እነሆ ትዝብቴ

Wednesday, 02 December 2015 14:45

 

 

 

እንዴት ሰነበታችሁ ወዳጆቼ። ለዛሬ በዕለት ተእለት ኑሮ ስንባዝን ከምናስተውላቸው ነገሮች ለቅምሻ ያህል ሁለት ወጎችን እነሆ።

 

***          ***          ***

ይድረስ የኑሮ ውድነት ላነተበህ፣ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ከሰውነት ተራ ላወጣህ ምሁሩ ወዳጄ!... ያቺ ከልደታ ባዕታ የማታደርስህን ገቢ ለመሸሸህ ከግማሽ እድሜህ በላይ ቆርሰህ እስከፒ.ኤ.ቺ.ዲ ዲግሪ ድረስ ተማርክ፤ ለፋህ፣ ደከምክ። እነሆ ተምረህ ስታበቃ የደመወዝህ ስኬል እንደአሮጌ የባቡር ፉርጎ እየተጎተተ 6 ሺ ብር ላይ ቆመ። ከዚህ ላይ መንግስት 35 በመቶ ታክስ ሲያነሳለት፣ የጡረታ፣ የአባይ ግድብ መዋጮ ሲቀነጫጨብለት.. ከዚያም ከዚህም የቃረምካቸው የቅሌት መዝገቦች (ብድሮች) ሲወራረዱ…ጠላትህ ክው ይበል ክው የሚያደርግ ፍራንክ ይዘህ ወደሚስትና ልጆችህ ትነጉዳለህ። አማኝ ነህና ለዚህም ተመስገን ትላለህ…“ተመስገን፤ ይህንንም አታሳጣኝ! ..ይህንንም ያጡ ብዙዎች አሉና አንተ በቸርነትህ ጎብኛቸው… አስባቸው!” እያልክ ነግቶ በመሸ ቁጥር ለብቻህ ታጉተመትማለህ።..

 

ጮሌዎቹ ባልንጀሮችህ “መንገዱን እወቅበት!” እያሉ ጠዋት ማታ ይጎተጉቱሃል። እነሱን እያቸው!... መንግስትን ደመወዝ ጨምርልኝ ከማለት ይልቅ “ይህ ልማታዊ መንግስታችን ባዶ ካዝና ነው የተረከበው፤ የገቢያችን ማነስ ድህነታችን የፈጠረው ችግር ነው! …ችግሩ በልማታዊ መንግስታችን ጥረት ይፈታል! …” በማለት በየመለኪያ ቤቶች ጭምር ዲስኩራቸውን እየነፉ፤ ግን ቀብረር …ሞልቀቅ ያለ ኑሮአቸውን ያጣጥማሉ። ከየት አምጥተው ይመስልሃል ወዳጄ?! ...ዕድሜ ለልማታዊ መንግስታችን!.. የአንተን ኪስ በጥሩ ደመወዝ መሙላት ቢያቅተውም፤ የሁነኛ ወጃጆቹን ቀዳዳ በርሜል ለመሙላት ግን ላቡን መዝራት አልተሳነውም። ለአንተና ለመሰሎችህ ግን በየቴሌቪዥኑ መስኮት፣ በየስብሰባ አዳራሹ ቋቅ እስኪልህ ድረስ “ዋንኛው ጠላታችን ኪራይ ሰብሳቢነት ነው!” ሲል ዲስኩሩን ይግታቹሃል። አንተም ምስኪኑ …አንዳንዴ የሰማኸው ሁሉ እውነት እየመሰለህ ይህንኑ በየሄድክበት እንደበቀቀን ስትደግም ትውላለህ፤ “ዋንኛው ጠላታችን ኪራይ ሰብሳቢነት ነው! ...ኪራይ ሰብሳቢነት የሥርዓቱ አደጋ ነውና በተባበረ ክንድ እናጥፋው! .....ተረረረም ..ተረረም …”

 

ያ አብሮ አደግህ ዶ/ር እንቶኔ 6 ሺ ብር የማትሞላ ወርሃዊ ደመወዝ ይዞ ግራውንድ ፕላስ ዋን ቤት ሰርቷል። ልጆቹን ለንደን፣ አሜሪካ ልኮ ዶላር እየመነዘረ ያስተምራል። ያኛው (ስሙን ቄስ ይጥራውና!)... ከካድሬው በላይ ካድሬ ነኝ የሚለው….፤ መሽቶ በነጋ ቁጥር በፓርቲው እየማለና እየተገዘተ ራሱን ወደንዑስ ከበርቴ መደብ ከፍ ካደረገ ሰንብቷል። አንተ ግን በፈሪሃ እግዚአብሄር ተሞልተህ… ባዶ ኪስህን…ባዶ ሆድህን …ባዶ ቤትህን ይዘህ ትናውዛለህ። ለልጆችህ ወርሃዊ ክፍያ አጥተህ ስንቱን ስትቧጥጥ እንደምትኖር የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው። …ደግሞ ይህቺ ባዶነትህ ውስጥ የተሰካች ኩራትህ አናትህ ላይ ወጥታ ስትጨፍር ወግ ነውና ኮራ..ጀነን ትላለህ። ሰው እናድርግህ! ያሉህን “ልማታዊያን” እየሸሸህ …እየሸሸህ፤ እነሆ በማትሸሸው ድህነት ማጥ ውስጥ ቦክተህ ….ሐሩር እንደመታው ቄጤማ ከነቤተሰብህ ጠውልገህ ትኖራለህ። ደሃ ነህ! …ገና ጠግበህ መብላት የምትመኝ ነህ! …እናም በስርቆት ከደረጁት ጋር ተሰልፈህ ዛሬም ባልበላ አንጀትህ “ዋንኛው ጠላታችን ኪራይ ሰብሳቢነት ነው!” እያልክ ትዘምራለህ። ሌላው መንገድ ያንተ አይደለምና ምን ምርጫ አለህ? ንጹህነትህን የሚጠየፉ ሌቦችን ከማጀብ ውጪስ ምን ተስፋ አለህ? ...ግን ይህ ጽዱ ኢትዮጵያዊ ንጽህናህ! ...ደግነትህ! …ጨዋነትህ! የት ድረስ ያዘልቅህ ይሆን? ...እንጃ?! ....አንድዬ ይታደግህ አቦ!...

 

***          ***          ***

 

እነሆ ትዝብቴ 2

አንድ ጓደኛዬ ሚዲያዎቻችንን የታዘበበት መንገድ እነሆ ሌላ ትዝብትን አስታውሶኝ ላካፍላችሁ ተነሳሳሁ።

 

አብነት 1

ስለቀድሞ ጠ/ሚኒስትራችን ራዕይ አውርቶ የማይጠግበው ኢቲቪ/ራዲዮ እየደጋገመ “የጠ/ሚኒስትሩ ሞት በሕዝቡ ዘንድ የፈጠረው መነቃቃት…” በሚል ወጉን ለማሳመር ሲሞክር ምን እያለ እንደሆነ እንኳን አለማወቁ ሲበዛ ያስገርማል። አባባሉን ልብ በሉ! ...ሕዝቡ እንዲነቃቃ ጠ/ሚኒስትሩ መሞት አለባቸው እያለን ነው።

 

አብነት 2

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደመፈክር የሚነገርለት አንድ አባባል እንደዋዛ ጆሮአችን እየደረሰ ነው። “ትልቅ ነበርን፤ ትልቅም እንሆናለን” የምትል። አባባሏ ተፈልቅቃ ስትታይ በአሁን ሰዓት “ትንሽ ነን” የሚል ውስጠ ወይራ ትርጉም አላት። እናም ሚዲያው ጮክ ብሎ “ትንሽ ነን!” ሲል እያወጀ ነው። ወይ ቅሌት!

 

አብነት 3

ሚዲያዎቻችን ደጋግመው “ ሲወርድ ሲዋረድ…” ሲሉ ይደመጣሉ፣ ይነበባሉ። ነገሩ “ሲወርድ ሲወራረድ..” ለማለት ተፈልጎ ነበር፤ ግን ቃሉ ያለቦታው በመሰካቱ ትርጉሙም የሚያዋርድ ሆነና አረፈው።

 

አብነት 4

ብዙ ዜናዎች መቋጫ ዓረፍተ ነገራቸው “አስምረውበታል” በሚል አባባል ይታሰራል።ማስመር ግን ምንድነው? የእንግሊዝኛውን ጥሬ ትርጉም አማርኛችን ውስጥ በመሸንቆሩ ትርጉም አልባ ቃል ተፈጠረ፤ጋዜጠኞቻችንም የቃሉን ትርጉምና ምንነት ሳይጨነቁ ነጋ ጠባ “አስምረውበታል” ይሉናል።

 

አብነት 5

አሁን አሁን በብዛት እየሰረገች ከመጡ አዳዲስ ቃላት መካከል “ውሃ የማይቋጥር…” የምትለዋ ትገኛለች። ለምሳሌ “ይህ ኀሳብ ውሃ አይቋጥርም” ሲባል ቢሰሙ ምን ትርጉም ይሰጥዎታል። ለእኔ ምንም!¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
831 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 864 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us