ሰብዓዊነት ምነው ጠፋሳ?!

Wednesday, 09 December 2015 13:58

 

እንዴት ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?....... አገር አማን ነው? አቤት!... ይህ የፌስ ቡክ ፍልሚያ እንዴት ተጋግሏል ጃል?! ፍልሚያው የተጧጧፈው የኦሮሞ ተማሪዎች ተጎዱ፣ ሞቱ በሚሉ ተቆርቋሪ ነን ባዮችና በአብዮታዊ ዴሞክራቱ መንግስታችን «ደጋፊዎች» መካከል መሆኑ እርግጥ ነው። የጠቡ መነሾ የፈረደበት የአዲስአበባና የኦሮሚያ ክልል የጋራ ማስተር ፕላን ነው። ፕላኑ ገና መሬት ሳይወርድ የኦሮሞ ወጣቶችን ደም ማራጨቱን ተያይዞታል። እኔ የምለው ግን ሀገሪቷ ሳይተርፋት ተበድራ አስለቃሽ ጢስና… ምናምን ገዝታለች ሲባል “እሰይ ሰለጠንን!” ብለን ጮቤም ረግጠን አልነበር? ያ የተገዛው አድማ መበተኛ ወዴት ይሆን ያለው? ሥራ ላይስ የሚውለው መቼ ይሆን? በእንቶኔ አካባቢ ሰላማዊ ሰልፍ ተወጣ ተብሎ ተነግሮ ሳያበቃ እነእገሌ ሞቱ፣ ቆሰሉ የሚል የመርዶ ዜና እንደዋዛ ይከተላል። ወላጅ አንጀቱን ቋጥሮ ለዓመታት ያሳደገው ልጅ በእንዲህ መልኩ ሲነጠቅ ለሰሚው ግራ ነው። አሁን አሁንማ ሞቱ አዲስነቱ ቀርቶብን ቁጥሩ ያወዛግበን ጀምሯል። የሟቹ ቁጥር አንድ ነው፣ የለም 10 ነው፣ 20፣ 30 ነው….ጨዋታ ውስጥ ተገብቶ እያየን፣ እየሰማን ነው። እኔ የምለው ግን… አንድ ስውስ ለምን ይሞታል? አድማ ለመበተን መተኮስ፣ ምን መተኮስ ብቻ መግደል ሕጋዊ ያደረገው ማነው? እውን እነዚህ ሕጻናት ተማሪዎች ላይ ቃታ እንዲሳብ የፈቀዱ፣ ቃታም የሳቡ ሰዎች ቤተሰብ፣ ልጆች አላቸውን? ይህ ክስተት በእነሱ ቤተሰብ ላይ ቢከሰት ምን ይሉን ይሆን? መቼም አንድ ሰው፣ ገና ለገና ተቃውሞ አሰማ ብሎ ቃታ መሳብ ምን የሚሉት ስልጣኔ ይሆን? የሚያሳዝነው…እጅግ በጣም የሚያሳዝነው ሁሉም ነገር አላፊ መሆኑ መረሳቱ ነው። ወደድንም ጠላንም… በጊዜው፣ በወቅቱ፣ በሰዓቱ….. ማናችንም ብንሆን እንደምግባራችን በሰፈርንበት ቁና የመሰፈራችን ሐቅ እንደምን ይረሳል?

አቤ ጉበኛ ሞትን (ዘላለማዊ አለመሆንን) የሚያንቆለጻጽሰው ወዶም አይደል!

“ሞት መኖሩ በጀን እንኳንም ሞት አልቀረ

ሁልጊዜ ይመስገን ሞትን የፈጠረ

ከእውነት ጋር ጠፍቶ ሞትማ ካልኖረ

ስንት ታምር፣ ስንት ገድል ካሁን የባሰ አመጽ

በዚህች ቀልማዳ ዓለም በታየ ነበረ”

አብዮታዊያኑ፤ “የጸረ ሰላም ኃይሎች… አሸባሪዎች…” እያሉ የሚጠሩዋቸው መቀመጫቸውን በአውሮፓና አሜሪካ ያደረጉ ተቃዋሚዎች በኦሮሚያ እንደተከሰተው እንደሰሞኑ ዓይነት ግጭት ጮማ መብያቸው ነችና ያለልክ ሲጮሁ ለጉድ ነው። እነሱን አዘውትሮ የተከታተለ በአዲስአበባ ጎዳናዎች ላይ በሰላም ወጥቶ ስለመግባቱ እርግጠኛ አይሆንም። በቃ! አውሮፓ ተቀምጦ «በለው!» እያሉ እንደፌስ ቡክ ያሉ ማህበራዊ ድረገጾችን ሲያጨናንቁ፣ ሲፎክሩ፣ ሲያቅራሩ ይውላሉ። ጥላቻ ይዘራሉ፣ ጥላቻ ያጭዳሉ።

አብዮታዊያኑን የተጠጉት (በተለይም አድርባዮቹና ሌቦቹ) በተገላቢጦሽ ያው ናቸው። ከአንድ ባህር የሚቀዱ፣ ከእኔ ጋር ካልሆንክ ከእነዚያ ጋር ነህ ባዮች ናቸው። ገና በ20ዎቹ መጀመሪያ የሚገኙ ታዳጊዎች ሰልፍ ወጥተው በደንብ ባልገባቸው ነገር ስለጮሁ ምላሹ ጥይት መሆኑ ትንሽም እንኳን አይቆረቁራቸውም። ለዚህም ነው፤ መንግስትን ለማንቆለጻጸስ ቃላት ከድቶአቸው የሚታዩት። ማሰብ፣ ማገናዘብ፣ ግራና ቀኝ ማየት፣ መንግስትም ሲያጠፋ ተገቢውን ሒስ መስጠት የሚባሉ ነገሮች እነሱ ሰፈር አይታወቁም። እነሱ ሰፈር የአድርባዮች ዋሻ ይበዛል። ብዙዎቹ መንግስታችን ወይንም ገዥያችን ሲያስነጥስ አብረው ያስነጥሳሉ፣ ፈጥነውም መሀረብ ያቀብላሉ። ጉያው ውስጥ ተወሽቀው እያመሰገኑና በሱ ስም እየማሉ በዚያው ፍጥነት 360 ዲግሪ ተሽከርክረው አሁንም በልማታዊ መንግስታችን ሰም ይሰርቃሉ፣ ሕግና ስርዓትን ይጥሳሉ፣ ፍትሕ ያዛባሉ። እነዚህኛዎቹ ብልጣብልጦች ብቻም ሳይሆኑ ደጋፊ መሳይ ገፍታሪዎች  የሚበዙበት ጎራ ነው። “ሁሉ ፈረስ ላይ ከወጣ ማን ገደል ያሳያል” የሚለው ብሂል የተመዘዘው ለእነዚህኛዎቹ አድርባዮች ሳይሆን አይቀርም። ለምን ቢሉ ገደል የሚያሳይ ከመካከላቸው የለማ!.....ስለዚህ ጉዳይ ሳወራ “ጌታን የሰቀሉት አመሰጋኞቹ ናቸው” የሚል አንድ ያነበብኩት ወግ ትዝ አለኝ። አንድ አሰልጣኝ ቡድኑ ሻምፒዮን በመሆኑ ድል ባለ ድግስ ተወድሶ መኪና ሲሸለም የተመለከተ አንድ ጋዜጠኛ ለአሰልጣኙ ቃለመጠይቅ ያደርግለታል። ጋዜጠኛው አሰልጣኙን ‘እንዲህ ተወድሰህ ስትሸለም ምን ተሰማህ?’ የሚል ጥያቄ ያቀርብለታል። አሰልጣኙ ‘ምንም’ የሚል አጭር መልስ ይሰጣል። ጋዜጠኛው በመልሱ ተገርሞ ‘ለምን’ ሲል መልሶ ይጠይቀዋል። አሰልጣኙ ‘ጌታን የሰቀሉት አመስጋኞቹ ናቸው። ዛሬ ውጤት በማግኘቴ የተሸከመኝ ሕዝብ ነገ ውጤት ሲጠፋ በድንጋይ ይወግረኛል፣ የገማ ዕንቁላል ያፈርጥብኛል። እኔ የማስበው ስለዛሬ ደስታ ሳይሆን ስለነገ መከራዬ ነው’ የሚል መልስ ሰጠ። የብዙዎቻችን ችግርም የነገን መከራ አሻግረን ማየት አለመቻላችን፣ በዛሬ አላፊ የምቾት ስካር ውስጥ መስጠማችን ነው። አቦ!... ሁላችንንም ከነገ መከራ ይሰውረን። አሜን!...አትሉም እንዴ?... የከርሞ ሰው ይበለን!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
834 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 82 guests and no members online

Archive

« July 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
            1
2 3 4 5 6 7 8
9 10 11 12 13 14 15
16 17 18 19 20 21 22
23 24 25 26 27 28 29
30 31          

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us