የድርቅ ግርዶሽ

Wednesday, 18 November 2015 14:11

 

እንደምን ሰንብታችኋል ወዳጆቼ?. . . መቼም የሰሞኑ መነጋገሪችን ሁሉ የ8 ሚሊዮን ህዝብ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ መጋለጥ የ25 ሚሊዮን ብር የጡረተኛ ባለስልጣናት መኖሪያ ቤት ጉዳይ ሆኗል። እኔ የምለው እንድዬ ግን ምን አጥፍተን ነው “ላይኞቹ” በቀበጡ እኛን እንዲህ የሚቀጣን? ይህን ሳሰላስል

ገጣሚ ታለጌታ ይመር “ማን ነበር መሪውን?” በሚል ርዕስ ካሳተመው የግጥም ስብስብ ውስጥ “ግርዶሽ” የተሰኘው ግጥም ሀሳብ ብልጭ አለችልኝ።

እያነባሁ ስስቅ -ቆዝሜ ስቦርቅ

ተርቤ ስጠግብ - እያወቅሁ ሳላውቅ

የቤቴ ገመና እንዳይታይ ውስጡ

የጋረድኩት ግርዶሽ ጠፍቶኝ መላ ቅጡ

ችግሬን ተረድቶ ሰው እንዳያዝንልኝ

የኔው መጋረጃ እኔኑ ጋረደኝ።

“ቅንድብ ለአይን አይታይም” እንዲሉ ሆኖብን ለእኛ የድርቅና የርሃቡ ወሬ ተጋርዶብን እነቢቢስ፣ አልጀዚራና ሌሎች ዓለምአቀፍ የዜና አውታሮች ጉዳችንን አደባባይ ዘሩልንም አይደል?. . . እሰይ እውነቴን እኮ ነው።  ምን ያህል ወገን እንደተራበና በድርቁ እንደተጎዳ ሳናውቅ “ጆሮ ለባለቤቱ” ሆኖብን ከምንቀር ሁሉን ማወቃችን አይከፋም። ደግሞም ህመሙን ያላወቀ ሰው መድሃኒቱን ሊያገኝ አይችልም ተብሎ የለ?. . . ግርም የሚለኝ ግን ኢቢሲ የርሃቡን ወሬ ረብ የለሽ ማድረጉ አስተዛዛቢ እንደሆነ አደራ ንገሩልኝ። (ኢቢሲን የመረጃ ግርዶሽ እንበለው ይሆን እንዴ ጎበዝ?)

እናላችሁ የድርቁ ምክንያት መንግሥታችን እንደሚለው ኤሊኒኖ የተሰኘ የአየር ለውጥ ነው። አንዳንድ ወዳጆቼ ግን ይሄ ነገር ለኛ ብቻ ነው እንዴ የመጣው? ምነው ጎረቤቶቻችን በኛ ደረጃ አልተጋለጡም? የአስራ አንድ በመቶ እንድገታችን ይህቺን እንኳን መጋረድ እንዴት አቃተው? ሲሉ ይጠይቃሉ። (እኔ ግን በቅንፍ አንድ ስጋት አለኝ፤ ይሄ ኤልኒኖ የሚሉት ነገር ከግንቦት 7 እና ከኦነግ አሸባሪ ቡድኖች ጋር ተመሳጥሮ ከኤርትራ መንግሥትም ተልዕኮ ተቀብሎ ድንበራችንን አልፎ የደፈረን ይሆን እንዴ? ግድ የላችሁም መጠርጠር ደግ ነው፤ ይጣራልን) . . . ቂ-ቂ-ቂ ወደው አይስቁ አሉ!

ይህ የሰሞኑ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ አይነት የርሃብ ፖለቲካ፤ መንግሥት ራሱን ለመከላከል የሚዘረዝራቸው ጉዳዮችና ተቃዋሚዎች መንግሥትን ለማሳጣት የሚዘረዝሯቸው ምክንያቶች ይገርማሉ። ጎበዝ!. . . ወገን በምግብ እጥረትና በውሃ ጥም እየተኮማተረ፤ ቀን እየቆጠረ ባለበት በዚህ ወቅት የቡድኖች ፖለተካዊ አሰጥ-አገባ በጣም አስተዛዛቢ ነው። እዚህች ጋር የክፋ ቀንን የምታሳይ አንዲት ተረት እንጠርቃለን።

በድሮ ጊዜ ነው አሉ፤ እንዲህ እንደአሁኑ ክፉ ቀን መጣና ፍጥረታት ሁሉ የሚልሱት የሚቀምሱት አጡ። ክፉ ቀኑ በመጣበት ወቅት እንዲህ እንደኛ ምክንያቱ ባለመታወቁ ሁሉም በየፊናው የድርቁን ምክንያት ለማውቅ ይጥር ነበር።

ታዲያ ከዕለታት አንድ ቀን አንበሳ፣ ነብር፣ ጅብና አህያ ክፉ ቀን የመጣበትን ምክንያት ለማወቅ ይወያዩ ጀመር። በመጨረሻ ግን ከመካከላቸው አንዱ ኃጢያት በመስራቱ ይሆናል ብለው ስለገመቱ እያንዳንዳቸው የሰሩትን ሃጢያት ሊናዘዙና ሃጢያት ሰርቶ የተገኘም ሊፈረድበት ተስማሙ።

በመጀመሪያ አንበሳ ተነሳና “አንድ ቀን አንዲት መሲና ላም ከበረት ወጥታ ስላገኘኋት በልቻታለሁ። ይህ ሃጢያት ከሆነ ፍረዱብኝ” አለ። እነሱም አንበሳን ሲመለከቱት ግርማው እጅግ የሚያስፈራ ስለነበር “መሲና እበረት ውስጥ መተኛት ሲገባት በረት ሰብራ መውጣቷ የራሷ ጥፋት እንጂ የእርስዎ አይደለም” አሉት። ነብር ደግሞ በፈንታው ተነስቶ፤ “አንድ ቀን ምግቤን ፍለጋ ጫካ ስዘዋወር አንድ የፍየል ጠቦት ከእረኞች አምልጦ እጫካ ውስጥ ቅጠል ሲቀነጥስ አግኝቼ እርሱን በልቻለሁ። ሃጢያት ከሆነ ፍረዱብኝ” አለ። እነአንበሳ “ጥፋተኛው ከእረኞች አምልጦ ጫካ የገባው እንጂ አንተ አይደለህም” አሉት።

ለጥቆ ደግሞ ጅብ ሃጢያቱን እንዲህ ሲል ተናዘዘ። “አንድ ሌሊት ምግቤን ፍለጋ መንደር ለመንደር ስዘዋወር አንዲት በግ እቤት ውስጥ እጋጥ ሆኖ ነገር ግን ላቷን በቀዳዳ ወደውጭ አውጥታ አግኝቼ ቆርጬ በልቻለሁ። ሃጢያት ከሆነ ፍረዱብኝ” አለ። የተቀሩት እንስሳትም  “ጥፋቱ ላቷን እውጪ ያሳደረችው በግ እንጂ ያንተ ስላልሆነ ልንፈርድብህ አይቻለንም” አሉት፡

በመጨረሻም አህያ ሃጢያቷን ለመናገር ተነሳችና፣ “አንድ ቀን ጌታዬ አንድ አቆማዳ እህል ጭኖኝ ወደገበያ ስሄድ መንገድ ላይ ዘመድ አጋጥሞት ቆሞ ሲያወራ እኔ ደግሞ ወደመንገድ ዳር ሄጄ ሳር ነጭቼ በልቻለሁ። ይህ ሃጢያት ከሆነ ፍረዱብኝ” አለች። እነአንበሳም አህያን “በእኛና በወገኖቻችን ላይ ይህን ሁሉ መዓት ያመጣሽ አንቺ ነሽ። ምክንያቱም ጌታሽ ከዘመዱ ጋር ሲያወራ ቆመሽ መጠበቅ ሲገባሽ ሳር መንጨትሽ ከፍተኛ ሃጢያት ነው” ብለው፤ ገድለውና ስጋዋን ተከፋፍለው በሏት ይባላል።

ፖለቲካዊ ምክንያትና መከራከሪያ እየፈለጉ በወገን ርሃብ ላይ ከመመላለስና ፍርድ ገምድል ከመሆን ቅድሚያ ለሚሰጠው ነገር ሁሉ ቅድሚያ ብንሰጥ ሳይሻል አይቀርም።. . . በድህነታችን፣ በማጣታችን፣ መኖሪያ ቤት አልባ በመሆናችን በመጠማታችንና ከመራባችን ላይ ጉንጭ አልፋ ክርክርና በፖለቲካዊ ጨዋታ ከመጠመድ ይልቅ ልብ የሚሞላ ስራን ብንሰራ ከትዝብት እንተርፋለን። አልያ ግን የድርቅ ከበርቴዎች ይመስል፤ በወገን ችግርና ችጋር ላይ የቃላት ወርወራን ቁም ነገር ማድረግ ግፍ ነው።

በክፉ ቀናችን አየሁሽ አላየሁሽ የሚያሰኝ የቁጥር ጨዋታን ትተን፤ በርሃብ የተጠቃ ወገናችንን የጦስ ዶሮ ከማድረግ ርቀን፤ ሁላችንም በጋራ እንረባረብ ዘንድ ነገር ሁሉ ለሁላችን ግልፅ ይሁን። እድገትና ልማድ ብቻ ሳይሆን፤ ርሃብና እጦታችንም በግልፅ ይነገር፤ የመረጃ ግርዶሹ ይቀደድ፤ ያኔ ለወገን ደራሽ ወገን መሆኑን እናስመሰክራለን።. . . ቸር እንሰንብት።

   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
740 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 922 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us