የፊት እና የኋላ

Thursday, 24 December 2015 11:16

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . እህሳ ቀየው መንደሩ እንዴት ከረመ?. . . አፋሽ አጎንባሹስ. . . ወዳጆቼ አጥብቄ መጠየቄ ወድጄ አይደለም።  አበው ሲተርቱ “እባብን ያየ ቢልጥ በረየ” ይላሉ።  እኛም ከዚህ ቀደሞ ያየናት ብዙ “እባብ” ነገር ስላለች ነው መሰለኝ በሰሞኑን ነገር የተነሳ እነሆ የድሃ ልባችንን ተበራየን ሁሉ ይዛለች።  አንድዬ ብቻ ሰላሙን ያምጣልን።

ሰውዬው አገር እያቆራረጠ ንግዱን የሚያጧጡፍ ብርቱ ሰው ነበር።  ክፉ ነገር አይቶ አያውቅም።  ክፉ ነገር ሲሰማ ግን ሰነባብቷል።  በተለይም እርሱ በሚሄድበት መንገድ አካባቢ ያሉ ሰዎች ከሽፍታ ጋር በተያያዘ ብዙ የሚወራለት አንድ ሽፍታ ሀሳብ ሆኖበት ከርሟል።

ታዲያ አንድ ቀን በምሽት ይኖርበት ከነበረ የገጠር ከተማ ተነስቶ ወደሌላ ሀገር በመጓዝ ላይ ሳለ ሁለት የእጅ ባትሪ መብራት የያዙ ሰዎች በጭለማ ውስጥ ገጠሙት።  አንደኛው አይናገርም፤ አይንቀሳቀስም አንደኛው ግን ባለበት እንዲቆም ነግሮት፤ ያለውን እንዲስቀምጥ አዘው፤ ዘርፈውት ሲቢቁ ወደትልቅ ግንድ ፊቱን አዙሮ እንዲቆም በማድረግ ንቅንቅ እንዳይል አስጠንቅቀው ከበስተኋላው ተሰወሩ።  ዳሩ ግን የተጓዥ ኮቴ ቢሰማውም ከቅድም ጀምሮ ከኋላው ባትሪ ይዞ የቆመ አንድ ሽፍታ እንዳለ በብርሃኑ ተረድቶ መዞር ፈራ።  ከግማሽ ሰዓት በኋላ ይብቃህ የሚለው ሰው ቢያጣ ጊዜ “ኧረ ጎበዝ በወንድ ልጅ አምላክ ልሂድ ፍቀዱልኝ” ሲል ድምፁን ጮክ አድርጎ ተማፀነ።   ነገር ግን ምላሽ የሰጠው ሰው አልነበረም።  

ገዳይ ነው፣ ምህረት አያውቅም፣ ጨካኝ ነው ሲባል የተወራለት ሽፍታ ያለበት አካባቢ በመሆኑ ያለአንዳች ትዕዛዝ እንዳይንቀሳቀስ በተሰጠው ማስጠንቀቂያ መሠረት ዞር ማለት ዳገት ሆነበት።  ያም ሆኖ የሚያናግረውም ሆነ የሰው እንቅስቃሴ ፍፁም ሊሰማ ባለመቻሉ፤ እንዲሁም ምሽቱ እየገፋ በመሄዱ “ኧረ ወዳጆቼ የልጆች አባት ነኝ።  ጅብ ከሚበላኝ እንድሄድ ፍቀዱልኝ” ሲል ወደዛፉ ፊቱን እንዲያዞረ ጠየቀ።  የሰማውም ሆነ የመለሰለት አልነበረም።  ነገር ግን አሁንም ድረስ አንድ ሰው ከኋላው ቆሞ ባትሪ እንዳበራበት ይጠርጥራል።  በስተመጨረሻም የሞት ሞቱን ቢዞር በኋላው ምንም ፍጡር አልነበረም።  በሰው እጅ የተያዘ የመሰለው የባትሪ ብርሃን ከተንጠለጠለበት የዛፍ ቅርንጫፍ የመጣ መሆኑን ሲመለከት ሁለት የመሰለው አንድ ሽፍታ እንደቀለደበት ተገንዝቦ በሽፍታው ብልጥነትና በራሱ ሞኝነት ከት ብሎ መሳቅ ጀመረ።  

ድንገት ግን በዚያ ምሽት ብቻቸውን እየተጓዙ የነበሩ መነኩሴ የሰውዬውን ሁኔታ አይተው በማዘን ተጠጉት።  አፅናንተውና አበርትተውም አብረው መጓዝ ጀመሩ።  በጉዟቸውም ላይ ነጋዴው ስላጣው ገንዘብና ሀብት፤ ስለዘራፊዎቹ ተንኮልና ስለተሰማው ፍርሃት ሲያወራ፤ መነኩሴው በበኩላቸው፣ “ስላተረፈው ነፍስና ስለመጪው ህይወቱ፤ ስለሙሉ ጤንነቱና ስላልጎደለው አካላቱ፤ የራሳቸውን ስለሚሰጡ መልካም ሰዎችና ጻድቃን እየነገሩት ብሶቱን ረስቶና ተፅናንቶ በሰላም ወደቤቱ ገባ።  እናም በመንገዱ ያስብ የነበረው፣ ፍርሃት በብልሃት ፊት የሚጥል ስለመሆኑ ነበር።  በፍርሃት ስለጣልነው ሀብት ብቻ ከማሰብ በተስፋ ስለምናገኘው መልካም ነገር ብናስብ የፊትን ከኋላ ማጣጣም እንችል ነበር።

እናላችሁ እኛም ከድሮ ጀምሮ ከኋላችን በበራብን የፍርሃት ባትሪ አሁን ድረስ ተደፍተንና መዞር አቅቶን ስንት ነገር አጥተናል መሰላችሁ? የቀድሞ ታሪካችን “ሀንጎቨር” ሆኖብን የምንፈራው ልጅነት፣ የምንፈራው ትዳር፣ የምንፈራው መምህር፣ የምንፈራው መንገድና የምንፈራው አስተዳዳሪ ሁሉ ስንት (በክፉም ሆነ በደጉ) አስመልጠውናል መሰላችሁ።  እናላችሁ ታሪክን የኋሊት ስንል የሚመጣልንና የሚመጣብን ሁሉ አስፈሪውና “ሆረሩ” ብቻ ከሆነ ምን ዋጋ አለን።  “እባብን ያየ ቢልጥ በረየ” እንዲሉ፤ አንዴ ባየነው እባብ መነሻነት ሁሌ ብልጥ ስንርበተበት መኖርን ያህል ፈተና ከወዴት ይመጣል ወዳጆቼ?

“የሰው ልጅ ከኋላ በትዝታ ከፊት ደግሞ በተስፋ ታጅቦ ነው የሚኖረው” ያለው ሰው ማን ነበር?. . . የኋላው ታሪካችን ለፊታችን ተስፋ ያለው ተፅዕኖ (በክፉም ሆነ በደጉ) ቀላል አይደለም።  ዳሩ ግን ሚዛናዊ አስተሳሰብ ያስፈልገናል።  ቀናውንም፤ ከችግር ባሻገር ያለውንም፤ ከማጣት በኋላ የምናገኘውንም የሚያስታውሰን ታሪክ (ሰው) ያስፈልገናል።

ስለኋላ እና ስለወደፊት ነገር ሲነሳ አንዲት ጨዋታ ትዝ አለችኝ።  ሰውዬው በሚስቱ ሁኔታ በጣም የተማረረ ነው።  እናም ከጓደኛው ጋር አንዲት ግሮሰሪ ውስጥ ተገናኝተው በጭውውታቸው መካከል፤ “ለመሆኑ ሚስትህ እንዴት ናት?” ሲል ጠየቀው።  በሚስቱ እጅግ የተማረረው ሰውም፣ “ኧረ ተወኝ ድንቄም ሚስት፤ አቃጥላ ልትደፋኝ እኮ ነው” ሲል ይመልሳል።  በሁኔታው የተመሰጠው ጓደኛም “ለመሆኑ ምን ብትበድልህ ነው እንዲህ የተማረርከው” ድጋሚ ጠየቀ።  “ዘወትር ስለቀድሞ ባሏ ታሪክ እያወራች ነዝንዛ ልትገድለኝ ነው ባክህ” ሲል በምሬት ከመመለሱ ጓደኛው ምን ቢል ጥሩ ነው? “ኧረ ወዳጄ ያንተዋ ትሻላለች።  የኔዋ እኮ ስላለፈው ሳይሆን ስለ መጪው ባሏ ነው የምትነተርከኝ” ብሎላችሁ እርፍ ቂ- ቂ- ቂ- ይህቺ ናት ጨዋታ አትሉልኝም?

እናላችሁ እንደመኪና ሁሉ በህይወታችንም ውስጥ ከፊቱ መስታወት ባልተናነሰ መልኩ የኋላ መመልከቻችንም (ስፖኪዮ) ከአስፈሪና ከአስደንባሪ ነገር የፀዳ እንዲሆን እንመኛለን፤ አልያ ግን ያተረፍነውን እረስተን የከሰርነውን ብቻ ስናብሰለስል መኖር መረገም አይመስላችሁም? ቸር እንሰንብት።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
725 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 896 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us