“ደንበኛ ካልቀበጠ. . .”

Wednesday, 28 October 2015 13:44

 

እኔ የምለው በሆነ ባልሆነው እንደሞላለት ሰው በቅብጠት የሚያስቸግረን ሰውና ተቋም በዛ እኮ ምን ተገኝቶ ነው?. . . መቅበጥን በተመለከተ የሀገራችን ሰው ምን ሲል ይተርታል መሰላችሁ፤ “የቀበጡ ዕለት ሞት አይገኝም”. . . እናላችሁ ዘንድሮ እንዲህ የሚቀብጥ በበዛበት የታክሲ ውስጥ ጥቅስ መለጠፍ አይከፋም። “ደንበኛ ካልቀበጠ ንጉስ ነው” ቂ-ቂ-ቂ-! (እንዴት ነው ይህቺ ነገር መልሳችንን [መብታችንን] ስለመጠየቃችን) በአሽሙር የምትካተት አይደለችም አይደል ወዳጆቼ?)

እናላችሁ ደንበኛ ካልቀበጠ ንጉስ ነው ይሉት ፈሊጥ በብዙ ነገራችን መካከል መግባት ያለበት ይመስለኛል። ተከባብረን፣ ተፈቃቅረንና ተፈቃቅደን በጋራ ለመኖር አንዳችን በአንዳችን ላይ አለመቅበጡ ሳያስፈልገን አልቀረም። ዘንድሮ ግን ማን ያልቀበጠ አለ። ቴሌ ይቀብጥብናል፤ (በራሳችን ሳንቲምና በማያስተማምን ኔትዎርኩ እንደጉድ ይቀልድብናል). . . መብራት ኃይል ይቀብጥብናል፤ (ጠዋት እያበራ ማታ ላይ እያጠፋ፤ ሲለው እቃችንን እያቃጠለ ሲለው ጨጓራችንን እየላጠ ይቀብጥብናል።) . . . ውሃ እንደጉድ ይቀብጥብናል። (የውሃ ነገርማ “ውሃን ቢወቅጡት እንቦጭ” ይሉትን ተረት አስተርቶን ቀብጦብን ከጠፋ ሰነባብቷል።) በመሬት ጉዳይ የሚቀብጥብን፣ በኮንዶሚኒየም ጉዳይ የሚቀብጥብን፣ በሚያከራየው ቤት የሚቀብጥብን ሁሉ ወየውለት፤ . . . ደንበኛ እስካልቀበጠ ጊዜ ብቻ ነው ንጉስ የሚባለው ይሉት ጥቅስ ያልገባው ወየውለት።

እኛማ ተቃጠሉ ሲለን ደንበኛ በማይከበርበት ስፍራ ጥሎን፣ “ቋንጣና ባለሟል ሳያር አይቀርምን” እያስተረተን አለን። . . . መብታችንን ስንጠይቅ፤ ይሄ ነገር ይገባናል ስንል፤ ኧረ ይሄ ነገር ልክ አይደለም ይቅር ብለን ስንመከር ደግሞ “ንጉስ” አድርገን የሾምናቸው አስተዳዳሪዎቻችን፣ መሪዎቻችን፣ የስራ ሂደት ባለቤቶቻችን ሁሉ “ቅብጠት” ያሳዩናል። እናም ድምጻችንን ከፍ አድርገን እንጠቅሳለን፤ “ደንበኛ እስካልቀበጠ ድረስ ንጉስ ነው” (ይህ ማለት ምንድነው? የቀበጠ ዕለት ግን ወዮወለት እንደማለት አይመስላችሁም?)

በአንድ አገር ስንኖር፤ በአንድ መንደር ስንኖር፣ በአንድ ሰፈር ስንኖር በአንድ ቤት ውስጥ ስንኖር እንደነገሰ ደንበኛ ተከባብረንና ተሳስበን እንኖር ዘንድ ግድ ነው። አልያ ግን ክብራችን ላይ ቅብጠት ከደፋንበት ነገር ይበላሽና አለቃና ሎሌው ይደበላለቃል። ያኔ ነገሮች መልካቸው ይቀየራል። እዚህች‘ጋ አንዲት ጨዋታ እናምጣና ወጋችንን እንጠቅልል።

ዳይሬክተሩ አዲስ ተሾሞ ወደ ትምህርት ቤቱ ከመምጣቱ እንዲህ ሆነ። ትምህርት ቤቱ በአስቸጋሪ ተማሪዎች የተሞላ በመሆኑ ከመጣበት ኃላፊነቶች አንዱና ዋነኛው የትምህርት ቤቱን ተማሪዎች ስርዓት ማስያዝና ብልሹ ስሙን መቀየር ነበር። እናም ገና በመጀመሪያው ቀን ከመምህሩ ቢሮ አቅራቢያ ያለ ክፍል ውስጥ የበረከተ ጩኸት ተሰማ።

ዳይሬክተሩ በፍጥነት ጩኸት የበዛበትን ክፍል በር በርግዶ ከመግባቱ ለሌሎች ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ ቅጣቱ መጀመር ያለበት ከትልቁ ተማሪ ነው በሚል እሳቤ፤ እየለፈለፈ የመሰለውን ትልቅ ልጅ እየጎተተ ይዞት ወጣ። እናም ወደቢሮው ወስዶ፤ “ስማ ይሄ የተከበረ ትምህርት ቤት እንጂ የረባሾች መሰብሰቢያ አይደለም። ለምንድነው ክፍሉን የምትበጠብጠው?” ሲል በቁጣ ተሞልቶ ጥያቄውን ከመጀመሩ፤ ፊት ለፊቱ የቆመው ወጣት ሳቅ ተናነቀው። በዚህ ጊዜ አንድ ወጣት ተማሪ ቢሮውን አንኳኩቶ ገባና። “ኧረ ክፍለ ጊዜው ከማለቁ በፊት የጀመርነውን አሪፍ ትምህርት እንጨርሰው ዘንድ መምህራችንን ይመልስልን” ብሎላችሁ እርፍ። ለካንስ ርዕሰ-መምህሩ ረባሽ ነው ብሎ ጎትቶ ያስወጣው ወጣት መምህር ነበር። ቂ-ቂ-ቂ ይህቺ ናት ጨዋታ አትሉልኝም?

አያችሁ አንዳንዴ እንዲህም መደበላለቅ ሊፈጠር ይችላል። ለማንኛውም በመብራት ያነገስናቸው፣ በቴሌ ያነገስናቸው፣ ለውሃ ያነገስናቸው፣ በትራንስፖርት ያነገስናቸው፣ በመኖሪያ ቤት ግንባታ ዘርፍ ያነገስናቸው ተቋማት ሁሉ “ደንበኛ ንጉስ የሚሆነው እስካልቀበጠ ጊዜ ብቻ እንደሆነ ቢገባቸው” ምን ይመስላችኋል?. . . እናም የአንቲገንን ቃል ተውሰን እንደሚከተለው እንመክራለን። “ንጉስነት እንጀራችሁ ነው” . . . እንጀራችሁን ብቻ እየበላችሁ ከሰራችሁ ያለውን ምስኪን ህዝብ የረሳችሁት ዕለት ወየውላችሁ፤ ምክንያቱም ንግስናችሁ እስካልቀበጣችሁ ብቻ የሚቆይ ነውና። ቸር እንሰንብት!!!n

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
1162 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 930 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us