የኡ! ኡታ ድርቅ

Wednesday, 03 February 2016 15:04

 

 

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . መቼም ዘንድሮ ያልደረቀ ነገር የለም። ምርታችን ደረቀ፣ ሀሳባችን ደረቀ፣ ዕቅዳችን ደረቀ፣ እንባችን ደረቀ፣ ኑሯችን ደረቀ በቃ ምን አለፋችሁ ድርቅ ተቆጣጥሮናል። (እኔ የምለው የኑሮ ድርቀቱም ከአየር ንብረቱ ለውጥ ጋር ይያያዝ ይሆን እንዴ?)

የድርቅ ነገር ከተነሳ አንድ ሃሳብ አለችን። እነዚህ የቢራ ፋብሪካዎች እንዲህ የሚምነሸነሹት በድርቅ አካባቢ ቅልና ገብስ አልተነካባቸውም እንዴ?.. .  እኛ ነገሩ ሁሉ ደርቆብናል እነሱ ግን በየደቂቃው በቲቪና በሬዲዮ እየተነሱ ይህቺን ተጎንጩ፤ ይህቺን ቅመሱ ሲሉን ግርም እኮ  ነው የሚለኝ። የመጠጥ ነገር ከተነሳ አይቀር አንዲት ሰንበትበት ያለች ቀልድ ታድሳ መጥታለች። ሰውዬው በመስሪያ ቤቱ እልል የተባለለት “ጠጪ” እና “ቃሚ” ነው። ታዲያ የሚሰራበት ግብርና መር መስሪያ ቤት ውስጥ በተጠራው ስብሰባ ላይ አለቅዬው መመሪያ እየሰጡ ነው፣ “ለዘንድሮው ክረምት በርከት ያለ ስንዴ እና ጤፍ ማምረት ይጠበቅብናል” ከማለታቸው ከአፋቸው ነጥቆ፣ “ገብስም ጫትም ጨመር ብናደርግበት አይከፋም” ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ ተናገረ። በዚህ ጊዜ በሰውዬው የዘወትር ተግባር እርር ቅጥል ያሉት አለቅዬው የጎሪጥ እየተመለከቱት ምን ቢሉ ጥሩ ነው? “አሁን እየተናገርን ያለነው ስለሰዎች ምግብ ነው። ያንተን ምግብ ኋላ ላይ እንመለስበታለን” ብለውት እርፍ ቂ-ቂ-ቂ ይህቺ ናት እንግዲ ልክ - ልክን መነጋገር ማለት።

ለማንኛውም አንድዬ እርጥቡን ጊዜ ያምጣልን አቦ!. . . ይህውና ዘንድሮ እዬዬም ሲዳላ ሆኖብን እንባችንም እንኳን ደረቀ እኮ። እንባችን ደረቀ ስል ምን ትዝ አለኝ መሠላችሁ፤ አንድ የፌስ ቡክ ወዳጃችን “ፖስት” ያደረጋት ቀልድ ናት። እንዲህ ትላለች። የእናትና ልጅ ጨዋታ መሆኗ ነው።

“አንተ ማሙሽ ምን ሆነህ ነው የምታለቅሰው?” ስትል እናት እየነፈረቀ ያለውን ልጇን ጠየቀችው።

“አባዬ መዶሻ ይዞ ሚስማር ሲመታ ስቶ ጣቱን ስለመታ” ልጁ አሁንም እያለቀሰ መለሰላት።

“ታዲያ ይሄ ያስቃል እንጂ ያስለቅሳል እንዴ? ነው ወይስ አባትህን በጣም ስለምትወደው አዝነህለት ነው እንዲህ የምታለቅሰው?” ብላ ስትይቀው የሰጣት መልስ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? “ስለሳኩበትማ ነው አሁን የማለቅሰው” ብሎላችሁ እሪታውን ማቅለጥ። (ለካንስ አባት ልጁን በኩርኩም ገጭ አድርጎት ነው ቂ-ቂ-ቂ!)

እናላችሁ አይዞን ማለት ትተን በሰው ስቃይ ስንስቅ በኩርኩም ገጭ ተደርገን ከማልቀስ ይሰውረንማ። እኔ የምለው የአፍሪካ መሪዎች (ያው “ባለመዶሻዎቹ” በሏቸው) በሆነ ባልሆነ ነገር እየሳቱ እራሳቸውን በመቱ ቁጥር እኛ ሳቅ ስንል በስልጣን ኩርኩም ገጭ የሚያደርጉን ነገር ቢቀር ምን አለበት?)

ለማንኛውም የድርቁ ነገር በቁጥር ከምንናገረው በላይ ሳይሆን የቀረም አይመስልምና በኛ አቅም ይፈታል ምናምን ማለታችንን ተወት አድርገን “ኡ ኡ ኡ ድረሱልን” ማለቱ ሳያዋጠን አይቀርም። “ባለቤቱ ካልጮኸ ጎረቤት አይደርስም” እንዲሉ ነው።

ድርቃችን የእህል ብቻ እንዳይመስላችሁ “ኡ!ኡ!ኡ!” ብለን ድረሱልን የምንልበት ብዙ አይነት ድርቅ አለን ጎበዝ። መንግሥታችን በነጋ በጠባ የስብሰባ አፍ መፍቻ ወይም ማፍታቻ ያደረገው “የመልካም አስተዳደር ችግር” የዘወትር ድርቃችን ነው። ግን ኡ! ኡ! ኡ! ብንል ማን ይስማን ይባስ አሁንማ መንግስትም አብሮን ይጮኸ ይዟል። እኔ የምለው የጠፋብንን ነገር “ሌባው” አብሮ ካፋለገን ነገርዬው መቼም አይገኝም።

የመልካም አስተዳደር ችግር ነገር ከተነሳ ምን ግርም ይልሃል አትሉኝም?. . .  መልካም አስተዳደር የጠፋበት ስፍራ እና ፍለጋው የተጧጧፈበት ስፍራ መለያየቱ። ይህን ነገር ለማስረዳት የሙላህ ነስሩዲን ወግ እዚህች ቢጠቀስ ምን ይለናል። የሚወደውና የሚሳሳለት የጣት ቀለበቱ በምሽት የጠፋበት ሙላህ ነስረዲን ከቤቱ ፊት ለፊት ከሚገኝ የመብራት ምሰሶ ስር ይፈልጋል። ታዲያ በመንገድ ያልፍ የነበረ ጎረቤቱ ወደነስረዲን ቀረብ ብሎ፣ “ወዳጄ ነስሩዲን ምን ጠፍቶ እየፈለክ ነው?” ብሎ ይጠይቀዋል። ነስሩዲንም፣ “ከወርቅ የተሰራው የጣት ቀለበቴ ወድቆ ጠፋብኝ” በማለቱ ፍለጋውን በጋራ ማካሄድ ጀመሩ። ነገሩን የሰሙት የሰፈሩ ሰዎችም ተሰባስበው የጠፋውን ቀለበት በመፈለግ ተጠመዱ።

በዚህ መሃል ግን አንድ ብልህ ሰው ወደነስሩዲን ጠጋ ብሎ፤ “እኔ የምልህ ነስሩዲን ቀለበትህ የጠፋው ግን እዚህ’ጋ ስለመሆኑ እርግጠኛ ነህ?” ጠየቀው። ነስሩዲንም ሲመልስ፤ “ነገሩማ የጠፋው ቤቴ ውስጥ ነው። ነገር ግን ብርሃን በሌለው ቤት ውስጥ ከምፈልግ ብርሃን ባለበት ውጪ ብፈልገው ይሻላል ብዬ ነው እዚህ መብራት ስር የምፈልገው” ብሎላችሁ እርፍ። ቂ- ቂ- ቂ! አንዳንዴ አለቆቻችን የመልካም አስተዳደር ችግር ዲስኩር በየስብሰባው መወራቱን ስታዘበው፤ አለ አይደል በየመስሪያ ቤቱ ቢሮ ውስጥ የጠፋውን መልካም አስተዳደር፤ በየስብሰባው አዳራሹ የሚፈልጉት ይመስለኛል። አይመስላችሁም?. . . አንድዬ ብቻ መብታችንን ሰርቆ፣ ኑሯችንን አድርቆ፣ አሰራሩን ሁሉ አጨመላልቆ ሲያበቃ ኡ! ኡታችንን አፍኖ አብሮን ከሚፈልግ ነውረኛ ሰው ይሰውረን አቦ! ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
848 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 374 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us