“ወጣ-ወጣና እንደ ሸምበቆ…..”

Wednesday, 02 March 2016 13:17

 

በመስራት ነው እንጂ ላብን በመጥረግ

በመስረቅ በመንጠቅ የለም መበልጠግ።

ቁጥራቸው ብዙ ነው ግፍ ሰርተው በከንቱ

ባመፅ የሰው ገንዘብ ሰብስበው ሲከቱ

ደም እያነቃቸው ሳይበሉት የሞቱ።

(ከክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል፤

“የቅኔ ውበት” መፅሐፍ የተወሰደ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?.... እኔ የምለው ይሄ የመልካም አስተዳደር ችግር እና የሙስናው ስር መስደድ እኛን እርር ድብን ከማድረግና ከሚዲያ ፍጆታ በዘለለ የምር የምንገማገምበት ጊዜ መቼ ነው?... የምሬን እኮ ነው፤ በእኛ የኑሮ ውድነት መሰላል ላይ፤ በእኛ የቤት ችግር ላይ፤ በእኛ የትራንስፖርት ትግል ላይ ተንጠላጥለው ስንቶች ሀብት እያካበቱ መልሰው በየስብሰባው “የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከህዝቡ ጋር ሆነን እንዋጋለን!” በሚል ጉንጭ አልፋ ዲስኩር ደጋግመው ሲሸነግሉን መስማት “ሼም” አይደለም እንዴ?... (ይህቺ ከህዝቡ ጋር ሆነን እንዋጋለን የሚሏት ነገር ቅኔዋ ሲፈታ “ህዝቡን በጋራ እንወጋዋለን!” እንደማለት ናት እንዴ? ግድ የለም ይጣራልን አቦ!)

እዚህች’ጋ ገጣሚና ደራሲው በዕውቀቱ ስዩም ሙስና ላይ የተሳለቀበትን አንድ ግጥም “ከስብስብ ግጥሞቹ” መሀል እነሆ፡-

ኀሰሳ ሥጋ

እልፍ ከሲታዎች ቀጥነው የሞገጉ

“ሥጋችን የት ሄደ?” ብለው ሲፈልጉ

በየሸንተረሩ፣ በየጥጋጥጉ

አስሰው አስሰው በምድር በሰማይ

አገኙት ቦርጭ ሆኖ ‘ባንድ ሰው ገላ ላይ።

አንዳንዴ ሳስበው አዲስ አበባ ውስጥ ሆነው አውሮፓን የሚያስንቅ አይነት ኑሮ የሚኖሩ ሰዎች ስመለከት፤ አለ አይደል ከትንሽ ቅናት ብጤ’ጋ “በእነዚህ ሰዎች ቤት ውስጥ የኔም ሀብት አለበት” ብዬ እላለሁ። (እውነቴን  እኮ ነው፤ ጐበዝ በጠራራ ፀሐይ ሙስና ሕጋዊ መስሎ “ቢዝነስ ነው” እየተባለ በሚሰራበት በዚህ ጊዜ በእኛ ደም የደለቡ ሁሉ ወየውላቸው)… ደም እያነቃቸው ድፍት እንዳይሉ ነው የምሰጋላቸው።

እኛ በጋራ ባጣነው ነገር ልክ አንድ ሰው ብቻውን በቅንጦት ሲኖር ማየት ምን ይባላል? (አንዳንድ ምስኪኖች “እነሱማ ተመርቀው ነው” ሊሉን ይችላሉ። ጐበዝ እኛስ መቼ በአደባባይ ተረግመናል እንዴ? ነው ወይስ “ዝርፊያ ይቅናችሁ!” ይሉት አይነት ምርቃትም እንዲህ በቀላሉ ይሳካል ማለት ነው?)… የምር ግን ሰው በፎቅ ላይ ፎቅ፤ በመኪና ላይ መኪና፤ በሰፈር ላይ ሰፈር፤ በሚስት ላይ ሚስት፤ በወንበር ላይ ወንበር፤ በሀብት ላይ ሀብት የሚያገኘው ሰርቶ ነው ወይስ አሰርቶ?... ግድ የለም ይሄም ቢሆን ይጣራልን አቦ!

ለእኛ ኑሮ ተራራ ሲሆንብን፤ ለእነ አጅሬ ኑሮ ፎቅ በፎቅ ሲሆንላቸው ታዲያ ምን ይባላል።… ግድ የለም እምባችን ጐርፍ ሆኖ ይወስዳችኋል ምናምን እያልን አናስተዛዝንም። ግን-ግን በአንድ ሀገር፤ በአንድ መንደርና በአንድ ሕገመንግስት ስር እስከኖርን ድረስ ምናለበት ትንሽ እንኳን “ፌርነስ” ቢኖር መባባሉ ደግ አይመስላችሁም?

እስቲ ደግሞ ትዝብታችንን በጨዋታ ለማዋዛት ያህል የከተማችንን የፎቅ ብዛት የምታስታውስ አንዲት ወግ ከጋቭሮቮዎች መንደር እንካችሁ።… ጋብሮቮው መኝታ ፍለጋ ሆቴል ቤት ይሄዳል። “ለአንድ ሌሊት ስንት ነው የምታስከፍሉት?” ጠየቀ። “ክፍሉ አንደኛ ፎቅ ላይ ከሆነ አስር ብር፤ ሁለተኛ ፎቅ ከሆነ ስምንት ብር፣ ሦስተኛ ፎቅ ከሆነ ስድስት ብር፣ አራተኛ ፎቅ ከሆነ ደግሞ አራት ብር ነው የምናስከፍለው” የሆቴሉ እንግዳ ተቀባይ የተጠየቀውን አብራራ።

ጋብሮቮው ጥቂት አሰብ አድርጐ ከሆቴሉ መውጣት እንደጀመረ እንግዳ ተቀባዩ ድምፁን ከፍ አድርጐ፣ “ምነው ኪራዩ በዛብዎት እንዴ?” ሲል ጠየቀው፤ ጋብሮቮውም ሲመልስ፣ “ኪራዩ በዝቶብኝ ሳይሆን ፎቃችሁ አንሶብኝ ነው” ብሎ ሄደ። ቂ…ቂ… ቂ…! እኛ ዘንድ ያሉት ሰዎች ግን አብዛኞቹ ፎቆች ከሰማይ ብቻ ነው የሚያንሱት ቂ… ቂ… ቂ…!

እናላችሁ ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል እንዳሉት፤ “ደም እያነቃው ሳይበሉት የሞቱት” ይበዛሉና የህሊና ሰው ያድርገን፤ አልያ ግን ሀብታችንን፣ ላባችንንና ወዛችንን በዕውቀቱ ስዩም እንዳለው “አንድ ሰው ቦርጭ ላይ” ያየነው እንደሆን ያ ጊዜ የክፉ ቀን ምልክት ታይቷል ማለት ነው።

የመልካም አስተዳደር ችግርና ሙስና ላይ የመጨረሻ የወግ ድንጋይ ከመወርወራችን በፊት የድምፃዊ መሀሙድ አህመድን አንዲት ስንኝ ላስታውሳችሁ፡-

ባልደከሙበት ሀብት ሰማይ የነበሩ

አይተናቸው የለ ወድቀው ሲሰበሩ።

አንድዬ የምንተዛዘንበትና የምንተጋገዝበትን ጊዜ ያቅርብልን። በሚያልፍ ነገር ውስጥ የማያልፍ የነገን መልካም ታሪክ ለመስራት የምንችል ሰዎች ያድርገን።… አልያ ግን የሀብታችን፣ የዝናችንና የወንበራችን ነገር ሁሉ “ወጣ ወጣና እንደ ሸምበቆ፣ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ” አይነት መጨረሻ እንዳይኖረው እሰጋለሁ። ቸር እንሰንብት!

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
994 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 951 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us