“ደግ ጐረቤት…”

Wednesday, 30 December 2015 13:53

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?... መቼም አብረን ስንኖር ወዳጅነት ለመቼ ነው የሚያስብለን አጋጣሚ ብዙ ነው። በተለይ ጐረቤት ሆኖ ወዳጅ ከተገኘ፤ ሐዘንን የሚያቀል ደስታን የሚያበዛ ነውና መታደል ነው። ስለመልካም ጐረቤት ከተነሳ የአገራችን ሰው አዘውትሮ የሚጠቅሳት አንዲት አባባል አለች፤ “ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጐረቤት ይበልጣል” ትላለች እውነት ነው።

አንድዬ ብቻ በከፋን ጊዜ “አይዞኝ!” በተደሰትን ጊዜ ደግሞ “እሰይ!” እያለ አብሮነቱን የሚያሳየን የጐረቤት ወዳጅ አይንሳን አቦ። እኛም ለዛሬ ትዝበት አዘል ጭውውታችን “ደግ ጐረቤት፣ ያወጣል ከመዓት” ይሉትን ብሂል ራስ አድርገን የመጣነው ያለነገር አይደለም።

እስቲ ደግሞ ወጋችንን ማሳመሪያ ይሆነን ዘንድ ዋዛና ቁምነገር ከማያጣው ሙላህ ነስሩዲን ታሪክ አንዱን እንመልከት። …. በአንድ ወቅት ነስሩዲን ወደሚኖርበት ግዛት አዲስ ተሿሚ ይመጣል። ነስሩዲንም እንደመተዋወቂያም እንደ እጅ መንሻም ይሆንለት ዘንድ ወደተሿሚው ቤት ትላልቅ ድንች በከረጢት አዝሎ መንገድ ጀመረ። በመንገዱም ላይ የሙላህ ነስሩዲን ጐረቤት የሆነ ሰው፣ “ነስሩዲን ወዴት እየሄድክ ነው?” ሲል ጠየቀው። ነስሩዲንም፣ “አዲሱን አስተዳዳሪ ልተዋወቃቸውና ሹመት ያዳብር ልላቸው እየሄድኩ ነው” ሲል መለሰ።

“ለመሆኑ ምን ይዘህ ነው የምትሄደው?” የጐረቤቱ ጥያቄ ነበር።

“ቤት ያፈራውን ድንች እየወሰድኩ ነው።” የነስሩዲንን ምላሽ የሰማው ጐረቤትየው በነገሩ ተገርሞና ደንግጦ፤ “በል ወዳጄ ወደቤትህ ተመለስ። እንዴት ብለህ ነው አዲሱ አስተዳዳሪ ፊት ድንች ይዘህ የምትቀርበው ባይሆን ፍራፍሬ ወይም እንጆሪ ነው እንጂ” ሲል መክሮና አስጠንቅቆ መለሰው። እናም ወደቤት ተመልሶ ጐረቤቱ አለኝ ከሚለው የእንጆሪ ተክል የደረሰውንና ምርጥ ምርጡን ሰብስቦ ወደ አዲሱ ተሿሚ ቤት ጉዞውን ቀጠለ።

የከተማው ዋና አስተዳዳሪ ቤት ደርሶ በርካቶች አስደናቂና ውድ ስጦታዎችን በማበርከት ላይ ሳሉ፤ ሙላህ ነስሩዲንም “ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም” በሚል መንፈስ ጣፋጭ እንጆሪዎቹን በትሪ ዘርግፎ ለአዲሱ አስተዳዳሪ አሳላፊዎች አቀረበ። የነስሩዲንን ስጦታ የተመለከቱት አዲሱ አስተዳዳሪም በጣም ተናደው ባመጣው እንጆሪ ይወገር (ይደበደብ) ዘንድ ለባለሟሎቻቸው አዘዙ። በእንጆሪ ውርጅብኝ ፊቱና አናቱን የሚቀጠቅጠው ነስሩዲን ግን በሁኔታው ተገርሞ ከት-ከት ብሎ ይስቅ ነበር።

በነስሩዲን ሳቅ የተደነቁት አዲስ ተሿሚ ወገራው እንዲቆም በማዘዝ ወደእሱ ቀረቡና፣ “ለመሆኑ በእንጆሪ አየተደበደብክ ማዘን ሲገባህ ስለምን ትስቃለህ?” ሲሉ ጠየቁት። ነስሩዲንም፣ “ጌታዬ የጐረቤቴን ምክር ባልሰማ ኖሮ ይደርስብኝ የነበረውን የድንች ወገራ እያሰብኩ ነው መሳቄ” ሲል መለሰ ይባላል። ወዳጆቼ ለክፉም ለደጉም ወዳጅና መካሪ ጐረቤት አያሳጣን ማለቱ አይከፋም። (አንድዬ ብቻ የሰውነት ክብራችሁን በምትሰጡት ስጦታ ከሚለካ ሰው ይሰውራችሁ።)

ሐዘንና ደስታ በሚፈራረቅበት በዚህ ዓለም ሰው ያለ ሰው መኖር ይከብደዋል። እዚህች’ጋ አንዲት አባባል ላስታውስ፤ “ጫማ የለኝም ብለህ አትዘን እግር የሌለው ብዙ ሰው አለና።” እናም አሁን ከደረሰበን ችግር በላይ ይደርስብን የነበረውን በማሰብ መፅናናቱ አይከፋም። ወዳጃችን ሙላህ ነስሩዲንም በእንጆሪ ሲደበደብ የሳቀው በድንች ቢሆን የሚሰማውን የበለጠ ህመም ከግምት አስገብቶ ነውና ገጠመኙ ያስቃል። ይህቺን ሀሳብ የምታጐላልን ከክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል “የቅኔ ውበት” መፅሐፍ ውስጥ የሚከተሉትን ስንኞች እንካችሁ፤

ደስታና ሐዘን ውርጭና ፀሐይ

ሆነው ይመጣሉ በሰውነት ላይ

ሰው ደስ ባለው ጊዜ ሐዘኑን ይረሳል

ሐዘንም ሳያገኘው መጨነቅ ያበዛል።

አስቦ ሁለቱም አላፊ መሆኑን

ሲከፋው ደስታውን ደስ ሲለው ሐዘኑን

አስቦ በመጠን ሁሉን የወሰነ

ብልህ ሰው ይባላል የተመሰገነ።

ስለ ብልህ ሰውና ወዳጅነት ካነሳን አይቀር ደግሞ ይህቺን ጨዋታ እንካችሁ፤ “… ሁለት ጓደኛሞች በአንድ መዝናኛ ውስጥ ተቀምጠው ቢራ ይጠጣሉ። ሲጋራ አቁሜያለሁ እያለ ሲያስወራ የከረመው አንደኛው ጓደኛ ከሌላኛው ሲጋራ ይሰጠው ዘንድ ወጥሮ ያዘው። በዚህ ጊዜ ሲጋራ የተጠየቀው ሰው አውጥቶ እየሰጠው፣ “ሲጋራ አቁሜያለሁ ብለህ አልነበረም እንዴ?” በማለት ሲጠይቀው ምን ብሎ ቢመልስ ይሻላል? “አዎ! የማቆም የመጀመሪያው ደረጃ ላይ ነኝ። ይህ ማለት ደግሞ መግዛት አቁሜያለሁ ማለቴ ነው” ብሎላችሁ እርፍ ቂ… ቂ… ቂ… ይህቺ ናት ጨዋታ አትሉልኝም።”

እናላችሁ ወዳጆቼ “ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም” ብለን ያቀረብነው በረከት መዓት ሊያስከትልብን የሚችልበት ወቅት ላይ ነው ያለነው። አንድዬ ብቻ በደስታውም በሐዘኑም የማንተወውና የማይተወን ጐረቤት ይስጠን አቦ!... ያኔ “ደግ ጐረቤት፣ ያወጣል ከመዓት” ይሉትን ተረት እናጣጥመዋለን። ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
1152 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1092 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us