ውሸት እና ስንቅ. . .”

Wednesday, 24 February 2016 14:24

 

          ‘ርግማን

እዚህ እዚያ ማዶ -ጥሪ በረከተ

ሆ! ብሎ ተጥራራ - በጋራ ከተተ

አይሆን እንዳቀዱት ሆድ ስላለውዬ

እውነት እርሙስ ቢሆን -መች ሲረታ ታዬ።

ሀሳብ እየሆነ አራምባና ቆቦ

በውሉ ባይፀና ተናደ ተክቦ!!

ስጋት ጉም ‘ንዲሆን - ሺ ቢሆን ስለቱ

አንድ ልብ ካልሆኑ አይሰምርም ፀሎቱ

ርግማን ምረቃ - ጥንቱኑ ሆኖለት

ቆረጠው! ያልነውን - ዕድሜ ቀጠለለት።

            (ገጣሚ ውድአላት ገዳሙ፤ “ስደተኛ ግጥሞች” መድብል የተወሰደ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . እነሆ አለን ብለን የምናወራለት፤ የኛ ነው ብለን የምንመካበት ነገር ሁሉ ደመናን የመዝገን ያህል ሲሆንብን ጊዜ ግራ መጋባታችን አይቀሬ ነው። . . . እኔ የምለው ገጣሚዋ እንዳለችው “ርግማን ተመርቀን” ይሆን እንዴ?. . . ጎበዝ መጠርጠሩ አይከፋም። እውነት ግን የከፉ ሰው ዕድሜ ረጅም ነው እንዴ?. . . ምን ይደረግ ቢቸግረን የጅል ጥያቄ መጠየቅ ጀመርን መስለኝ።

የክፉ ሰውና የደግ ሰው ዕድሜ ንፅፅር ስናነሳ አንድ ጨዋታ ትዝ አለችኝ። ልጅ እናቱን ይጠይቃል፤ “እማዬ ደጋግ ሰዎች ግን ለምንድነው ቶሎ የሚሞቱት?” እናት በልጇ ጥያቄ ተገርማ ስታበቃ በምሳሌ ልታስረዳው ታስብና፤ “ልጄ በአበባ በተንቆጠቆጠ መናፈሻ ውስጥ ስትመላለስ ቀድመህ ለራስህ እንድትሆን የምትቀጥፈው የትኛዋን አበባ ነው?” ስትል መልሳ ትጠይቀዋለች። ልጅም፤ “ከሁሉም አብልጣ የምታረዋን ነዋ!” ይላል። እናትም ፈገግ ብላ፤ “አየህ ደጋግ ሰዎችም እንዲሁ ናቸው” አለችው ይባላል።

እንካችሁ ደግሞ እስቲ ይህቺን ጨዋታ። . .  ሴትየዋ ባለትዳር ብትሆንም ከውሽማዋ ጋር ቅልጥ ያለ ፍቅር ይዟታል አሉ። ታዲያላችሁ ውሽምዬው የባለቤቷ ሹፌር ቢሆን ምን ይላችኋል። ለካንስ ሚስትና ውሽሜ የሆነች ሴራ በአባወራው ላይ ጎንጉነዋል።. . . እናም ሹፌር ነው የተባለው ውሽማ አባወራውን ከስራ ወደቤትና ወደመስክ ሲያንሸራሽረው ከአንዴም ሁለቴ የመኪና አደጋ እንዲደርስበት ሞክሮ ነበር። ይህ የሹፌሩ ነገር ያላማረው ባል ምሽት ቤቱ ሲገባ በንዴት እየተብከነከነ፤ “እኔ ይኼን ሹፌር ልቀይረው ነው። ይኸውና ሰሞኑን እኮ ከአንዴም ሁለቴ የመኪና አደጋ አድርሶብኝ ነበር። ፈጣሪ ነው ያተረፈኝ” ( አይ ይሄኔ ያራዳ ልጆች  በልባቸው ምን ይላሉ መሰላችሁ? “የዋህ ምን ይሆናል”. . . እናላችሁ ከአደጋ መትረፉን ለሚስቱ ሲነግራት ሚስት ምን ብትለው ጥሩ ነው “ምናለበት ታዲያ ሶስተኛ ዕድል ብትሰጠው፤ በኋላ በውሳኔህ ትፀፀታለህ” ብላላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ. (ምናለ እስኪገድልህ ብትጠብቀው ከማለት እኮ አይተናነስም)

የአገራችን ሰው እንዲህ አይነት የአስመሳዮች ጨዋታ ሲገጥመው ምን ይላል መሰላችሁ?. . . “ውሸትና የስንቅ አቁማዳ እያደር ይቀላል” ይላል። አንድዬ ብቻ እያደሩ ከሚቀሉ ወዳጆች፤ እያደሩ ከሚቀሉ ታላላቆች፣ እያደሩ ከሚቀሉ የትዳር አጋሮች፣ እያደሩ ከሚቀሉ ካድሬዎች፣ እያደሩ ከሚቀሉ የሃይማኖት መሪዎች እያደሩ ከሚቀሉ አመራሮችና የፖለቲካ ሰዎች ይሰውረን አቦ!!!. . . እንደውሸትና እንደስንቅ አቁማዳ እያደር ከመቅለል እኛንም በክህደት ከማሳቀል የሚሰውር “ሚሽን” ይሰራልን ይሆን እንዴ?

በተለይ - በተለይ የኔ ነው በምትሉት ህይወት ውስጥ እንዲህ አይነት ውሸትና ክህደት ሲፈጠር በእጅጉ ማማረሩ የተገባ ቢሆንም አንድዬ ከአራጁ የሚውል በሬ እንዳንሆን ይጠብቀን ማለቱ አይከፋም።

ጨዋታችንን ለማዋዛት ያህል አንዲት የውሽማ ታሪክ ከወደገጠር እንምዘዝ። . . . ሰውዬው (አባወራው) ትጉህ የሚባል ገበሬ ነው። ጠዋት ወጥቶ ማታ ነው የሚገባ፤ በዚህ መሀል ታዲያ ሚስት የቀን ጨዋታ ከውሽማዋ ጋር ለምዳ ኖሮ አንድ ቀን ባሏ በጊዜ ወደቤት ይመጣና ነገር ይለወጣል። መደቡ ላይ ጋደም እንዳለም ከውጪ ውሽማ ይመጣል፤ ሚስት ግን በር ላይ እህል እየፈጨች ለውሽማዋ ባሏ ቤት ውስጥ እንዳለ እንዲገባው እንዲህ ስትል ማንጎራጎር ጀመረች፤

ኧረ በሬው - በሬው

ቤቴን አታፍርሰው፤

ራቱን ይብላበት

ደክሞት የዋለ ሰው

ይህቺ ነገር ለተደጋጋሚ ቀናት የሰማት ባልም የሚስትንና የውሽማዋን ቀን መቃጠር ገብቶት ኖሮ እርሱም ድምጹን ከፍ አድርጎ ምን ቢላት ጥሩ ነው?

እኛም እናውቃለን

ሰዋሰው ጨዋታ፣

ቀን ያልተቃጠሩት

በሬ አይመጣም ማታ።

አላት ይባላል። ቂ-ቂ-ቂ- ይህቺ ናት የመነቃቃት ጨዋታ አትሉልኝም? . . . እናም እንደውሸትና እንደስንቅ አቁማዳ እያደር ከሚቀሉ ሰዎች እንዲህ በጊዜ ነቅተን ካልተገላገልን የመጨረሻ ሀዘኑን አንችለውም።

ክህደታቸው እንደይሁዳ፣ ንቃታቸው እንደጎሊያድ፣ እምነታቸው እንደሎጥ ሚስት ከሆነ እያደር ቀላሎች የምናመልክበት ብቸኛው መንገድ ተጋፋጭነት ብቻ ነው። ከአዋቂነታቸው ይልቅ ታዋቂነታቸው፤ ከመንገዳቸው ይልቅ መድረሻቸው፤ ከስጋታቸው ይልቅ ስጋቸውን ብቻ ለምናይላቸው “እያደር ቀላል” ሰዎች “ርግማናችን ምርቃት” ይሆናቸው ዘንድ እንዲህ ብለን እንለያቸው፤ “ውሸት እና የስንቅ አቁማዳ እያደር ይቀላል”. . . አንድዬ እያደር ከሚቀሉ ነገሮች ሁሉ ይሰውረን አቦ! ቸር እንሰንብት።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
664 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 915 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us