ዋናው ነገር. . .

Wednesday, 27 January 2016 12:43

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!? . . . ከምንም ነገር በላይ ዋናው ነገር ላይ መተማመን የሚችል ሰው ይመቸኛል። ለመሆኑ በህይወታችን ውስጥ ዋናው ነገር ምንድነው?. . . ጤንነት? ሥራ? ትዳር?. . . ሁሉም ትክክል ነው። አንድ ነገር ግን እርግጥ ነው ከንጉስም ንጉሰ - ነገስት እንዳለ ሁሉ፤ ከዋናም ዋና አለው። የአገራችን ሰው ከሚበልጥ ሁሉ የሚልቅ ነገርን ለመግለፅ ሲፈልግ “ከእንጨት መርጦ ለታቦት፣ ከሰው መርጦ ለሹመት” ሲል የሚተርተው ወዶ እንዳይመስላችሁ። ለማንኛውም አንድዬ ከሁሉም ነገር በላይ የሆነውን ዋና ነገር አያሳጣችሁ አቦ!

እስቲ ደግሞ ለዛሬ ትዝብት አዘል ጨዋታችንን ለማሳመሪያነት ከፓውሎ ኩዌልሆ ቁም ነገር አዘል ወጎች መካከል አንዷን እንምዘዝ። አንድ ሽማግሌ ባህታዊ ዝናው እጅግ የገነነ ንጉስ ቤተመንግስት ለጉብኝት ተጋብዘው ይገባሉ። ንጉሱ ሁል ጊዜ ስለ ባህታዊው ሲያስብ የሚሰማውን አንድ  ሃሳብ እንዲህ ሲል ሰነዘረ፤ “የተቀደሱት አባቴ ሆይ! በብህትውና ህይወትዎ በጥቂት ነገር ረክተው መኖር መቻልዎን ሳስብ በአያሌው እደነቃለሁ” ንጉሱ ተናገር። የንጉሱ ንግግር ፍሬ ነገሩ የገባቸው ባህታዊም ፈገግ ብለው፣ “እኔ ደግሞ ንጉስ ሆይ ከእኔ ባነሰ ንብረትዎ የረኩትን እርስዎን ሳስብ በእጅጉ ነው የምደነቀው” ሲሉ መለሱ።

ንጉሱ ግራ በመጋባት፣ “አባቴ እኔ ነኝ ከእርስዎ ያነሰ ንብረት ያለኝ?” ሲል በአግራሞት ጠየቀ። ባህታዊውም የንጉሱን መገረምና ግራ መጋባት ለማርገብ ሲሉ እንደሚከተለው ማስረዳት ጀመሩ፤ “ንጉስ ሆይ! እኔማ ንብረቴ ብዙ ነው። በእውነቱ የሌለኝ ነገር የለም። የሰማይ ሰማያት ዝማሬ አለኝ። ወንዞችና ተራሮች አሉኝ፡ ጨረቃና ፀሐይም የኔ ናቸው። ምድርን ሁሉ ገዝቻለሁ፤ ምክንያቱም በልቤ ውስጥ የሁሉ የበላይ የሆነው አምላክ ነግሷልና። ግርማዊነትዎ ግን በአንፃሩ ድሃ ነዎት። ግዛትዎ ከዚህች በድንበር ከተከለለች ምድር አይሰፋም። እኔ ግን ዋናውን “ባለንብረት” ይዣለሁና ሁሉም ንብረቴ ነው” አሉ ይባላል።

ወዳጄ ዋናው ነገር ዋናውን ነገር ዋና ማድረግ ነው የሚባለው እኮ ለዚህ ነው። መድሃኒት አዋቂውን ሳይሆን ጤና ጠባቂውን ዋና ማድረግ ይሻለናል። ጋብቻውን ሳይሆን ትዳሩን ዋና መመዘኛችን ማድረግ ይገባናል። ከመኪና ዙዋሪው ይልቅ መኪና ሰሪውን ማድነቅ ይገባናል። ከገፀ-ባህሪው ይልቅ ገፀ -ባህሪውን ተላብሶ የተጫወተውን ተዋናይ ማድነቅ ይገባናል። ከተመራማሪው በላይ ተመራማሪውን ያስተማረውን ማክበር መቻል ይገባናል። ከበራሪው ይልቅ አብራሪውን ብናደንቅ ሳይሻለን ይቀራል? ለምን ቢባል ከተሰራው ይልቅ ሰሪው ዋና ነውና።

ዘወትር የምትተረክ የቻይናውያን አባባል አለች፤ “አንድን ሰው ከባህር ውስጥ እያወጣህ ከምትሰጠው አሳ አወጣጡን ብታስተምረው ትጠቅመዋለህ”. . . ዋናውን ነገር ማስተማሩ ጥሩ  ነው። ለራሱም ለሌላውም መትረፍ የሚችለው ዋናውን ዕውቀት የራሱ ማድረግ የቻለ ዕለት ነውና። ስለዋናው ነገር ስናወሳ አንዲት ተረት ትዝ አለችኝ። ሴትየዋ በተደጋጋሚ ጊዜ ቡሆዕቃዬ (ማቡኪያዬን) ውሻ ለከፈብኝ በሚል የንሰሐአባታቸውን እየጠሩ “አባ ይባርኩልኝ” እያሉ ያስረጫሉ። አባም ከአንዴ ሁለቴ ሶስቴ ተመላልሰው የነፍስ ልጃቸውን ማቡኪያ መርጨት አልታከቱም ነበር። ታዲያ ግን መደጋገሙ በርትቶ ለአራተኛ ጊዜ “ኧረ አባ ቡሃቃዬን ይርጩልኝ ይህቺ ውሻ አላስቀምጥም አለችኝ” በሚል ተማፅንኦ ቢደርሳቸው ወደሴትየዋ ቀርበው ምን ቢሉ ጥሩ ነው? “የኔ ልጅ ይሄ ነገር እኮ በዛ አንቺ ቡሃቃሽን መጠበቅ ካቃተሸ አንደኛውን ውሻዋን አምጪልኝና እርሷን ልርጭልሽ” አሉ ይባላል። እንደአፍሪካዊ መሪዎች በመልካም አስተዳደር ጉዳይ ላይ ደጋግሞ ከመነጋገር እንዲህ ችግሩ ላይ መወሰን ሳይሻል አይቀርም ጎበዝ። ቂ-ቂ-ቂ!!!!!

ሰዎች ዋናው ነገራቸው ሰላም፣ ነፃነት፣ ፍትህ ነው ብለው ሲያምኑ እነርሱን ለማግኘት የስደት፣ የእስራትና የሞት መስዋዕትነትሁሉ ሊከፍሉ ይችላሉ። ለምን የሚል ካለ ለእነርሱ ሰላም፤ ነፃነትና ፍትህ ከሁሉም ነገር በላይ ዋናዎቹ ነገሮች ናቸውና።

እስቲ ደግሞ በምትከተለዋ ወግ የፍትህ፣ የሰላምና የነፃነት ጥማት ጥጉ የትድረስ እንደሚደርስ እንመልከት ።. . . ታሪኳን ከ “ጥበብ” መፅሐፍ እንዳነበብናት ማስታወሱ አይከፋም። ታይ በተባለ ተራራ አቅራቢያ የምትኖር አንዲት ሴት ዘወትር በእንባና ሀዘን እየተሰቃየች እንደሆነ ኮንፊሺየስ ይሰማና ወደእሱ ያስጠራታል። ደቀመዛሙርቱ በተሰበሰቡበት ስፍራም ሴቷ ደርሳ እንደቆመች ኮንፊሺየስ፣ “አንቺ ሴት ዘወትር በታይ ተራራ ስር በሀዘን እንደምትኖሪ ሰምቻለሁና ምን እንደሆንሽ ልትነግሪኝ ትችያለሽ?” በማለት ይጠይቃታል። ሴቷም፣ “የባሌ አባት፣ ባሌና ብቸኛው ወንድ ልጄ ከተራራው አቅራቢያ የሚኖር ነብር በላብኝ። በዚህም ምክንያት ዘወትር አለቅሳለሁ” በማለት መለሰችለት።

በታሪኳ ያዘነውና የተገረመው ኮንፊሺየስም፣ “እንደዚህ ከሆነ አንቺስ ለምንድነው በዚያ የነብር መኖሪያ በሆነ አስፈሪ ስፍራ የምትኖሪው?” በማለት ጠየቃት። “መምህር ሆይ! በዚያ ተራራ ስር ጨቋኝ ገዢ የለም እኮ” አለችው። በዚህ ጊዜ ኮንፊሺየስ ወደደቀመዛሙርቶቹ በመዞር፣ “ልብ በሉ! ጨቋን ገዢ ከነብርም በላይ የሚያስፈራ ነገር ነው” አላቸው። . . . ይህቺ ናት ጨዋታ! እኔ የምለው እኛም ወደአፍሪካዊያን መሪዎች ዞር ብለን “ልብ በሉ እንደነብር ነው  የምንፈራችሁ፤ እንደሆረር ፊልም ነው የምናያችሁ፤ ዋናውን ነገር የሚያስተውል ልብ ይስጣችሁ” ብለን ብንነግራቸው ይገባቸው ይሆን እንዴ? መልካም የአፍሪካ መሪዎች የስብሰባ ሳምንት ይሁንላቸው ጎበዝ። . . . ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
776 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1089 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us