አጥፊ እና ቀጣፊ

Wednesday, 04 November 2015 14:07

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ?! . . . አባቶች የሚሏት አንዲት ሸጋ ተረት አለች። “ሰው እከትበታለሁ ብለህ ጉድጓድ አርቀህ አትቆፍር፤ ምክንያቱም ማን እንደሚገባበት አይታወቅምና” . . . እንደሰነፍ ሰው ናቂ፣ እንደሞኝ ሰው ሳቂ ካልሆንን በስተቀር ይህቺን አነጋገር በዋዛ አናልፋትም። ዘንድሮ መንገዳችንን ቆፋሪው፤ መብራታችንን ደግሞ ደጋግሞ አጥፊው የበረከተ አይመስላችሁም? እኛማ ይህውና “አሳሳች ከላይ ሲሉት ከታች” እየሆነብን ማንን ይዘን፣ ማንን ጨብጠን እንደምንናገር ሁሉ ግራ ገብቶናል።

የተጀመረን መንገድ ጉድጓድ ሳይዘጋ፤ ለኤሌክትሪክ ዝርጋታ የተከፈተ ጉድጓድ ሳይዘጋ፤ ለውሃ መስመር ዝርጋታ የተከፈተው ጉድጓድ ሳይዘጋ እኛ እስክንገባበት ነው እንዴ የሚጠበቀው? በዚህ ላይ የከተማችንን ነገር ልብ ብላችሁ ከታዘባችሁት ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች ሁሉ እኛ ላይ አብረው የተነሱ እኮ ነው የሚመስላችሁ። ለምን? አላችሁ. . . እስቲ ተመልከቱ ቀን -ቀን ቴሌ ወይም መንገዶች ባለስልጣን ቆፍረው ክፍቱን ትተውት የሄዱትን መንገድ ማታ ላይ መብራት ኃይል መብራት አጥፍቶብን ገደል እንድንገባ ያደርገናል። ታዲያ ከዚህ በላይ የቀጣዩን አምስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት ተቀናጅቶ መስራትን ከየት ይምጣ? (ቂ-ቂ-ቂ!. . . ይህቺ ናት ጨዋታ ማለት ይሄኔ ነው። አጥፊና ቀጣፊ ጠምደው ይዘውናል እኮ ጎበዝ)

እናላችሁ ይሁን እያልን ያለፍነው ነገር ሁሉ እንደሞኝነት እየተቆጠረብን ባለጌ የያዘው ከበሮ ይመስል ማንም አመታት እንኳን ሳያውቅበት በሆነ ባልሆነ አንዴ በጭለማው፣ አንዴ በውሃ ጥሙ፣ አንዴ በኔትዎርኩ፣ አንዴ ደግሞ በመብራቱ ስም ይደልቀን ይዟል።

መብራት ኃይል መብራት አጥፊ ሆኖ፤ ቴሌና ውሃ ልማት መንገድ ቆፋሪ ሆነው እኛን ሊቀብሩን የቆረጡ ይመስል የከተማችን አንዳንድ አካባቢዎች ነገር በጣም አስተዛዛቢ ሆኗል። . . . በዕድገት ተፈትልካለች፣ በዘመናዊነት መጥቃለች፣ በኑሮ ምቹነት ናጣለች የተባለላት አዲስ አበባ ይህውና አጥፊና ቀጣፊ ብቻ የሚርመሰመሱባት መስላላችኋለች።

በተስፋ በተሞሉ ቃላት፣ በመድረክ ጭብጨባ በታጀቡ ዲስኩሮች፣ በእቅድና በቁጥር ሪፖርት ከተሞላ የስራ አካሄድ ሁሉ እግራችንን ከስብራት አይናችንንም ከጨለማ፣ ሰውነታችንን ከውሃ ጥማት ይሰውርልን ዘንድ ቃል የሚገባ ብቻ ሳይሆን ሰርቶ የሚያሳይ ተቋም እንዲኖረን ዘወትር ተግተን እንፀልያለን። (እዚህች’ጋ የፀሎት ነገር ከተነሳ አይቀር ከገጣሚ ቴዎድሮ ፀጋዬ “ነፍሰጡር ስንኞች” የግጥም መድብል ውስጥ “የአትክልተኛው ማሳልይ” የተሰኘውን ስራ እነሆ)

አፍርቻለሁና

በዛ ያለችግኝ፣

እባክህ አምላክ ሆይ

አንዷን “አፅድቅልኝ”. . .

እኛም እንላለን ፅድቁ እንኳን ቀርቶባቸው በቅጡ ይኮነኑ ዘንድ ባለስልጣን መስሪያ ቤቶቹን አምላክ ሆይ ልብ ስጣቸው። እናም እንዳቸውን እንኳን አፅድቅልን።

የመንገድ ቆፋሪና የመብራት አጥፊ ነገር በብዙ ጉዳያችን መካከል አይጠፋም። ትዳራችንን ለማጥፋት በተንኮል የሚቆፍሩ እንዳሉ ሁሉ፤ ስራችንን ለማበላሸት እንደሚቆፍሩ እንዳሉ ሁሉ፤ መንገዳችንን ለማበላሸት የሚቆፍሩ እንዳሉ ሁሉ፤ ተስፋችንን ለማጨለም በተንኮል እንደሚታትሩ ሁሉ አንድዬ በአክናፉ ከክፉ ሁሉ የምንጠበቅበትንና የምናመልጥበትን መላ አይንሳን አቦ።

እነሆ ለተቋማቱ ባለስልጣናት እንዲህ እንላለን፤ ግድ የላችሁም ጉድጓዱን አርቃችሁ አትቆፍሩት፤ መብራቱንም አዘውትራችሁ አታጥፉት እኛ የእናንተ እንደሆንን ሁሉ እናተም ልክ እንደኛ የምትሆኑበት ጊዜ ይመጣልና እንተዛዘባለን። . . . እዚህች’ጋ አንድ ወዳጄ የጠቀሳትን የቅዱስ መፅሐፍ ምክር እነሆ፤ “ሰውም ጉድጓድ ቢከፍት፣ ወይም ጉድጓድ ቢቆፍር ባይከድነውም፤ በሬም ወይም አህያ ቢወድቅ፤ የጉድጓዱ ባለቤት ዋጋቸውን ለባለቤታቸው ይከፈላል፤ የሞተውም ለእርሱ ይሁን” ይላል።

እናላችሁ አንድዬ ብቻ ከአጥፊዎችና ከቀጣፊዎች ይሰውረን እንጂ፤ ቀን ጉድጓድ እየማሱ፣ ማታ እኛን በጨለማ በሚያተራምሱ ተቋማት መካከል ተከስተን ጉዳችን አይሏል። አካሉ የሚጎድልበት፤ ነፍሱን የሚያጣ ዜጋ በዝቷልና ነግ በኔ የገባው ሰው ልብ ይበል። በመጨረሻም ወዳጄ ሆይ ጉድጓዱን አርቀህ አትቆፍረው ማን እንደሚገባበት አይታወቅምና፤ ቸር እንሰንብት!!!n

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
957 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1053 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us