“ወዳጅ ሲጣላ…”

Wednesday, 17 February 2016 14:25

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?... አንድ ሰው ያሰበው ሳይሳካ ሲቀር፤ ያለመው እውን አልሆን ሲለው፤ የጨበጠው ጉም፤ ያፈሰው አረፋ ሲሆንበት ጊዜ በቁጭት ሰንሰለት እንደታሰረ አዘወትሮ “ነበር ባይሰበር” ማለቱ አይቀርም። ባይሰበርማ ስንትና ስንት ነገር በሆነ ነበር ወዳጄ። የ“ነበር ባይሰበር” ጨዋታን ያስታውሰኝ ሰሞኑን የገጠመኝ ነገር ነው።

 

ከዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለሁ የማውቃትን ልጅ ሰሞኑን አገኘሁ። በአጋጣሚ የተገናኘነው ደግሞ ከጊዮርጊስ ወደሳሪስ በሚወስደው ባቡር ውስጥ ነበር። ልጅቱን ገና ሳያት “ልጁ” ትዝ አለኝ። እርሷና እርሱ በወቅቱ በገቢው ውስጥ የፍቅር ተምሳሌቶች ነበሩ። (እንዲህ እንዳሁኑ “የቫላንታይንስ ዴይ” ደምቆ ሳይከበር በፊት፤ ከበዛብህና ሰብለወንጌል፤ ከሮሚዮና ዡሊየት ቀጥሎ ህያው የፍቅር ምስክሮቻችን “እነርሱ” ነበሩ) … ምን ያደርጋል “ነበር ባይሰበር” ያሰኘኝን ታሪክ ግን የሰማውት በአጋጣሚ በባቡር ውስጥ ተገናኝተን ከመለያየታችን በፊት ነበር።

 

ባቡራችን ከፌርማታ - ፌርማታ በእንግሊዝኛና በአማርኛ ማስታወቂያና ማስጠንቀቂያ እየሰጠ ሲጓዝ እኔና ልጅቱም ከአመታት በፊት በግቢ ስለነበረው ጊዜ የኋሊት በትውስታ እንጓዝ ነበር። የጉዳያችን መነሻ በተሳፈርንበት ባቡር ውስጥ ቆመንና እጃችንን በማንጠልጠያ ዘንጉ ላይ አንጠልጥለን ስንሄድ ባየሁት ነገር በመደንገጤ ነበር። ይህቺ የቀይ ዳማ ወጣት ከታች ውሃ ሰማያዊ ጅንስ ሱሪ እና ከላይ ቲሸርት እንዳጠለቀች ደምቃ ፊቴ ቆማለች። ጥርጣሬዬን ለማረጋገጥ ስል፣ “እኔ የምልሽ ያ ወዳጅሽ እንዴት ነው? ሰላም ነው? አሁንም አብራችሁ ናችሁ አይደል?” የጥያቄዬን ናዳ አዘንበው ጀመር። የልጅቱ ፊት ግን በሀዘን ደመና ተመታ። ለትንሽ ደቂቃዎች ዝም ተባባልን።

 

የባቡሩን መንጠልጠያ ብረት አጥብቃ በመያዝ እጇን ስታነሳ የፊቷን ሀዘን ክንዷ ላይ በድጋሚ በጉልህ አየሁት። ክንዷ ላይ ብዙ የቅርብ ጓደኞቿ የምናስታውሰው ንቅሳት ነበር። አሁን ግን ያ ንቅሳት በስርዝ-ድልዝ እንደተበላሸ ደብተር መልኩን ቀይሯል። የሆነ መጥፎ ነገር እንደተከሰተ ጠርጥሬያለሁ። (ያስቀመጡት ዕቃ እንደነበር አይገኝ፤ አይደል አበው የሚሉት፤ ብዙ ነገር ሳይቀየር አይቀርም ስል በልቤ አሰብኩ)

 

“እኔ ያገባኛል ብዬ ስጠብቀው እርሱ ግን ዲቪ የደረሳት ልጅ አግብቶ በቅጡ እንኳን ሳይሰናበተኝ ከሀገር ከወጣ ሦስት ዓመት አለፈው” አለችኝ፤ በጣም ደነገጥኩ። እኚያ ፍቅራቸው የሚያስቀናን፣ እኚያ ፍቅራቸው ምሳሌ የሆነን፤ እኚያ የት ይደርሳሉ ያልናቸው ልጆች ተለያይተዋል። እርሷ ክንድ ላይ የነበረውን የወዳጇ ስም ንቅሳት ስርዝ-ድልዝ ስመለከት፤ እርሱም ደረቱ ላይ ያስነቀሰውን ስሟን እያሰብኩ፤ “ንቅሳቱን ለማጥፋት ደረቱን አስተልትሎት ይሆን?” ስል እራሴን ጠየኩ። (ዳሩ የጅል ሀሳብ መሆኑ ገባኝ፤ አሜሪካ ንቅሳት አይደለም ፍቅር እንደምታጠፋ እያየሁ ይህን አይነት ጥያቄ መጠየቅ አልነበረብኝም።)

 

ሳሪስ ደርሰን ከባቡር ወርደን፤ ማኪያቶ እየጠጣን ስለተከሰቱት ነገሮች ስናወራ፤ ስለነበራቸው ትዝታ ስናወራ፤ ስለነበራቸው ዕቅድ ስናወራ የወጣቷ ቁጭትና ፀፀት በጉልህ ይታየኝ ነበር። … እናም ይሄን ሁሉ ነገር ሰምቼ “ነበር ባይሰበር” አልኩ በልቤ። የሀገራችን ሰው ወዶ አይደለም ለካ፣ “ወዳጅ ሲጣላ ያረክሳል” የሚለው። የልጅቱን ገላ ሳየው ወዳጇ ምን ያህል እንዳረከሳት ታዘብኩ፡፡

 

ልጆቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ይዋደዱ እንደነበር ጓደኞቻቸው ሁሉ እናውቃለን። ያንን የተማሪነት አስቸጋሪ ጊዜ ካለፉት በኋላ ደግሞ ሁለቱም ስራ እንደያዙ ስንሰማ የበለጠ ደማቅ የፍቅር ዘመን እንደሚኖራቸው እናስብ ነበር። ሀሳባችን ግን ከነበር መዝለል አልቻለም። ከልጅቷ እንደተረዳሁት ፍቅራቸውን ለአሜሪካ አፈር ሰውቶ ከሄደ ሦሰት ዓመታት አለፈው። በዚህ ዘመናዊ ዓለም አንድም ቀን ጽፎላትም ሆነ ደውሎላት አያውቅም። አሜሪካና ያቺ ኢትዮ-አሜሪካዊት ልጅ እንድ ቬርሙዳ ውጪው አስቀርተውታል።… እርሷ ግን ከእርሱ በኋላ ወንድ ለምኔ ብላ፤ ፍቅር ለምኔ ብላ፤ ነበርን ብቻ አንጠልጥላ፤ ከተማ መሀል ገዳም የገባች መስላለች።

 

የት ይደርሳል ያልነው ግንኙነት፣ የት ይደርሳል ያልነው ፍቅር፣ የት ይደርሳል ያልነው ትዳር፣ የት ይደርሳል ያልነው አጀማመር ሁሉ እንዳይሆኑ ሆኖ ሲቀር “ነበር ባይሰበር” ከማለት ውጪ ምን አማራጭ አለን? (እነሆ ዘንድሮ ከንቅሳት በላይ “በቫላንታይን” ስም አልጋ ፍለጋው፤ ፍቅር ወዲያ ወሲብ ወዲህ ዓይነት ነገር መበራከቱን ስትታዘቡ ሰው ሁሉ የወሲብ አብዮት ውስጥ ጭልጥ ብሎ የገባ ይመስላል፤ ነገ ለማይቀጥል ነገር “ወዳጅ ሲጣላ ያረክሳል” ይሉትን ተረት ዝም እንበል እንጂ ጐበዝ። በነገራችን ላይ የሆቴል፣ የአበባ፣ የወይንና የቼኮሌት ገበያው እንዴት ነው?) በረከሰ አልጋ ላይ መዋሰቡስ እንዴት ይታያል?

 

 እናላችሁ ስማቸውን ገላችን ላይ የተነቀስንላቸው፤ ሀሳባቸውን በልባችን የተካፈልናቸው፤ ውጥናቸውን በወረቀት ላይ ያረቀቅንላቸው፤ ጤንነታቸውን የተመኘንላቸው፤ የስልጣን ማማውን ያመቻቸንላቸው፤ አለቅነትን የፈቀድንላቸው ሰዎች ድንገት እንደጤዛ እብስ (ጥፍት) ሲሉ ልብን ከማሳዛንም አልፈው “ነበር ባይሰበር” ይሉትን ቁጭት ያስታጥቁናል።

ውድ በሆነውና የቅዱስ ቫላንታይን ዴይ ስለፍቅር በሚታስብበት በዚህ ሳምንት የፍቅርን ዋጋ ከፍ ስለማድረግ እንጂ፤ የውስጥ ሱሪን ዝቅ ስለማድረግ (የወንዶቹን አላልኩም) መታሰብ ያለበት አይመስለኝም። ውድ ነገርም በነፃ ሲሆን ይረክሳል እንዴ? ይህቺን ትዝብት አዘል ጨዋታ ከመቋጨቴ በፊት አንዲት ከጋብሮቮች ዓለም የተቀዳች ዋዘኛ ጨዋታ እንካችሁ።

 

ጋብሮቮች የንስሃ አባታቸውን ሊጠይቁ የሄዱ ጓደኛሞች ስለመብራት ጉዳይ ውይይት ይከፍታሉ። “አባታችን ለምን ሁልጊዜ በሻማ ይገለገላሉ? የመብራት ዋጋ እኮ እጅግ ዝቅተኛ ነው። ይህን አያውቁም እንዴ?” ሲሉ ይጠይቃሉ። ቄሱም ሲመልሱ፣ “አውቃለሁ ልጆቼ፤ ነገር ግን ሻማዎቹን የማገኛቸው በነፃ ስለሆነ ለእኔ የበለጠ ርካሾች ናቸው” አሉ ይባላል።

 

አንድዬ ብቻ ፍቅራችንን ከሚያረክሱ፤ ክብራችንን ከሚያንኳስሱ፤ ውለታችንን ከሚረሱ፤ በሰጠናቸው አለቅነት ስም ከሚናከሱ፤ በፍቅር አስነቅሰውን በጥላቻ ከሚያስደልዙን ሰዎች ይጠብቀን እናም “ወዳጅ ሲጣላ ያረክሳል” ከሚሉት ተረት ይሰውረን። ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
1154 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 914 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us