የሚወጡ እንጂ የማያዋጡ . . .

Wednesday, 10 February 2016 13:33

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . እኔ የምለው “ይውጣ-ይውጣ!” ብለን የመረጥነው እንደራሴ እና “ይውጣ - ይውጣ” ብለን ያፀደቅነው ሕግ ሁሉ ምነውሳ አላዋጣን አለ? እውነቴን እኮ ነው፤ በዚህ ጊዜ በፓርላማ የሚወጣ ሕግ እንጂ የሚያዋጣ ማግኘት ቸግሮናል። . . . እሰይ ችግር ፈቺ ሕግ ወጣልን ብለን ሳንጨርስ ነገር አለሙ ሁሉ ተገለባብጦ ሕጉም ወዲያ ተቀምጦ መፋጠጥ ይዘናል።

ይህን ያስባለኝ ምን መሰላችሁ በቅርቡ የአዲስ አበባን ጎዳናዎች ከአሸዋና ከጠጠር ክምር ነፃ ያወጣል የተባለለት ትዕዛዝ አዘል መመሪያ ይፋ እንደተደረገ እናስታውሳለን።. . . እኛም እሰይ ከመኪና ጋር እየተጋፋን መሄድ ቀረልን ብለን እልል ብለን ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል፤ ብዙ የተባለለት ሕግ ገና ከመውጣቱ ጠጠር እና አሸዋ አፈር ለበሰ መሰለኝ ይኸውና የሚተገብረው አጥቶ እኛም መንገዳችን ጠቦ ከመኪና ጋር እየተጋፋን መሄድ ስራችን ሆኗል።

እኔ የምለው በሚወጡ እንጂ በሚያዋጡ ሕጎች እንዲህ ጉጉታችንን ከጣሪያ በላይ የሚያደርሱት ሕግ አውጪውና ሕግ አስፈፃሚው አይናበቡም እንዴ “. . . ስንትና ስንት ሕግ፣ መመሪያና ደንብ መሠላችሁ ፀድቋል ተብለን፤ ተግባራዊ ይሆናል ተብለን እንደቋመጥንላቸው የውሃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል። እኛን እያቋመጡ በእልልታ ካስጨበጨቡን በኋላ ወዲያው ተግባር ላይ ዜሮ ሆነው በኡኡታ  የሚያስጮሁን በርካታ ሕጎች አሉን።

ያው ተዘወትሮ እንደሚነገረን ሀገራችን የአሪፍ ሕግ ችግር የለባትም፤ የአፈፃፀም እንጂ፤ እውነቱን ለመናገር ግን የማይፈፅሙትን ሕግ ከማውጣት በላይ ምን ኃጢያት አለ? አንዳንዶቹ ደግሞ ሕጉ ከወጣ በኋላ በጀርባ በኩል የሆነ ነገር አምጣ የሚያስብሉ ይሆኑና ግራ ሲገባን እንደሚከተለው ቅኔ ዘራፊ እንሆናለን፡-

ያማዶ ተራራ ረጅም ነው በጣም

በከብት ነው እንጂ በግር አይወጣም።

            (እንዲል ያገሬ ሰው)

ይህን ስል አንድ ጨዋታ ትዝ አለኝ። በአንድ ወቅት አንድ ሰው ይሞትና በሰማይ ቤት የገነትና ሲኦል ምርጫ እንዲሰጠው ይፈቀድለታል። በሁለቱም ስፍራዎች አንድ አንድ ሳምንት በማሳለፍ ምርጫውን እንዲያሳውቅ በተሰጠው ፈቃድ መሠረት በመጀመሪያ በእጅጉ ወደሚጓጓለት ገነት ይገባል።

በገነት ቆይታውም የመልአክት ዝማሬ፣ የፃድቃን ጾምና ፀሎት እንዲሁም ረጅም የፅሞና ጊዜን ተመለከተ። ነገሮች ሁሉ በእርጋታ፣ በትዕግስትና በፍቅር የሚከወኑ ከመሆናቸው የተነሳ ኮሽ የሚል ነገር አይሰማም ነበር። ሁኔታው ከበደው። የጓጓለት ገነት እንዲህ በአጭር ጊዜ ስለሳለችው ተገረመ። በመቀጠልም ወደ ሲኦል ተወስዶ የአንድ ሳምንት ጉብኝቱን ጀመረ። ጉብኝቱም በተድላና በጭፈራ፣ በመዝናናትና በግብዣ፣ በስካርና በጥጋብ የተሞላ ነበር። በምድር እያለ የሚመኘው ቅንጡ ሕይወት በሲኦል እንዳለ አረጋገጠ። እናም በልቡ ውሳኔውን አፀደቀ።

በቀጣዩም ቀን ውሳኔውን ለማሳወቅ በተነሳበት ቅፅበት ምርጫው ሙሉ በሙሉ ሲኦል እንደሆነ ተናገረ። በአጠገቡ ያሉ ሰዎች ግን ተው ይቅርብህ ብለው መከሩት። አልሰማቸውም ነበርና እንደምርጫው የሲኦል በር ተከፍቶለት ገባ።

ወደሲኦል ገና እንደገባ ግን ለሳምንት ያየውን የቅንጦትና የተድላ ኑሮ፤ የስካርና የጭፈራ እንክብካቤና የውቤ በረሃ አይነት ነገር ፈፅሞ ማግኘት አልቻለም። ወደአንድ ፈርጣማ ጎረምሳ ጠጋ ብሎም፤ “እኔ የምለው ባለፈው ስመጣ ያየሁት ሲኦል እኮ እንዲህ አልነበረም፤ ምንድነው የተለወጠው?” ሲል ይጠይቃል። ወጣቱም ሲመልስ፤ “ሰውዬ ባለፈው የመጣኸው እኮ በጎብኚ ቪዛ ነው። ያኔ ደግሞ ሰዎችን ለማማለልና ለማነሳሳት የቅስቀሳ ስራ እያሰራን ነው። ይህ ሕጋችን ነው። እውነተኛው ሲኦል ግን ከእንግዲህ በኋላ የምታየው ይሆናል” ሲል ድብድብና ውንብድና፤ መተናነቅና መተላለቅ፤ ወደማይጠፋው እሳትና ይቅርታ ወደሌለው ፀፀት ጎራ ወረወረው ይባላል።

እኛም ለቅስቀሳና ለሙገሳ በሚበቁ፤ ነገር ግን ከተግባር የራቁ ሕጎች ሲፀድቁ እያየን፤ እልል እያልን ተገላገልን ብለን ሳንጨርስ “ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ” እንዲሉ፤ አፈፃፀም ላይ ዜሮ ይሆንብናል። እናም የሚወጡ እንጂ የሚያዋጡ ሕጎችን እናይ ዘንድ እንለምናለን።

“እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል” እንዲሉ ለጊዜያዊ መተላለፊያነት ያወጣናቸውን ሕጎች የማንተገብራቸው ከሆነ በጣም ያስተዛዝቡናል።

መጀመሪያ እልል አስብለውን በኋላ ግን ካለመተግበራቸው የተነሳ እርር የሚያደርጉን ሕጎች ሁሉ ስያሜያቸው “የሚወጡ እንጂ የማያዋጡ ሕጎች” ይባልልን።

የምሬን እኮ ነው፤ ዕቃዎችን ያለልክ ለጥጠው የሚያስተዋውቁ ማስታወቂያዎች ስመለከት በኋላ ጨጓራ የሚልጡ ላለመሆናቸው ምንም ዋስትና የለንም። ፍቅር ሲጀምርም እንዲሁ ነው። ሲጀመር ፀባዩ/ፀባዩዋ መሬትና የእናት የመሰለን ሁሉ ይሁን ብለን አፅድቀን፤ ትዳር ከፈፀምን በኋላ ግን “በምን ቀን ነው እሷን/ እሱን ያገባሁት” የሚያሰኙን አይጠፉም። በነገራችን ላይ የአፈፃፀም ደካማነት ነገር ከተነሳ ስልጣን ላይ የወጡ ሰዎች ችግር ብቻ ሳይሆን አልጋ ላይ የወጡ ሰዎችም ችግር እንደሆነ ልብ ይባላልን። በአልጋ ላይ አፈፃፀም ደካማነታቸው ምክንያት ስንትና ስንት ትዳሮች እንደፈረሱ ቤቱ ይቁጠረው)

ለማንኛውም አጎጠጎጡ ተብለው ወዲያው ከሚዋጡ፤ መጡ ተብለው ወዲያው ከሚወጡ፤ ፀደቁ ተብለው እኛን ከሚያደቁ፤ ለገሱ ተብለው እኛን ከሚነክሱ፤ ወጡ ተብው ከማያዋጡ ሕጎች ሁሉ አንድዬ ይጠብቀን አቦ፤ ቸር እንሰንብት።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
657 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1038 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us