“በፍየል ዘመን - በግ. . .”

Friday, 08 January 2016 12:18

 

“ስበረው”

ሌላ መንገደኛ አልፎ እንዳይመጣበት

ካንተ ጋር እንዳቻ እንዳይኩራራበት

ያደጋ ምልክት ቀይ አንጠልጥልበት

ስበረው አፈንዳው አመድ አርገው ትቢያ

ምን ያደርጋል ድልድይ አንተ ካለፍክ ወዲያ?

        (ከዓምፀሐይ ወዳጆ፤ “የማታ እንጀራ” የግጥም መድብል የተወሰደ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ?. . . መልካም የገና በዓል እንዲሆንልን ተመኘሁ። አንድዬ ተወልዷል ብለን ልደቱን በምናከብርለት በዚህ የበዓል ሰሞን በጉልህ ሊታሰብ የሚገባው መንፈሳዊ አርአያነቱ ነው። እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ፤ ይቅር እንድንባባል፤ እንድንታዘዝን፤ ህብረት እንዲኖረንና ህይወት እንድናገኝ ነው አንድዬ ሰው ሆኖ ወደኛ የመጣው። እኛ ግን ክብረ-በዓሉን አጥብቀን ይዘን፤ ዋናውን መንፈሳዊ ተግባር ግን ወዲያ ጥለን የምንተዛዘብበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።

እንዲያውም ከሰሞኑ ታክሲ ግድግዳ ላይ ያነበብኳት ፅሁፍ ዘመናችንን በትክክል ትገልጻለች መሰለኝ፤ “በፍየል ዘመን -በግ አትሁን”. . . ሕዝቤ እንደአሜሪካና ሩሲያ የጎሪጥ እየተያየ በሚያስመስልበት በዚህ ዘመን “ፍየል” መሆን የግድ ሳይለን አይቀርም።

ከታክሲ ጥቅስ ስንመለስ ባስ ውስጥ የገጠመኝን ነገር ማውሳቱ ተገቢ ነው። በፍየሎች ዘመን በግ መሆን የሚያስከትለው ነገር እንዲህ ነው።

በበዓል ግር ግር መካከል ወደመርካቶ በምትወስደኝ ባስ ውስጥ ሆኜ ነው። ከመነሻው በመሳፈሬ ቦታ ላጣሁምና ተቀምጫለሁ። እናንተዬ ወንበር ለካ እንዲህ ይመቻል። (መቼ የወንበር ነገር ቅኔ እንደሆነች ለናንተ አይነገርም) እናላችሁ ከአንድ ሁለት ሶስት ፌርማታ በኋላ ሰው እየሞላ መጣ። በመሃል አንድ አዛውንት ሰውዬ አጠገቤ ቆመው ቁልቁል ገላመጡኝ (በሆዴ ሳስበው፤ አትነሳም ወይ፣ አትነሳም ወይ እሱ ወንበር የኔ አይደለም ወይ? ያሉኝ መሰለኝ ቂ.ቂ.ቂ እኔ የምለው በባቡር ውስጥ ለአቅመ ደካሞች መቀመጫ ልቀቁ የምትለው የሥነ-ምግባርና መምህርት የምትመስለው ሴትዮ ባስ ውስጥም ታስፈለገን ይሆን እንዴ?)

እናላችሁ ሰውዬው ሲገላምጡኝ የተመቸኝ ወንበር ጎረበጠኝ። ታዲያ ወዲያው በፈገግታ ተሞልቼ “አባቴ ይቀመጡ” ብዬ ከመቀመጫዬ ከመነሳቴ ምን ቢሉኝ ጥሩ ነው “አዬዬ ይህቺን አመል እናውቃታለን፤ ተቀምጠሽ አልተመቸሽም መሰል” ብለውላችሁ እርፍ፤ እኔስ ሽምቅቅ። እናንተዬ እውነቴን ነው የምላችሁ በፍየል ዘመን በግ መሆን ጣጣው ብዙ ነው።

በነገሮች ሁሉ እንደእባብ እየተያየ ካብለካብ በሆነው ባልሆነው እየተጨቃጨቅን፤ የጎሪጥ እየተያየን፤ ክፉ ሀሳብ እየጎነጎንን እርስ በእርሳችን በክፋት ከመነታረክ አንድዬ ይጠብቀን አቦ። “ከኑግ የተገኘ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ” እንዲል የአበው ተረት፤ በስንዴው መካከል እንክርዳድ እንደማይጠፋ ሁሉ፤ ከሸረኛው መካከል ቅን ልቦና ያለው እንደማይጠፋ ሁሉ፤ ከተንኮለኛው መካከል ደጋጉ እንደማይጠፋ ሁሉ፤ ከፍየሎቹም መካከል በግ አይጠፋምና መተሳሰቡ አይከፋም። (ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ እኛ ዘንድ አይደርስም ስንል ጅምላ ጨራሽ ባህሪይን ተላብሰነው ቁጭ ስንል በጣም ያሳዝናል)

በተለይ የሰሞኑ የበግ ገበያ ብዙ ፍየሎችን አሳይቶናል። እኔ የምለው ግን ገበያው እናንተ’ጋ እንዴት ነው? . . .. ወዳጄ ይቅርታ ይደረግልኝና ዘንድሮ ነጋዴና ጎራዴ ልዩነታቸው ሊገባኝ አልቻለም። እውነቴን እኮ ነው፤ የበግና የፍየል ዋጋ በራሱ የህንፃ ኪራይን የሚያክል ሲሆን ምን ይባላል?. . . የገበያ ነገር ከተነሳ አይቀር አንዲት ቆየት ያለች ጨዋታ ላስታውሳችሁ።

ሰውዬው አህያ ሊገዛ ይወጣና በገበያው መካከል ሲዟዟር አመት በዓል በመሆኑ ምክንያት በግ፣ ፍየል፣ ዶሮና በሬ በዝተው በማየቱ ለጥየቃ ወደአንደኛው ነጋዴ ጠጋ ይላል። “ለመሆኑ ይሄ በግ ስንት ነው?” ጠየቀ ሰውዬው፤ “ሶስት ሺህ ብር ናት ጌታዬ” መለሰ ነጋዴው። በዋጋው የደነገጠው ሰውዬም፤ “እንዴ በዚህ ዋጋማ አህያ አልገዛም እንዴ?”ከማለቱ ነጋዴው ምን ቢል ጥሩ ነው? “ይችላሉ ጌታዬ! የሚጥመውን እርሶ ያውቃሉ” ብሎላችሁ በነገር ጠቅ አደረጋቸው። ቂ-ቂ-ቂ ይህቺ ናት ጨዋታ ማለት ይሄኔ ነው።

እናላችሁ በዓል እና ነጋዴ በዘዴ የምንመራውን ኑሮ በዳዴ እንዲያስኬደን እያንደረደሩት በመሆኑ በዓልም ቢሆን ምነው ባልመጣ የምንለው ቀን ፤እየበረከተ ነው።

ከገበያና ከነጋዴ ነገር ሳንወጣ የምትከተለዋን ጨዋታ እንካችሁ፤ አንድ ባለሱቅና ጓደኛው እየተጨዋወቱ ነው። በመሀል ጓደኝዬው ባለሱቁን፣ “ሁሌ የሚገርመኝ ነገር አለ። ለምንድነው በሱቅህ ግድግዳ ላይ የተለጠፉት ማስታወቂያዎች ሁሉ የሰዋሰውና የፊደል ግድፈት የማይጠፋባቸው?” ሲል ይጠይቃል። ነጋዴው ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ? “ሰዎች ሞኝ ነው ብለው በማሰብ በርካሽ ጥሩ ነገር ለመግዛት እንዲመጡ ብዬ ለማሳሳት የማደርገው ነው” ብሎ እርፍ።

ወዳጄ አንድዬ ይጠብቀን እንጂ በፍየል ዘመንማ በግ መሆን የሚቻል አይደለም። ይህውና የአባይስ ነገር “ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣልን” ሊያስተርትብን አልነበር እንዴ. . . ብቻ ግብፅ ፍየል ሆኖ እኛ በግ እንዳንሆን ጠንቀቅ ማለቱ አይከፋም።  . . አንድ ነገር ግን አለ፤ ከፍየሎቹ በላይ የበግ ለምድ የለበሱቱን ፍየሎች መፍራት ነው። ባለሁለት ቢለዋዎችን፤ ባለሁለት ምላሶችን፤ ባለሁለት ራሶችን፤ ባለሁለት ስህተቶችን አንድዬ ያርቅልን አቦ፤ መልካም በዓል። ቸር እንሰንብት።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
1091 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 929 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us