ከምንፈልገው ይልቅ የሚያስፈልገን

Wednesday, 25 November 2015 15:01

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!? . . . ጠይቀን ያልተመለሰልን፤ ጠብቀን የቀረብን፤ አስበን ያልሆነልን ነገር መቼም ብዙ ነው። ያኔ ታዲያ ተስፋችን ስልምልም ሲል ወደፈረደበት አንድዬ አንጋጠን ብቻ እንደሚከተለው መቀኘት (መመቅኘት ነው አላልኩም) ነው።

ሳታድለኝ ቀረህ እጅ -እጅህን ሳይ

እኔስ ብሆን ያንተው አይደለሁም ወይ?

አንዳንዴ ሳስበው ግን እንድዬም ራሱ በእኛ ነገር ግር ሳይሰኝ አይቀርም። እንደው ማስጀመሪያ እርሾ ነገር እንኳን ሳንይዝ ቶሎ ሆድ እየባሰን ሙሾ የምናወርድ በርክተናል እኮ!. . . የምንፈልገው ነገር ያለው ሌላ ቦታ የምናስበው ሌላ ቦታ፤ ውሃ አጣጫችን ያለችው ሀገር ቤት እኛ የምንዳክረው ደግሞ ጎረቤት፤ ዕውቀት የሚገኘው ትምህርት ቤት እኛ የምንገኘው ደግሞ አዋቂ ቤት እየሆነ ነገራችን ሁሉ አስተዛዛቢ ሆኗል።

የምሬን እኮ ነው ነገራችን ሁሉ “ላም ባልዋለበት” እየሆነ ልፋታችን ሁሉ ድካም ብቻ ሆኗል ፍሬው።. . . እዚህች’ጋ ከሰሞኑ የታዘብኳትን ነገር ላጫውታችሁ። ከመንደራችን አለፍ ብሎ የተቀመጡ ሁለት የቆሻሻ ገንዳዎች መካከል ዘወትር የሚለምኑ “የኔ-ብጤ” አሉ። ታዲያ ስለሁኔታቸው ሳጣራ፤ አንድ ወጣት ልጅ እግር እያመጣ እዛ ቦታ አስቀምጧቸው ነው የሚሄደው።. . . ዳሩ ግን የቀን ገበያቸው እንደቀነሰ ሲያማርሩ በመስማቴ ቀረብ አልኩና “ምነው አባቴ!” አልኳቸው።

“እንጃልኝ ልጄ! ሰው መስጠት አቆመ መሰለኝ ጠብ የሚል ነገር የለም” አሉኝ። ሰውየው ደካማ ከመሆናቸው ባሻገር አይነ-ስውርም በመሆናቸው አካባቢያቸውን እንዳላስተዋሉት ጠረጠርኩ። “አባባ ቦታው እኮ የቆሻሻ ገንዳዎች ያሉበት ነው። በዚህ ላይ ቆሻሻው ስለማያስጠጋ ሰው እርስዎ በተቀመጡበት በኩል ሳይሆን በሌላኛው አቅጣጫ ነው የሚመላለሰው” ብላቸው ጊዜ ምን አሉኝ መሠላችሁ። “አይ የኔ ነገር? ልጄ እኔ እኮ የማሽተት ችግር አለብኝ። አፍንጫዬ ከጥቅም ውጪ ነው። ለዛነው ምንም ሳይመስለኝ ቀኑን ሙሉ የምቀመጠው” ይህን ብለውኝ፤ ሲያበቁ ወደሌላ ቦታ እንድወስዳቸው ተማፀኑኝ። እንዳሉትም ቦታ ቀይረው “እናንተ እምታዩኝ፣ እኔ የማላያችሁ!” የሚል የዘወትር መማፀኛቸውን አስከትሎ ጥሩ ገቢ አገኙ።

በቀጣዩ ቀን ወደስራ ሳልፍ ያለኝን መፅውቼ፤ እንደምን አደሩ አባት ከማለቴ የምርቃት መአት ዘነበብኝ። ለካንስ በቆሻሻ ገንዳዎቹ መካከል በቆዩባቸው ቀናት ሽታው ስለማይሸታቸው እንጂ ገበያቸው መቀነሱን አውቀውታል። አሁን ግን ትክክለኛ ቦታ በመቀመጣቸው ለነፍሱ የሚያድር መፅዋች አላጡም።

እናም አንድ ነገር ታዘብኩ፤ እንደው ባልሆነ ቦታ ተገኝተን ያልሆነ ነገር ከምንጠይቅ፤ ያልሆነ ቦታ ተቀምጠን የማይሆን ነገር ከመጠበቅ የትነው ያለሁት?. . . ማንን ነው ያገኘሁት?. . . ማንን ምንድነውና እንዴት ነው የጠየኩት ማለቱ ያዋጣል። አለበለዚያ ግን “ምነው ሰው ሁሉ ንፉግ ሆነ” እያሉ ወደአንድዬ አቤቱታ ማብዛቱ ተገቢ አይደለም።

ሳታድለኝ ቀረህ እጅ እጅህን ሳይ

እኔስ ብሆን ያንተው አይደለሁም ወይ?

እስቲ ደግሞ ከመሰነባበታችን በፊት “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማን” ከሚያስታውሱ የሙላህ ነስሩዲን ወጎች መካከል አንዱን ጀባ ልበላችሁ።. . . ሙላህ ነስሩዲን በምሽት የወርቅ የጣት ቀለበቱ ጠፍቶበት ተደናግጧል። እናም ከቤቱ ፊት ለፊት ከተገተረው የመብራት ቋሚ ስር ፍለጋውን በማጧጧፍ ላይ ሳለ፤ አንድ ያካባቢው ሰው መጥቶ፣ “ነስሩዲን ምን እየፈለክ ነው?” ሲል ይጠይቀዋል። ነስሩዲንም፣ “ባክህ ከመሸ የጣት ቀለበቴ ጠፋኝ እርሱን ፍለጋ ላይ ነኝ” ከማለቱ ሰውዬው ፍለጋውን ተቀላቀለው።

ከቆይታም በኋላ አንድ ሁለት የሙላህ ነስሩዲን ጎረቤቶች በመንገድ ሲያልፉ ሁኔታውን ጠይቀው በመረዳት ቀለበት ፍለጋውን ተያያዙት። ከሶስቱ ሰዎች አንዱ ግን ፍለጋው ውጤት አልባ ቢሆንበት ጊዜ፣ “ስማ ነስሩዲን በርግጥ ቀለበትህን እዚህ ቦታ ነው የጣልከው?” ሲል ጠየቀ። ያገኘው መልስ ግን፣ “ነገሩማ ቀለበቴ የጠፋብኝ ቤቴ ውስጥ ነው” አለ። ከሶስቱ ሰዎች አንድ በጣም ተገርሞ፣ “ታዲያ ቀለበትህ ቤትህ ውስጥ ከጠፋ ስለምን እዚህ ደጅ ታስፈልገናለህ?” ሲል ይጠይቀዋል። ሙላህ ነስሩዲንም ሲመልስ፤ “ቤቱ ውስጥ መብራት ባለመኖሩ ዝም ብዬ ከመቀመጥ ብዬ  ነው፤ ከመንገዱ መብራ ስር በመፈለግ ላይ የምገኘው” ብሎላችሁ እርፍ፤ ቂ-ቂ-ቂ-! ይህቺ ናት ጨዋታ ማለት ይሄኔ ነው።

እናላችሁ “ማሞ ሌላ ሆነ መታወቂያው ሌላ” አይነት ፍለጋና ጥያቄ ግኝትም ሆነ መልስ የለውምና አንልፋ። ምን እንምንፈልግ እንወቅ፤ የት እንደሚገኝ እንወቅ፤ እንዴትና ማን እንደሚያገኝልን ወይም እንደሚረዳን እንወቅ። ያኔ ነገር ሁሉ ልክ ይመጣል። እናም አንድዬ የምንፈልገውን ሁሉ ከሚሰጠን፤ የሚያስፈልገንን ቢሰጠን ምን ይለናል። ለኛም ቢሆን ከምንፈልገው ይልቅ የሚያስፈልገን ይበልጥብናል። ቸር እንሰንብት።n  

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
868 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 924 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us