“የጅብ ችኩል. . .”

Friday, 22 January 2016 12:54

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . ቸኩለን የሰራናቸው ነገሮች ከሚያስከትሉት የፀፀት ራስምታት ይሰውረን። በምናቅደውም፣ በምንተገብረውም፤ በምናገኘውም በምናጠራቅመውም ነገር ሁሉ “የጅብ ችኩል” ከሆን ቀንድ መንከሳችን ሳይታለም የተፈታ ነው። . . . ታዲያ አንዳንዴ በንዴትና በፀፀት መካከል ስንዋልል የምንናገረው ነገር “ካፍ የወጣ አፋፍ” ይሉት ነገር ነው።

እስቲ የፀፀት ነገር ከተነሳ አንዲት ጨዋታ ላምጣ። ባል በሚስቱ ነገር እርር ትክን ያለው ይመስላል። በአፍላ የፍቅር ጊዜያቸው እፍ -ክንፍ እንዳላለ አሁን ላይ እሷን እርግፍ አድርጎ የሚተውበትን አጋጣሚ እየፈለገ ነበር። ታዲያ አንድ ቀን እንዲሁ እንደተፋጠጡ ነገር በሆዱ ያደረው ባል ምን ይላል? “አንድ ሰው ከሰረቀ ሁሌም ቢሆን ሲፀፀት ይኖራል፤ ይህ ሳይታለም የተፈታ ሀቅ ነው” ብቻውን እያጉረመረመ ነበር። ዳሩ ግን ሚስት ሰምታው ኖሮ፤ “የኔ ፍቅር! እኔን እኮ ወላጆቼ እምቢ ሲሉህ ሰርቀኸኝ ነው ያገባኸኝ፤ ታስታውሳለህ አይደል?” ብትለው ባል ሆዬ ምን ቢል ጥሩ ነው? “እርሱ እኮ ነው፤ እስካሁን ይኸው የእግር ውስጥ እሳት ሆኖ የሚያንገበግበኝ” ብሎላችሁ ሆድ ያባውን ያለብቅል ዘረገፈው። አንድዬ ብቻ የማናምንበትን ከማድረግና፤ የማንወደውን አይነት ኑሮ ከመኖር ይሰውረን አቦ!!

“የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል” ይሉት ተረት ብዙ ነገራችንን ይገልጻል። ለመፍረድ ስንቸኩል፤ ለመደምደም ስንቸኩል፣ ለመወሰን ስንቸኩል፣ ለመሳደብ ስንቸኩል፤ ዱላ ለማንሳት ስንቸኩል ስንትና ስንት ስጋ እና መረቅ እየጠበቀን ቀንድ ስንነክስ ከርመናል መሰላችሁ።

በተለይ -በተለይ በክፋት ላይ ችኩልነት ሲደመር የስንቱን ቤት፣ የስንቱን ድርጅት፣ የስንቱን ዝምድና፣ የስንቱን ህብረት፣ የስንቱን ሀገር አፈራርሷል መሰላችሁ?. . . ወዳጄ ዘንድሮ ግራና ቀኝ አይቶ፤ ነገሩን አጣርቶ ፍርድ ከሚሰጠው ይልቅ ፍርድ የሚያመልጠው ደፋር ፈራጅ በዝቶልናል። አንድዬ ብቻ በድፍረትና በፍጥነት ከሚወስን ሰው ይጠብቀን።

እናላችሁ “የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳልን” እያሰላሰልን፤ የምናጣጥማት የድፍረት፣ የፍጥነትና የፀፀት ማሳያ ትዝብት አዘል ጨዋታን እነሆ፤ ነገርዬዋ የፈረንጆች ታሪክ በመሆኗ ወይ ጉድ ማሰኘቷ አይቀርም። ልጅቷ አዲስ የቤት ሠራተኛ ናት። እናም ተቀጥራ ስራዋን በጀመረችበት የመጀመሪያ ዕለት የሳሎኑ ስልክ ጠራ። ባለቤቷ ከእንግዳ ጋር መኝታ ቤት ውስጥ በመሆኗ የሳሎኑን ስልክ አንስታ መልዕክት መቀበል ግድ ነበር። ስልኩን አንስታ “ሄሎ” ከማለቷ፤

“ሃሎ አንቺ ማነሽ?” በስልኩ ውስጥ ጎርናና ድምፅ ጠየቀ።

“እኔ አዲሷ የቤቱ ሠራተኛ ነኝ” መለሰች ወጣቷ።

“እኔ እኮ የቤቱ ባለቤት ነኝ በቤታችን ሠራተኛ የሚባል ነገር የለም” ሰውዬው በመገረም ያናግራት ጀመር።

“ይቅርታ ጌታዬ እርስዎ ላያውቁ ይችላሉ። ባለቤቷ ዛሬ ጠዋት ነው ያስገቡኝ። ሰራተኛዋ የቤቱ ባለቤት መሆናቸውን በማወቋ ድምጿ ለስለስ ማለት ጀመረ።

“መልካም እሺ አሁን ባለቤቴ አጠገብሽ ካለች አቅርቢልኝ ላናግራት” ሰውዬው ተናገረ።

“ይቅርታ ጌታዬ ባለቤትዎ ከአንድ ሰውዬ ጋር መኝታ ቤት ውስጥ ገብተው ከዘጉ ቆይተዋል። በርግጥ ሻይ እንዳቀርብላቸው አዘውኛል፤ እግረ መንገዴን ልጥራቸው ይሆን እንዴ?” ሰራተኛዋ ይህን ከማለቷ የሰውዬው ድምፅ በንዴት ተለዋውጦ። “ትሰሚኛለሽ አዲሷ ሰራተኛችን አንድ ነገር ልትተባበሪኝ ፍቃደኛ ከሆንሽ ስመጣ 30ሺህ ብር ልስጥሽ ቃል እገባልሻለሁ” አለ።

“ምን ልርዳዎ ጌታዬ”

“ከሱቅ መርዝ ገዝተሸ በሁለቱም የሻይ ብርጭቆ ውስጥ በማድረግ የቅሌታቸውን ዋጋ እንዲያገኙ አድርገሽ ግደያቸው” በድፍረትም በፍጥነትም ሰውዬው ሞት ፈረደባቸው። በቀረበላት የገንዘብ ስጦታ የጓጓችው ወጣቷ ሰራተኛ ስልኩን ሳትዘጋ እየተሯሯጠች ወደሱቅ በመሄድ እንደታዘዘችው በፍጥነት የሚገድል መርዝ ገዝታ ተመለሰች። ቀጥላም እንደታዘዘችው መኝታ ክፍላቸው ውስጥ በመላፋት ላይ ለሚገኙት ጥንዶች የተመረዘውን ሻይ አቀረበችላቸው። ሁለቱም የቀረበላቸውን ሻይ መጎንጨት ሲጀምሩ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እንደሚሞቱ እያሰበች የመኝታ ክፍሉን በር ዘግታ ወጣች።

ወደሳሎን ቤት ተመልሳም ክፍት የተወችውን ስልክ አንስታ “ጌታዬ እንዳዘዙኝ አድርጌያለሁ። በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ መሞታቸው አይቀርም። ሬሳቸውን ምን ላድርገው?” ስትል ጠየቀች።

ከወዲያ በኩል የበቀል ፅዋውን በማጣጣም ላይ የሚገኘው ባልም፣ “መሞቸውን እርግጠኛ ከሆንሽ በመኝታ ቤቱ መስኮት በኩል የሁለቱንም ሬሳ ወደመዋኛ ገንዳው ወርውሪው አላት። ይሄን ጊዜ ሰራተኛዋ ተገርማ፣ “ጌታዬ ግቢው ውስጥ እኮ አንድም የዋና ገንዳ የሚባል ነገር የለም” ከማለቷ፤ ሰውዬው ተገርሞና በድንጋጤ ተሞልቶ፤ የቤት ቁጥሩንና ስልክ ቁጥሩን ሲጠይቅ እንደተሳሳቱ ሁለቱም ተረዱት ይባላል። በተሳሳተ ስልክ ቁጥር ስንት ደፋርና ባለጌ ሰው እንደገጠመን ቤቱ ይቁጠረው።

“የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል” ማለት እንግዲህ እንዲህ አይነቱን ባለታሪክ ነው። አንድዬ ብቻ ቸኩለን ከመወሰን፤ ከመፍረድና ከመደምደም፤ ለአላስፈላጊ በቀል ከመነሳሳት ጠብቆ ከፀፀት ነፃ እንድንሆን ይርዳን። ቸር እንሰንብት!!!n

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
740 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 89 guests and no members online

Archive

« July 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
            1
2 3 4 5 6 7 8
9 10 11 12 13 14 15
16 17 18 19 20 21 22
23 24 25 26 27 28 29
30 31          

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us