ጦሳችን ይስረቅ!!!

Wednesday, 11 November 2015 13:29

 

ወዳጆቼ እንደምን ሰነበታችሁ?!. . . እኔ የምለው ጊዜያችንን ከሚሰረቅ፤ ብራችን ከሚሰረቅ፣ ዕድሜያችን ከሚሰረቅ፣ ሞባይላችን ከሚሰረቅ፣ ኑሮአችን ከሚሰረቅ ምናለበት ጦሳችን ቢሰረቅ ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ?. . . ለዛሬ ትዝብት አዘል ጨዋታችንን ለማሰናዳት ስነሳ ያነበብኳትን ምርጥ ታሪክ በመተረክ ይሁን።

በእጅጉ የሚዋደዱ ፍቅረኛሞች ነበሩ። ከተጋቡ አስር ዓመታቸው በመሆኑ ሚስት ባሏን በድንገቴ ደስታ (Surprise) ለማስፈንጠዝ ታስብና መላ ትዘይዳለች። ቤት ያፈራውን አዘጋጅታ፣ ወይንና አበባ አሰናድታ ምሽቱን በሻማ ብርሃን በተንቆጠቆጠ ድባብ ልትቀበለው ትሰናዳለች።

ቀኑን በሙሉ ባሏን ለማስደሰት ቀና ደፋ ስትል ውላ ሁሉ ሙሉ፤ ሁሉ ዝግጁ በሆነበት ሰዓት የበሩን ደወል በመጠባበቅ ላይ ሳለች የቤቱ ስልክ አቃጨለ። ስልኩን ፈጥና አነሳችው። የማታወቀው ሰው ድምጽ የባለቤቷን ስም ጠርቶ የእርሱ ቤት መሆኑን ጠየቃት። ስልኩም የቤቱ፤ እርሷም ባለቤቱ እንደሆነች ለጠያቂው ሰው አረጋገጠችለት። በዚህ ጊዜ ሰውዬው የሚከተለውን መናገር ጀመረ፣ “በጣም አዝናለሁ እመቤቴ! እኔ የምደውልልሽ ከፖሊስ ጣቢያ ነው። ባለቤትሽ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በፍጥነት የመኪና መንገድ ሲያቋርጥ አደጋ ደርሶበት ህይወቱ አልፏል። ምንም እንኳን አደጋው ማንነቱን ለመለየት አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ፊቱን ያበላሸው ቢሆንም ከኪሱ ውስጥ ባገኘነው የኪስ ቦርሳው መታወቂያ ላይ የቤቱን ስልክ ቁጥር አግኝተን ነው የደወልንልሽ። አዝናለሁ እመቤቴ!” የደወለው ፖሊስ የባለቤቷ አስክሬን የት ሆስፒታል እንደሚገኝ ነግሯት ስልኩ ተዘጋ።

ፍዝዝ፣ ድንግዝ እንዳለች፣ ስልኩ ከእጇ ተንሸራቶ ሲወድቅ አልታወቃትም ነበር። ያሳለፉት መከራ፤ ያሳለፉት መልካም ጊዜ፣ ያጣጣሙት ፍቅርና የተጓዙበት የህይወት ውጣውረድ ሁሉ በአይነ ህሊናዋ በቅፅበት ተመላለሱ። እናም አይኖቿ በእንባ እንደተሞሉ የፍቅረኛዋን (የባለቤቷን) ሞት ማመን እንደተሳናት ደርቃ ቀረች።

ድንገት ግን የቤቱ በር ሲንኳኳ ከገባችበት ጥልቅ ሀዘን ጎትቶ አወጣት። በሩ ደጋግሞ ሲደወል እየተጎተተች ሄዳ ከፈተችው። ያየችውን ማመን አቃታት፣ በመኪና አደጋ ሞተ የተባለው ባሏ በፈገግታ እንደተሞላ በሩ ላይ ቆሟል። በእጁ አንዲት ዘለላ አበባን እንደያዘ ነው። ድንገት ከዓይኗ ወፋፍራም የእንባ ዘለላዎች ዱብ- ዱብ ማለታቸውን የተመለከተው ፍቅረኛዋ፣ “ይቅርታ ውዴ የጋብቻ 10ኛ ዓመታችንን ስናከብር፤ የምትወጂውን ወይን ይዤልሽ ልመጣ አስቤ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ቀን ላይ የኪስ ቦርሳዬን በመሰረቄ ምክንያት ገንዘብ አልነበረኝምና አልቻልኩም” አላት። ለካንስ ሞተ የተባለው ሰው የኪስ ቦርሳውን የሰረቀው ኪስ አውላቂ ነበር። እናም በረጅሙ ተንፍሳ ተጠመጠመችበት። የሆነውን ነገር ስትነግረው ባል ምን ቢል ጥሩ ነው? “ብራችንን ሳይሆን ጦሳችንን ሰርቋልና ነፍሱን ይማረው!!!” ቂ-ቂ-ቂ ይህቺ ናት ጨዋታ ማለት ይሄኔ ነው ጎበዝ!

እናላችሁ ድምጻችን ከፍ አድርገን “ጦሳችን ይሰረቅ!” እናላለን። ቀልባችን ከሚሰረቅና ቀለባችን ከሚያልቅ ጦሳችን ቢሰረቅ እንመርጣን። ድምጻችን ከሚሰረቅ፣ ሃሳባችን ከሚሰረቅ፣ የሞላነው ካርድ ከሚሰረቅ፣ አለን ብለን የተማንበት ነገር ሁሉ ከሚሰረቅ ምን አለበት አንዳንዴ እንኳን ሰራቂዎቻችን ጦሳችንን ቢሰርቁን የምታሰኝ ወግ አይደለችም?

ያኔ ጦሳችንን ሰርቀው በእጃቸው ይዘውት ምን ያህል እንማቅቅና እንሸማቀቅ እንደነበር ያውቁት ይሆናል። አልያም ቦርሳ እንዲሰረቀው “ሌባ” ድፍት ብለው ይታዩ ይሆናል።. . . እኔ የምለው ከሰሞኑ ጠቅላያችን ስለ ደላሎችና ስለኔቶርክ በነገር ጠቅ- ጠቅ ያደረጓት ነገር አልተመቻችሁም?. . . እንደው የምር- የምር ከሆነ እኮ ስንት ለውጥ አምጪ ተአምሮችን በቅርቡ እናይ ነበር። ለማንኛውም የጠቅላያችንና የጠቅላላ ተስብሳቢዎችን ነገር ልብ ብዬ ስታዘበው “ከጥበብ ሁለት” መፅሐፍ ውስጥ አንዲት በመካከለኛ ምስራቅ አካባቢ የተደረገች ተረክ ትዝ አለችኝ። እነሆ፡-

. . . ባህሉል የቱንም ያህል በጥበብ ቢበስል በዚሁ ምክንያት በሚደርስበት አደጋ በመፍራት ጥበቡን በእብደት መጋረጃ ሸፍኖታል። ስለዚህም ለማንኛውም ሰው ያልተፈቀደውን “ጥበብን በአደባባይ የመናገር ዕድል” እሱ በዚያች መጋረጃ ተከልሎ ሲተነፍሳት ኖሯል። አንድ ቀን ባህሉል ወደቤተመንግስቱ አደራሽ ሳይታይ ገብቶ በንጉሱ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ተያዘ። በንጉሱ ዙፋን ከመቀመጥ በላይ ወንጀል በሌለባት የዚያ ሀገር ባህሉልን የያዙት የንጉሱ ወታደሮች፤ ቆዳው እስኪገለበጥ ይተለትሉት ጀመር። የባህሉልን ጩኸትና ለቅሶ ከሌላው አዳራሽ ሆኖ የሰማው ንጉስም ሲሮጥ ይመጣና ባህሉልን አስጥሎ ጥፋቱን ይጠይቅ ጀመር። “ንጉስ ሆይ! በዙፋንህ ላይ ተቀምጦ አገኘነው” አሉ ወታደሮቹ።

በዚህ ጊዜ ንጉስ አዝኖ ባህሉልን እያባበለ ወደ ወታደሮቹ ዞረ፣ “እናንተ እብዶች! ባህሉል እብድ መሆኑን እንኳን አታውቁም? ጤነኛ ሰው በእኔ ዙፋን ላይ ሲቀመጥ አይታችሁ ታውቃላችሁ?” በማለት አፈጠጠባቸው። ይህን ጊዜ ባህሉል፣ “ንጉስ ሆይ! ወታደሮችህን አትቆጣ። እኔን ያስለቀሰኝ የእነሱ ግርፋት አይደለም። ነገሩ ሌላ ነው. . . “አለው።

ንጉሱም ግራ ተጋብቶና ወደባህሉልም በአግራሞት እየተመለከተ “ያስለቀሰህ ሌላ ምክንያት ታድያ ምን ይሆን?” አለው። ባህሉልም፣ “ንጉስ ሆይ! እኔ አንድ ቀን ለተቀመጥኩበት ዙፋን ይህን ያህል ግርፋት ከደረሰብኝ አንተ ሃያ ዓመት ከተቀመጥህ በኋላ የሚደርስብህ መከራ ትዝ ብሎኝ ነው ያለቀስኩት. . .” አለው። ንጉስ ሀሩን ለዓመታት ያላየውን ዕውነት እብዱ ባህሉል አሳየው። በቤተመንግስቱም አስተማሪ አድርጎ ሾመው. . . ሲል ድንቅ ታሪክ ይተርክልናል።

እኛም እንላለን ሰርቃችሁ እንኳን ቢሆን ስቃያችንን ታዩ ዘንድ እንጋብዝለን። የተቀመጣችሁበት ዙፋን የሚያስገርፋችሁ እንደሆነ ተግታችሁ ትሰሩበትም ዘንድ እንመኛለን። “ለአደገኛ ቦዘኔዎች” ደግሞ መልዕክት አለን፤ ቢቻላችሁ የሚስኪን ሰው ቦርሳ፣ የምስኪን ሰው ላብ፣ የምስኪን ሰው እምነትና የምስኪን ሰው ተስፋን ከመስረቅ በተጨማሪ አንዳንዴም ቢሆን ጦሳችንን እንድትሰርቁ ይሁን- አሜን!!! . . . ቸር እንሰንብት።n  

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
912 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1033 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us