“መርፌ ሰርቆ ማረሻ. . .”

Wednesday, 16 December 2015 13:43

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!? . . . እኔ የምለው ያገራችን ሰው “ከነገሩ አነጋገሩ” የሚላትነገር እኮ ድንቅ ናት። እውነቴን ነው፤ አሁን እስቲ ማን ይሙት “ነገሩ ነው እንጂ ጩቤ ሰው አይጎዳም” ማለትን የመሰለ አባባል አለ?. . . እናላችሁ ነገራችን እና አነጋገራችን ድንቅ ቢለኝ ጊዜ “እንደባቢሎኖች” ከተሰኘው የታምራት መቻል የሥነ-ግጥም ስብስቦች መካከል “መርዝና መድሃኒት” የተሰኘውን ግጥም እነሆ ማለት ወደድኩ፤

እውነቱን በመንገር፤ ህመሙን ቢያክመው

መድሃኒቱ ሳለ ከመርዝ ቆጠረው

ወይ አለማስተዋል፤ “ልክነህ” ስላለው

“መድሃኒቴ” ይላል፤ መርዝ ሆኖ ሲገድለው።

                        (ገፅ÷23)

እናላችሁ ስንት መድሃኒት ይሆናል ያልነው ነገር ከነገራችን ይሁን ከአነጋገራችን ወደመርዝ እየተቀየረብን እርስ በእርስ አጠማመዶ ይዞናል። የምሬን እኮ ነው፤ ቢቻል በውል፤ በወግና በማዕረግ ነገር ሁሉ ቢደረግ በጣም ሸጋ አይመስላችሁም። ባልና ሚስት፤ አሰሪና ሰራተኛ፤ ሹፌርና ረዳት፤ እግረኛና ባለመኪና፤ መሪና ተመሪ፤ መምህርና ተማሪ፤ ከሳሽና ተከሳሽ፤ አሳዳሪና አስተዳዳሪ፣ መሪና ተመሪ፤ ህዝብና መንግስት ሁሉ በህግና በወግ ተግባብቶ ቢኖር፤ ሁሉም በወጉና በማዕረጉ ከሕግ በታች ቢውል ምን አለበት?. . . ወዳጄ የአገራችን ሰው ምን ይላል መሰለህ? በውል ከሄደችው በቅሎዬ፣ ይልቅ ያለውል የሄደችው ቆሎዬ ታንገበግበኛለች” እውነት አይደል?

ለክፉም ለደጉም በመነጋገርና በመግባባት ላይ የታሰረ ውል መያዙ አይከፋም። አልያ ግን መግቢያው እንጂ መውጫው ዋጋ የሚያስከፍለን ይሆናል። ትዳሩ ያለሰላም፣ ትምህርቱ ያለውጤት፣ ስራው ያለስኬት፣ ደሞዙ ያለበረከት፣ ንግግሩ ሁሉ ያለለከት ሆኖ አመድ አፋሽ እንዲያደርገን ሕገ - መንግስት ብቻ ሳይሆን ሕገ - ሕሊናም ያስፈልገናል።

ወዳጄ ዘንድሮ ለመድሃኒት ያልነው ለመርዝ የሚመነዝርበት ነገር በርክቷል። አንድዬ ብቻ አስተዋይ ልቦናና ቀና ሃሳባችንን አበርክቶ፤ በጋራ ለማደግ እንጂ በጋራ ለመውደቅ ከመውተርተር ይሰውረን። . . . መድሃኒትነተን ወደመርዝነት የምትለዋን ሃሳብ ሳውጠነጥን አንድ ወዳጄ በፌስቡክ ገፁ ላይ “ሼር” ያደረጋት ጨዋታ ትዝ አለችኝ።፡. . . ገጠር ውስጥ ነው። ሰውዬው ጥርሱን ሊነቀል ማደንዘዣ ወደሌለው ጥርስ ሀኪም ዘንድ ይሄዳል። ታካሚው ነገሩን ሲያስበው ያለማደንዘዣ ጥርሱን ማስነቀል ይፈራል። “የቸገረ ነገር የጠፋ ለመላ” እንዲሉ በፍርሃት የሚንቀጠቀጠውን ህመምተኛ የተመለከተው ዶክተሩ መላ ይዘይዳል። “አይዞህ ምንም እንኳን ዘመናዊ ማደንዘዣ ባይኖርም ፍርሃቱ እንዲለቅህ ይህቺን ካቲካላ (አረቄ) ግጥም አድርጋት” ብሎ አንድ ጠርሙስ ፊቱ ያስቀምጥለታል። “የቸገረው እርጉዝ ያገባል” እንዲሉ ቢሆንልኝ ብሎ ህመምተኛው ካቲከላውን ገጥሞ ጨረሰው። ከደቂቃዎች በኋላ ግን ዶክተሩ፣ “እሺ እንዴት ነው ፍርሃቱ ለቀቀህ አይደል፤ አሁን ጥርስህን መንቀል እችላለሁ። ከማለቱ ታካሚው ምን ቢል ጥሩ ነው? “አዎ አሁን ፍርሃቴ ለቆኛል! እስቲ ማንአባቱ ወንድ ጥርሴን ሊነቅል ይጠጋኝና አሳየዋለሁ” ብሎላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ! ይህቺ ናት ጨዋት እንግዲህ፤ ለመድሃኒት ያልነው ለመርዝ ሲመነዘር አያችሁም አይደል?

የመተማመንና የጥርስ ህመም ነገር ከተነሳ ላይቀር አንዲት ጨዋታ ልጨምር። ሴትየዋ ጥርሳቸውን በጠና ታመው ወደሀኪም ዘንድ ይመጣሉ። የጥርስ መነቀያው ወንበር ላይ እንደተቀመጡም ቦርሳቸውን ከፍተው ገንዘባቸውን በጥንቃቄ መቁጠር ይጀምራሉ። ይሄን ጊዜ ሃኪሙ፣ “ግድ የለም እሜቴ ከተነቀሉ በኋላ ይከፍላሉ” አላቸው። ታዲያ ሴትየዋ ምን ቢመልሱ ጥሩ ነው?. . .” ያንንማ አውቃለሁ። ማደንዘዣውን ከመወጋቴ በፊት ምን ያህል ገንዘብ ይዤ እንደመጣሁ ለማወቅ ፈልጌ ነው” ብለውት እርፍ።  

እናላችሁ አንዳንዴ አምነንና ፈቅደን ካደረግነው ትልቅ ነገር ይልቅ ተገደንና ፈርተን ያደረግነው ትንሽ ነገር ብዙ ያንገበግበናል። ለዛምነው በአበው ዘንድ “መርፌ ሰርቆ ማረሻ ቢተኩ ልብ አይሞላም” የሚባለው። አንድዬ ብቻ ክፉ ነገራችንን ነቃቅሎ የልባችን በመልካም ሃሳቦች የሚሞላበትን ዘመን ያምጣልን አቦ፤ ቸር እንሰንብት።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1323 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 929 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us