የተረሳ ጥያቄ!

Wednesday, 21 October 2015 15:14

 

 

ወዳጃችን በጠና ታመመ። የታመመው ግን ኩላሊቱን አይደለም፤ ጉበቱንም አይደለም፤ ሆዱንም አይደለም፤ የታመመው ልቡን ነው። በሌለ በሽታ ልቡ ደከመበት። ልቡ የደከመው ግን አንዲትን ልጅ ወዶ ነው። ማንን እንደወደደ፣ መውደዱ መቼ እንደተጀመረና እዚህ ደረጃ እንዴት እንደደረሰ ግን ማናችንም ማወቅ አልቻልንም። እናም ወዳጃችን በፍቅር ክፉኛ ማቀቀ። ….. ምግብን እንደ ጠላቱ ይሰለቅጠዋል የሚባልለት ወዳጃችን ምግብ የተባቱ ማለት ጀመረ። መጠጥ ሲያገኝ አሸዋ ነው የሚባልለት ወዳጃችን መጠጥ አስነዋሪ ነው ማለት አዘውታሪ ሆነ። እናም ወዳጃችን በፍቅር ማቆ፣ ገላው አልቆ፣ ፊቱ ደርቆ፣ ከአልጋው ተጣብቆ ውሎ ማደር የዘወትር ተግባሩ ሆነ።

ወዳጅ ቤተሰቡ ሁሉ ጭንቅ ገባው። ብለነው ብለነው እምቢ ቢለን የልቡ ነገር ወደጭንቅላቱ ሳይሄድ አልቀረም የሚል ሀሳብ ገባን። እናም “ልጅቱን ያያችሁ!” ማለት የእኛ የወዳጆቹ ስራ ሆነ። ልጅቷን ማንም አያውቃትም፤ ከአፍቃሪው በስተቀር። የጨነቀ ነገር የጠፋለት መላ ሆኖ ቀናት አለፉ። ያም ሆኖ የወዳጃችን የምግብና የመጠጥ ፍላጐት ተፈልጐ ሊገኝ አልቻለም። (ይሄ ሰውዬ ቤቱ ውስጥ ሱባዔ ጀመረ እንዴ ሳንባባልም አልቀረም) የሚገርመው ነገር እኛ ጓደኞቹ ተሰብስበን እርሱን ለመጠየቅ የምንወስደውን ምግብ እኛው እየበላነው ነበር የምናስታምመው።

አንድ ቀን ግን ሁላችንም ሰብሰብ ብለን እስቲ ይሄን ልጅ እናጫውተው ብለን ቤቱ ስንገባ ያለወትሮው ሙዚቃ ጣሪያ ድረስ ከፍቶ እየሰማ ደረስንበት። ሙዚቃው የክብር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ሲሆን፤ እንደወዳጃችን ስሜት ከፍና ዝቅ የሚል መንፈስ አለው።

ፍቅርሽ ነው የጐዳኝ (3x)

በልቼ እንዳልበላሁ

ጠጥቼ እንዳልጠጣሁ

ያረገኝ ፍቅርሽ ነው

መች አጣሁ፣ መች አጣሁ

ከሰው ተራ አውጥቶ ያረገኝ ብቸኛ

አውቃለሁ ፍቅርሽ ነው ይሄ መዘዘኛ (2x)

እውነትም ፍቅሯ ጐድቶታል። … እናም የወዳጅ አንጀታችን አላስችል ቢለን እንዲያው ምግብ እንኳን እሺ የሚልበት መድሐኒት ቢገኝለት ብለን እያጣደፍን ሐኪም ዘንድ ወሰድነው። ፍቅር ያጐሳቆለው ወዳጃችን ግን “መስሏችሁ ነው እንጂ እኔ እኮ አልታመምኩም እርሷን ሳገኝ በሽታዬ ይለቀኛል” ቢለንም አንሰማህም ብለን በአቅራቢያችን ወደሚገኝ ከፍተኛ ክሊኒክ ይዘነው ሄድን።…. (ያው እንደሚታወቀው ከፍተኛ ክሊኒኮች አዲስ አበባ ውስጥ ዝቅተኛ ሕክምናና ከፍተኛ ወጪን እንደሚያዘወትሩ ይታወቃል)

ታሪክ ሰሪና ታሪክ መዝጋቢ አይተጣጡም የተባለ ይመስል በፍቅር እንክት ስብርብር ያለ ወዳጃችን ወደሐኪሙ ቢሮ ደግፌው እንድገባ ዕጣ ወጣልኝ (እንዲህ አይነት አጋጣሚ ሳገኝ እጣ ወጣልኝ እንጂ እጣ ወጣብኝ አይባል ነገር)

የተመራንበት የሐኪም ቢሮ በር ላይ ስንደርስ ተረኛዋ ዶክተር ሴት ነበረች። አንኳኩተን ወደውስጥ ከመዝለቃችን “ጠላታችሁ ክው ይበል!” ወዳጄ ክው አለ። ግራ ገባኝ፤ ገብተን እኔ ስቀመጥ ወዳጄ ግን ቆሞ ቀረ። እንደመውጣትም ቃጥቶት እንደነበር ትዝ ይለኛል። ይሄኔ ወጣቷ ዶክተር ፈገግ እንደማለት ብላ “ማነው የታመመው?” አለች። (“የጉድ ሀገር ገንፎ እያደር ይፋጃል” ይሉት የአበው ተረት ትዝ አለኝ። እስቲ አሁን ከእኔና ከወዳጄ የታመመውን መለየት ይከብዳል በናታችሁ?.... ነው ወይስ ዶክተር አሽሙር መናገሯ ነው? ለነገሩ እዚህ ሀገር ከፍቅር ይልቅ ኑሮ ያከሳን ሰዎች እንበዛለን ቂ.ቂ.ቂ… ኸረ ይደብራል አለኩ በልቤ)

“እርሱን ነው ያመመው።” ድምፄን ከፍ አድርጌ በመናገር ጤነኝነቴን ያረጋገጥኩ መሰለኝ። ወዳጄ በሽታው ሌላ ሳይሆን አይቀርም እንደወባ ሁሉ ያንዘረዝረው ጀመር። እናም ሲደናበር ከመቀመጡ በፊት በዶክተሯ ትይዩ ካለው ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠ የፎቶ “ፍሬም” ገለበጠ።….. ዶክተሯ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት መሆኗን በፍሬሙ ውስጥ በታጠረው ፎቶ አረጋገጥኩ። በማስከተልም የጋብቻ ቀለበቷ ይህንኑ አፀናልኝ።

“እንዴት ነው የሚያደርግህ? ምን ይሰማሃል?” ዶክተሯ ማዳመጫውን ወዳጄ ደረት ላይ ለጥፋ ምርመራዋን ስትጀምር፤ የወዳጄ ልሳን ግን ምንም አይናገርም ነበር። “ምኔን ነበር ያመመኝ” ሲል የሰማሁት መሰለኝ። (ህመሙን መርሳቱ በጣም ገረመኝ) ወጣቷ ዶክተር ወደኔ አየት ስታደርግ፣ “ዶክተርዬ ሰንበትበት ብሎበታል። የምግብም ሆነ የመጠጥ ፍላጐት እንደዳይኖሰር ከጠፋበት ሊገኝ አልቻለም። በሽታውስ….” ብዬ ልቀጥል ስዘጋጅ። ተዳክሟል ያልኩት ወዳጄ፣ “ዶክተር እኔ የምፈልገው “አፒታይዘር” ብቻ ነው። ሌላው ሌላው ቀላል ነው” ሲል መለሰላት።

ምርመራውን አጠናቀን፣ መድሐኒት ተፅፎልን ከዶክተሯ ክፍል ስንገባ ተደግፎ የነበረው ወዳጃችን ጭራሽ ጥሎን በፍጥነት መራመድ ጀመረ። ዶክተሯ ስትደባብሰው ሳይፈወስ አልቀረም ተባባልን። ታዲያ ያን ዕለት አመሻሽ ላይ መጠጥ ቤት በጃንቦ ተከቦ አገኘነው። ምነው? ብንለው “አዲዮስ ፍቅር” እያለ በላይ - በላይ ይጠጣ ነበር። (የኋላ-ኋላ ነገሩ ሲጣራ ለካንስ ወጣቷ ዶክተር ወዳጃችንን በፍቅር መንገድ ላይ የዘረረችው የዓይን ረሃቡ ነበረች። ያን ዕለት ትዳር እንዳላት ካረጋገጠ በኋላ ግን ሊተዋት ወስኖ - ውሳኔ ግሮሰሪን እንደ ስነ-ልቦና አማካሪ ቢሮ ደጋግሞ መጐብኘት ጀመረ።)…. እናም ወዳጃችን ለመጠጡ አሸዋ ሆነበት። ታዲያ አንድ ጃንቦውን በአንድ ትንፋሽ ፉት ማለት ምን ይሉታል?

ታዲያ አንድ ቀን አጠጣጡ ያላማረው አንድ ወዳጃችን፣ “ለምንድነው እንደዚህ አብዝተህ የምትጠጣው፤ በኋላ እኮ ከልብህ የተረፈው ጤንነትህ ለጉበትህ ሰበብ ሊሆን ይችላል። ደግሞም መጠጥ ለጥያቄህ ሁሉ መልስ አይሆንም” ሲለው ወዳጃችን ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው? “እርግጥ ነው መጠጥ መልስ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን መጠጥ ጥያቄዬን ያስረሳኛል” ብሎላችሁ እርፍ። ቂ.. ቂ.. ቂ.. ይህቺ ናት ጨዋታ ማለት ይሄኔ ነው።

እኔ የምለው መልስ ላጣንለት የመብራት ጥያቄያችን፣ የመኖሪያ ቤት ጥያቄያችን፣ የውሃ ጥያቄያችን፣ የመንገድ ጥያቄያችን፣ የትራንስፖርት ጥያቄያችን፣ የዴሞክራሲ ጥያቄያችን ሁሉ የሚያስረሳ መጠጥ ይኖር ይሆን እንዴ? ለዚህ ይሆን’ንዴ በጥቂት ዓመታት ጊዜያት ውስጥ በቢራ ራሳችንን የመቻላችን ሚስጢር?! አውራው ፓርቲ እንደውም በቀጣዩ አምስት ዓመት መስራት ካለበት ነገር ሁሉ ጥያቄያችን ላይ ሳይሆን ጥያቄያችንን የሚያስረሳ ነገር ላይ ቢሆን ምን ይለዋል? ቂ.ቂ.ቂ… ቸር እንሰንብት።    

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
1004 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 934 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us