወሰነ ነገር አይደለም። በክፉም በደጉም በየሄድንበት አንድ ነገር መማር የምንችል ይመስለኛል። ልብ ያለው ልብ ይበል ማለት ይሄኔ ነው። እዚህች’ጋ በቅርቡ ያነበብኳትን ጣፋጭ ታሪክ እነሆ፤

ሁለት በጣም የሚዋደዱ ጓደኛሞች በአንድ የንግድ ስራ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥረው መስራት ጀመሩ። ከዓመታት በኋላ የሁለቱ ጓደኛሞች አለቃ በሁለቱም የስራ ፍቅርና ታታሪነት መደነቁን ተናግሮ ምስጋና ከቸራቸው በኋላ አንደኛውን የሽያጭ ክፍል ኃላፊነት ስፍራውን እንዲወስድ ዕድገት ሰጠው። ምንም እንኳን ሁለቱም ብርቱ ሰራተኞች ቢሆኑም ለአንደኛው ብቻ ዕድገት በመስጠቱ ሌላኛው ቅር ተሰኘ። የቅሬታው ወሰን አልፎም ስራ ለመልቀቅ እንደሚፈልግ ለአለቅዬው በደብዳቤ አሳወቀ። በዚህ ጊዜ ይህን ወጣት ማጣት ያልፈለገው አለቃ፤ ምንም እንኳን ወጣቱ በስራው ታታሪ ቢሆንም የሚጎድለው ጥበብ እንዳለ እንዲያውቅ በሚል ሁለቱንም ጓደኛሞች ወደቢሮው አስጠርቶ፣ በገሀድ ሊመዝናቸው ፈለገ። እናም በመጀመሪያ ዕድገት አላገኘሁም ብሎ ቅሬታ ያቀረበውን ወጣት አስጠራውና “እስቲ ሂድና ወተት በገበያ ውስጥ መኖሩን አረጋግጠህ ተመለስ” ሲል ወጣቱን ላከው። ወጣቱ በፍጥነት ወደከተማዋ ዋነኛ ገበያ ሄዶ ተመለሰ። “ጌትዬ ወተት በብዛት በመሸጥ ላይ ነው” ሲል ከመመለሱ፤ አለቅዬው “አንድ ሊትር ወተት በምን ያህል ዋጋ እየተሸጠ ስለመሆኑ አጣራ” አለው። ወጣቱ ሰራተኛ ተመልሶ ወደገበያው ሄደ። “ጌትዬ አንድ ሊትር ወተት በ25 ብር እየተሸጠ ነው” ሲል መልሱን ይዞ ተመለሰ። አስከትሎም “የትኛው ወተት አቅራቢ በተሻለ ዝቅተኛ ዋጋ እንደሚያቀርብና በቀንስ ምን ያህል ሊትር ሊያዘጋጅልን እንደሚችል ታውቃለህ?” ይህን የአለቃውን ጥያቄ አሟልቶ ለመመለስ አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ ሳይሰለች እየተንደረደረ ወደገበያው ሄዶ መልሱን ይዞ መጣ። በዚህ ጊዜ አለቅዬው ዕድገት የሰጠውን የወጣቱን ጓደኛ ወደቢሮው እንዲገባ በማድረግ የመጀመሪያውን ተመሳሳይ ጥያቄ ሊጠይቀው ወሰነ። “እስቲ ባክህ ወተት በገበያ ውስጥ ስለመኖሩ አጣርተህ ንገረኝ” ሲል አዘዘው። ታታሪውና ዕድገት ያገኘው ወጣትም ከቢሮ ወጥቶ በፍጥነት በከተማዋ ወደሚገኘው ትልቅ ገበያ በመሄድ የወተቱን ሁኔታ አጣርቶ እንደተመለሰ የሚከተለውን መልስ ሰጠ፤ “አለቃዬ በርካታ መደብሮች ወተት እየሸጡ ነው። ነገር ግን አንደኛው ሱቅ በተለየ አንድ ሊትር ወተትን በ23 ብር እየሸጠ ነው። ይህ መደብር በቀን 300 ሊትር ማቅረብ የሚቻል ሲሆን በትራንስፖርት በኩልም ችግር እንደሌለበት ነግሮኛል” ሲል በዝርዝር አስረዳ።

በዚህ ጊዜ ዕድገት የተነፈገው ወጣት በጓደኛው ፈጣንና መረጃ አዘል ማብራሪያ በጣም ተደነቀ። እርሱ ሶስት ጊዜ የተመላለሰበትን ጉዳይ ጓደኛው በአንድ ጊዜ ጨርሶ መምጣቱን አስተዋለ። እናም በሁለቱ መካከል ያለው የአሰራር ሂደት ልዩነቱ ስለገባው ከወዳጁ ሊማር ቃል ገብቶ ስራውን ቀጠለ ይለናል ታሪኩ። ብልህ ሰው እንዲህ ነው አጠገቡ ካሉ ሰዎች ይማራል፤ ከራሱ ስህተት ይማራል፤ ከአጋጣሚዎቹ ይማራል፣ ከታላላቆቹም ሆነ ከታናናሾቹ ይማራል። ከትምህርት ቤት ብቻ አይደለም። ለማንኛውም መማር ለዘላለም ይኑር አቦ! ቸር እንሰንብት!!!        

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1608 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 81 guests and no members online

Archive

« July 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
            1
2 3 4 5 6 7 8
9 10 11 12 13 14 15
16 17 18 19 20 21 22
23 24 25 26 27 28 29
30 31          

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us