የማናውቀው ነገር

Wednesday, 14 October 2015 13:24

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . እኔ የምለው ያወቅነው የሚመስለን ነገር ግን ያላወቅነው ነገር የበዛ አልመሰላችሁም?. . . እውነቴን እኮ ነው። ወዳጄ ነው ያላችሁት ሰው ድንገት ባላንጣችሁ ሲሆን፤ ዘመዴ ነው ያላችሁት ሰው ድንገት ባዳ ሲሆን፤ ትልቅ ሰው ነው ያላችሁት ድንገት ትንሽ ሲሆን፤ ዳር ደርሶልኛል ያላችሁት ነገር ገና ሲጀመር፤ አውቄዋለሁ ያላችሁት ነገር ድንገት የማታውቁት ሆኖ ሲገኝ ምን ይባላል?

አባት ልጄን አውቀዋለሁ ብሎ ሽንጡን ገትሮ ይከራከራል። ልጅ ግን አባቱ እንደማያውቀው ገብቶታል። ታዲያ የዓመቱ አጋማሽ ላይ ልጅ ከትምህርት ቤት አንድ ደብዳቤ ይዞ ይመጣል። ደብዳቤው ልጅ በትምህርቱ ደካማ መሆኑን፣ አዘውትሮ ክፍል የማይገባ መሆኑን፣ የወላጅ ክትትል የሚያስፈልገው መሆኑን በዝርዝር የሚያትት ነበር። ልጅ ግን ይሄን ነገር ለአባቱ ማሳየት ሃፍረት ስለፈጠረበት መላ ዘየደ። (ያው እንደሚታወቀው የመብራትና የውሃ መጥፋት የተለመደ ነገር ነውም አይደል?). . . ድንገት ምሽት መብራት ድርግም ሲል ጠብቆ ልጅ  ሆዬ ወደአባቱ ቀረበና። “አባዬ በጭለማ ውስጥ ስምህን መፃፍና መፈረም እንደምትችል ተወራርጃለሁና አታሳፍረኝም አይደል?” አለ።

የነገሩ አካሄድ ያልገባው አባትም፣ “ምን ችግር አለው፤ በጨለማ ውስጥም ቢሆን የራሴን ስም ፅፌ መፈረም አያቅተኝም ከማለቱ ልጅ ሮጥ ብሎ የትምህርት ቤቱ አስተዳደር የፃፈለትን ደብዳቤ አስጠግቶ “እስቲ እዚህች’ጋ ስምህን ፅፈህ ለመፈረም ሞክር” በማለት አግባባው። አባት የተባለውን ፈፀመ። ድንገት ግን ተጋለጥ ሲለው የጠፋው መብራት ከች ሲል፤ ማህተም ባለበት ህጋዊ የትምህርት ቤት ደብዳቤ ላይ መፈረሙን የተገነዘበው አባት የልጁን ጉድ አንብቦ ደረሰበት ይባላል።

ያወቅነው የመሰለን ልጅ፣ ያወቅነው የመሰለን የትዳር አጋር፣ ያወቅነው የመሰለን መንገድና ያወቅነው የመሰለን አካሄድ ሁሉ ድንገት ሲቀያየር አያድርስ ነው። ከሁሉም ከሁሉም ደግሞ ካንተ በላይ እኔ አውቅሃለሁ። ካንተ በላይም እኔ አውቅልሃለሁ የሚል ከመጣ ምን ይውጠናል?

እዚህች’ጋ አንዲት ጨዋታ እናመጣለን። መምህሩ ተማሪዎቹን ሂሳብ እያስተማረ ነው። በመደመር ሃሳባዊ ስሌት የልጆቹን ዕውቀት ለማበልጸግ ያሰበው መምህር ታዲያ ከፊት ከተቀመጡት ተማሪዎች መካከል የአንዱን ስም ጠርቶ፣ “አሁን ለምሳሌ አንተ 100 ብር አለህ እንበል። ከዚያም አባትህ አንድ መቶ ብር እንዲጨምርልህ ጠየከው በድምሩ ስንት መቶ ብር ይኖርሃል ማለት ነው?” ከማለቱ የተማሪው ምላሽ ምን ቢሆነ ጥሩ  ነው? “ያው ለምሳሌ አለህ ያሉኝ 100 ብር ብቻ ነው የሚኖረኝ” መምህሩ እንደመናደድም እንደመቆጣትም እየቃጣቸው፣ “ለምንድነው 100 ብር ብቻ የሚኖርህ፤ አባትህም እኮ 100 ብር ጨምሮልሃል፤ መደመር አታውቅም ማለት ነው እንዴ?” ቢሉት ተማሪ ሆዬ ምን አለ መሰላችሁ?” እኔማ መደመር አውቃለሁ፤ እርስዎ አባቴን አያውቁትም እንጂ፤ አባቴ እኮ መቶ ብር ከሚሰጠኝ መቶ ኪሎ ሜትር ቢያስሮጠኝ የሚመርጥ ቆንቋና ነው” ብሎላችሁ እርፍ፤ ቂ-ቂ-ቂ! ይህቺ ናት እንግዲህ ጨዋታ ማለት። (ስንትና ስንት እናውቃለን ብለን የሰጠነው ምሳሌ እንደዚህ ጉድ አፍልቷል መሰላችሁ፤ በልጁ ከሚታማ አባት ይሰውረን አቦ)

እናላችሁ “ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው” ብንባልም፤ ያወቅነው የመሰለን ነገር በዝቶ ነገር ግን በተጨባጭ የማናውቀው ነገር ከበረከተ ነገር አለ ማለት ነው። . . . ሰውዬው በሚስቱ ጨቅጫቃ ባህሪይ ተናዶ በተደጋጋሚ ጊዜ ለጓደኛው ያማታል። ታዲያ አንድ ቀን ይህ ሃሜት የሰለቸው ጓደኛ “ቆይ እስቲ ብመክራት ትለወጣለች” በሚል አንድ ቀን ድንገት ቤታቸው ይሄዳል። ሚስት ሆዬ እንደምንጣፍ ልነጠፍልህ፤ እንደጃንጥላ ልዘርጋልህ አይነት በፈገግታ የተሞላ አሪፍ መስተንግዶ ለባሏ ጓደኛ አደረገችለት። ታዲያ በቀጣዩ ቀን ሁለቱ ጓደኛሞች ስራ ቦታ ተገናኝተው፣ “አንተ ሚስትህን የምታማት ዝም ብለህ ነው ባክህ!. . . እናት የሆነች ሴት አይደለች እንዴ?” ብሎ ምሬቱን ቢያጣጥልበት ጊዜ ባል ምን ቢል ጥሩ ነው? “የኔ ጌታ አንተ የማታውቀው ብዙ ነገር አለ “ውስጡን ለቄስ” ብለን እንለፈው፤ እሷ’ኮ ማለት ለቤት ቀጋ ለውጪ አልጋ ናት። እኔም ይሄ እንክብካቤዋ አታሎኝ ነው። አወኳት ብዬ አግብቻት የምንገበገበው” ብሎላችሁ እርፍ። አንድዬ ብቻ አውቀነዋል ብለን አፋችንን ሞልተን ተናግረን እንዳላወቅነው ከሚያዋርደን ነገር ሁሉ ይጠብቀን አቦ! ነገሩ ነው እንጂ ጩቤ ሰው አይጎዳም እንዲሉ፤ ነገርን ያወቅን መስሎን ባናውቀው እንኳን እንማረው ይሆናል። ዳሩ ግን እደር ባይቆጭ ያንገበግባል ተብሏል። እናም ቅኔ እንዘርፋለን፤

ዋናውስ በሽታ ምንም አልጎዳቸው

ካገገሙ ወዲያ ግርሻ ገደላቸው።

እንዲል ያገራችን ሰው።  ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
871 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 894 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us