“ፍቅር ሲጠና. . .”

Wednesday, 13 January 2016 14:34

 

 

እነደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . ከምኑም ከምኑም ፍቅርና ሰላሙን ያብዛልን አቦ!. . . በፍቅር ስሞ የራሱን እንጀራ የሚጋግር ሰው እንዳለ ሁሉ፤ አልፎ -አልፎም ቢሆን በፍቅር ስም ነገር የሚያሳስም ሰው አይጠፋምና አንድዬ ይጠብቀን። (እኔ የምለው የጠቅላያችን ልጅ ፍቅር ሰምሮላት ትዳር መሠረተችም አይደል? እሰይ! ተመስገን ነው መቼም ይሄ ቤተመንግስት ከተቆረቆረ ጀምሮ ደስታና መከራን፣ ትዕቢትና ውርደትን፣ አምባገነንነትንና ውድቀትን፣ በዓይነት፣ በዓይነቱ ሲያጣጥም ኖሯልና የሰሞኑ ሰርግም ቢሆን አዲስ አይሆንበትም።

እናላችሁ የትዳሩን ነገር ያሰባችሁም ካላችሁ “ሙሽሪት ለምዳለች፣ ከናቷም ካባቷም ባሏን ትመርጣለች” ይሉትን የሰርግ ዘፈን አሰደምጣችሁን ላጥ በሉ አቦ!. . . እኔ የምለው ግን ይሄ በየፌስ ቡኩ “ተጠላልፈናል፣ ተቀላቅለናል፣ “ተጋብተናል” እያላችሁ “የምትፖስቱት” እንትናዬዎች እኛን ተስፋ ለማስቆረጥ ነው ወይስ የምር ነው? የምሬን እኮ ነው ግልጽ አርጉትና ገላግሉን አቦ! (አግብቻለሁ፣ አግባ ማለት ማንን ገደለ?)

የፍቅርና የትዳር ነገር ከተነሳ አንዲት ደስ የምትለኝ የአበው ተረት ምን ትላለች መሠላችሁ? “ፍቅር ሲጠና ቆሎ ያጉራርሳል” ቂ-ቂ-ቂ ደስ አትሉም?. . . ግጣሙን አግኝቶ፤ ሶስት ጉልቻ መስርቶ እንደሚኖር ሰው የታደለ የታለ በናታችሁ?

ወዳጆቼ ቆሎ የሚያጎራርስ ፍቅር አይንሳን አቦ!. . . እንዲህ ካልሆነማ በንትርክ የሚጠፋው ጊዜና ጨጓራ ከየት ይመጣል? ይልቅዬ አንዲት በታክሲ ውስጥ ጥቅስ ትዝ አለችኝ። “የሚጠሉንን ለመጥላት ጊዜ ምክንያቱም የሚወዱንን በመውደድ ተጠምደናልና” ደስ አይልም?

የዚህ አለም ነገር በፍቅር ካልሆነ ብዙ ነገሩ ይሰለቻል እኮ።. . . ለዛሬ ትዝብት አዘል ጨዋታችንን ታደምቅልን ዘንድ አንዲት የሂንዱ ወግ እንካችሁ።. . . አንድ የሂንዱ መንፈሳዊ አባት በመንደር ውስጥ ጉብኝት በማድረግ ላይ ሳሉ ሰዎች በኃይል እና በንዴት እየተጯጯሁ ሲነጋገሩ ይታዘቡ ነበር። በኋላም ወደ ተከታዮቻቸው ሲመለሱ አንድ ጥያቄ አነሱ፤ “ስለምንድነው ሰዎች እርስበርሳቸው እየተጯጯሁ በንዴት የሚነጋገሩት?” ጥያቄውን የሰሙት ተከታታዮቻቸው ፈጣን ምላሽ ከመስጠታቸው በፊት ጥቂት ሲያብሰለስሉ ቆዩና ከመካከላቸው አንደኛው፣ በንዴት ውስጥ መረጋጋት ስለማይኖረን ጮኸን እንናገራለን” ሲል መለሰ።

“የምትጮኽበት ሰው አጠገብህ ቆሞ ስለምን በከፍተኛ ድምፅ መናገር አስፈለገ? ወይም ዝቅ ባለድምፅ ማስረዳት የምትፈልገውን ነገር መናገር አይቻልም እንዴ?” መንፈሳዊው አባት በድጋሚ ጥያቄውን ወደ ተከታዮቻቸው ሰነዘሩ።

አሁንም ተከታዮቻቸው ይሆናል ያሉን ምክንያት በመልስነት አቀረቡ። ነገር ግን የአንዳቸውም መለስ አጥጋቢ አልነበረም። በመጨረሻ ግን መንፈሳዊው አባት የሚከተለውን ምላሽ ለተከታዮቻቸው ማብራራት ጀመሩ፤ “ሁለት ሰዎች እርስበእርሳቸው ከተቆጡ ወይም ከተጣሉ የልባቸው ርቀት ይሰፋል። የልባቸውን ርቀት ለማጥበብ ሲሉ ደግሞ ጮኸው ለመናገር ይገደዳሉ። በጥላቻ፣ በንቀትና በክፋት መካከል የሚገኙ ሰዎች ሁሌም ልባቸው የተራራቀ ስለሆነ ጮኸው መናገራቸው የተለመደ ነው።” ብለው የተከታዮቻቸውን ገፅታ ሲመለከቱ ጥቂት ቆዩና ጉሮሯቸውን ጠራርገው ገለጻቸውን ቀጠሉ፤ “የተፋቀሩ ሰዎችስ? በፍቅር ውስጥ ያሉ ጥንዶች ተመልከቱ አይጮሁም ይልቅስ ቀስ ብለው በማውራት ይግባባሉ። ምክንያቱም የልብ ወዳጆች በመሆናቸውና ልባቸው አንድ በመሆኑ ነው።. . . ሰዎች ይበልጥ በተፋቀሩ ቁጥር ድምፅ አውጥተው አይነጋገሩም፤ ያንሾካሹካሉ እንጂ ለምን ቢባል? ስለሚደማመጡ። . . . ይባስ ብሎም ፍቅራቸው ሲጠና መነጋገር አቁመው በመተያየት ብቻ የሚግባቡበት ጊዜ ይመጣል። ይህ ነው እንግዲህ በጩኸትና በመረጋጋት፣ በጥላቻና በፍቅር መካከል የተሰመረው መስመር። ልባችሁ በንዴት፣ በቅናት፣ በትዕቢት፣ በተንኮልና በክፋት የተራራቀ ቀን በመካከላችሁ ያለው  የልብ ክፍተት ያለቅጥ ይሰፋና ተለያይታችሁ ትቀራላችሁ። ስለዚህ ነገሮችን ሁሉ በመደማመጥ በእርጋታና በፍቅር ለመቀየር መሞከር ጠቢብነት ነው።” መንፈሳዊው አባት ለተከታዮቻቸው ይህንን ተናግረው መንገዳቸውን ቀጠሉ።

እናላችሁ ጎበዝ “ፍቅር ጠንቶ፣ ቆሎ የሚያጎራርሰን ቀን እንዲመጣ የዘወትር ምኞታችን ነው። በሀገር ጉዳይ ስንነጋገር፤ በክልል ጉዳይ ስንነጋገር፤ በመንደር ጉዳይ ስንነጋገር፤ በሰፈር ጉዳይ ስንነጋገር፤ በፍቅር ጉዳይ ስንነጋገር፤ በትዳር ጉዳይ ስንነጋገር ዘወትር በንዴት ተሞልተን ጮክ ብለን የምንነጋገር ከሆነ ነገራችን ሁሉ ከፍቅርና ከቅንነት መንገድ የራቀ ነውና ጠንቀቅ እንበል።

የአንዳንዶች ፍቅር ግን ፀጥታንና አለመነጋገርን ምክንያት አድርጎ ሊፈታ እንደሚችል መጠርጠሩ አይከፋም። አንድዬ “ፍቅር ሲጠና ቆሎ ያጎራርሳል” ይሉትን ተረት በእኛም ላይ እስኪያስተርትብን ድረስ የምትከተለዋን የጲላጦስ ግጥም ከ“ሴትና ፈጣሪ-የግጥም” መድብል ተገባብዘን እንለያይ፤

ጨዋነት

ለዓመታት ስኖር ከሚስቴ አብሬ

ቃል ወጥቶኝ አያውቅም ይኸው እስከዛሬ

ዝምታን የለበስሁ አይደለም ፈርቼ

እንዳልረብሻት ነው በመሃል ገብቼ።

ውዶቼ ቆሎ የሚያጎራርስ ፍቅር ይስጣችሁ አቦ፤ ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
2207 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 90 guests and no members online

Archive

« July 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
            1
2 3 4 5 6 7 8
9 10 11 12 13 14 15
16 17 18 19 20 21 22
23 24 25 26 27 28 29
30 31          

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us