ልክ እንደ “ጆተኒ”. . .

Wednesday, 09 March 2016 13:49

እንደምን ሰንብታችኋል ወዳጆቼ!?. . . ለዛሬ ትዝብት አዘል ጨዋታችን እንደመቆስቆሻ ትሆነን ዘንድ ከወደ ትግራይ የተገኘችን ተረት እነሆ፤ “አፌ ዝም ብሎ እጄን ይጎራረሱበታል” ቂ-ቂ-ቂ- ድንቅ አባባል አይደለች?. . . ይኸውና እኛስ ኪሳችን ደርቆ አፋችን ዝም ብሎም አይደል “እነ እከሌ” በስማችን ቁንጣን እስኪይዛቸው የሚጎራረሱት?

እኔ የምለው ፆመ ልጓሙን እንዴት አጠባበቃችሁትሳ?. . . ግድ ነዋ! “ቫላንታይንስ ዴይ አመለጠን” ያለሁሉ ከአልጋውም ከስጋውም ቅዳሜና እሁድን ሲታገል ውሎ ማደሩን ሰምተናል። እኔን ግን የቱ አሳቀኝ መሰላችሁ?. . . አንዱ እኮ ነው፤ ልጅቱ አንጀቱ እስኪርስ የሆነ ነገር ሆናለታለች መሰለኝ ሲለያዩ ምን ቢላት ጥሩ ነው? “እንደዚህ ፆሙን ካሰርን ስንፈታው እንዴት ሊሆን ነው?” ቂ-ቂ-ቂ አሪፍ ጥያቄ አይደለች (እዚህችጋ ሀሳብ አለን ወጪ ለመቀነስ ያህል “ቫላንታይን ዴይ” እና “ቅበላ” ቢቀላቀሉ ምን ይለናል?. . . እንዲህ ናትና ነገርዬው እኮ አይን አውጥቷል ጎበዝ) መቼም ዘንድሮ ወዳጅነት ከጉርሻና ከልፊያ አላልፍ ብሎ አስቸግሯልም አይደል? እንካችሁ የጋሻው አዳል ዘፈን እነሆ፡-

በምን አወቅሽበት በመመላለሱ

ሲታሰር ወደእኔ ሲፈታ ወደሱ።

እናላችሁ ወደዛሬው ትዝብት አዘል ጨዋታችን ስንመለስ ዘንድሮ ሰው ሁሉ እንደ “ጆተኒ” ኳስ ሳንቲም ካልነከሰ አልወጣምም፤ አላዋጣምም ማለት ጀምሯል።  . . . ያኔ ታዲያ መፈፀም የነበረበት ጉዳይ ጠረጴዛ ላይ አፉን ከፍቶ “በእጁ” የመጡት ወዲያው ሲጨርሱ እኛ የባሰ አጥተን ጫማችን ተንሻፎ በእግር እየመጣነው የቅድሟን ተረት በቁጭት መተረት እጣ ፈንታችን መስሏል፤ “አፌ ዝም ብሎ እጄን ይጎራረሱበታል” . . . ጎበዝ እኛን ወደኋላ በማስቀረትና ሌላውን ወደፊት በመግፋት ሰበብ እኮ ስንቱ በእኛ ላይ እየተጎራረሰ እንደሆነ አንድዬ ይወቀው።

ጨዋታችንን ለማሳመር ያህል ልክ እንደ “ጆተኒ” ሳንቲም ካልነከሱ ደም የሚያፋስሱ እና ፍቅርንም የሚያረክሱ ሰዎች እንዳሉ የምታሳይ ወግ እንካችሁ።. . . ወጣቶቹ በጣም ይፋቀራሉ። ታዲያ የልጅቷ ታናሽ ወንድም እንደ ምቀኛ ነገሩን ለቤተሰብ እየተናገረ የልጅቱ ስቃይ በዛ። ይህንንም ለመከላከል የሳንቲም ጉርሻ አስለምዳው ኖሮ፤ አንድ ምሽት ጓደኛዋ ሸኝቷት ከሰፈር ከመመለሱ በፊት ሳም ያደርጋታል። ይህን አድፍጦ ያየው ታናሽ ወንድም ወደቤት ከመግባቷ በፊት ጓደኛዬው ልጅቱን፣ “ይህውልሽ ስንሳሳም ወንድምሽ አይቶናል፤ ምን ይሻልሻል?” ቢላት ልጅት የወንድሟን አመል ነቄ ብለው የለ? “ግድ የለም አንድ ብር እሰጠዋለሁ። ሁልጊዜ አንድ ብር እየሰጠሁት ነው አፉን የማዘጋው” ብላላችሁ እርፍ። . . . እኛ ታዲያ ከደረቀ ኪሳችን ከየት አምጥተን ነው ጉዳይ ለማስፈፀም አፍ መዝጊያ የምናስነክሰው ጎበዝ? እናችሁ ዘንድሮ “እከክልኝ -ልከክልህ” ይሉት ነገር ሁሉ መስመሩን ስቶ “ጉዳይ መግደያ” ከሆነ ሰነባብቷል። እናም በየቦታው፣ በየቢሮውና በየመስኩ በብዛት ልክ እንደ “ጆተኒ” ሳንቲም ካልጎረሱ መረጃ እንኳን የማይተነፍሱ ሰዎች ሊያጋጥሟችሁ ይችላሉ። እኔ የምለው እኛ ባስተማርናቸው ፊርማና እኛ ባስጠናናቸው ማህተም መልሰው የሚያንከራትቱን “የህዝብ አገልጋይ” ተብዬዎች ግን ልባቸው ስንት ነው?

በእጅ መንሻ፣ በመጎራረስ፣ ሳንቲም በማስነከስ፣ በኔትዎርክ በመስራትና በሙስና ጉዳይ ደረጃችን የከፋ እንደሆነ ተስፋ ያስቆረጡን እኮ የቀድሞው ጠቅላያችን ናቸው። . . . ሰምታችኋል አይደል የሙስና ትግሉን አንድ እጃችንን ታስረን እያካሄድነው መሆኑን?. . . እሳቸው በደህናው ጊዜ አንድ እጅ ታስረው ነው ያዩት ይኸውና አሁን እኮ ነገራችሁ ሁሉ ተተብትቧል። (አንድዬ ይፍታን አቦ?) . . . እናላችሁ እንኳን ግማሹን አስሮ እና ግማሹን ሰብሮ ይቅርና በሙሉ ሃይላችን እንኳን እንጃልን የሚያስብለን ደረጃ ላይ ሳይደረስ አልቀረም። (ያም ሆኖ ተስፋ አንቆጥ አይደል?. . . በገጣሚ ሰለሞን ሞገስ “እንዘራን ገና” ስንል እንደሚከተለው እንፎክራን።

እንዘራለን ገና

አርሰን አለስልሰን ካቻምና ዘር ዘራን

ምንም አልበቀለ ጥቂትም አልበላን

አምና አብቅለን ነበር ፍሬ የያዘ ዘር

ችጋራም አንበጣ እንዲያ በልቶት ባይቀር

ዘንድሮም ያው ዘራን ለአገር እንዲበጅ

እንደአምና ካቻምናው አልበቀለም እንጂ

ይሁን መቼስ ይሁን ኪዳን አለንና

በተስፋ እንዘራለን ለከርሞ እንደገና።

እስቲ ደግሞ ለዛሬ ትዝብታችንን ከመቋጨታችን በፊት የኃላፊነት ሽሽትን ከምታሳየን የሙላህ ነስሩዲን ወጎች አንዷን ላስታውሳችሁ።. . .  የኑስሩዲን ሚስት ከዘጠኝ ወር እርግዝና በኋላ በምጥ ላብ ተዘፍቃ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ተገላገለች። ታዲያ ከቀናት በኋላ አንድ ምሽት ላይ ነስሩዲን ስራ ውሎ በማረፊያው ሰዓት ላይ ህጻኑ ማልቀስ ጀመረ። ከጎኑ ተኝታ የነበረችው ባለቤቱ ወደሙላህ ዞር ብላ፣ “ነስሩዲን እስቲ ይሄን ልጅ አባብለው። ቀኑን ሙሉ እርሱን ሳጥብ፤ ሳጠባና ስንከባከበው ነው የዋኩት፤ ልጅነቱ የሁለታችንም በመሆኑ አንተም ልትንከባከበው ይገባልና እስቲ ሂድና አባብለው” ብትለው መልሱ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? “የኔ ውድ ከቻልሽ ተነሽና አንቺ አባብይው፤ ካልሆነ መጀመሪያ ያንቺን ግማሽ ኃላፊነት በማባበል ተባበሪኝ የኔን ግማሽ ደግሞ ተይው ያልቅሰው” ብሎላችሁ እርፍ. . . ይህቺ ናት ጨዋታ አትሉም።

እናላችሁ ኃላፊነታችንን እየሸሸን፤ መፈፀም የሚገባንን ተግባር ከመፈፀም ይልቅ “እጅ መንሻ” ስንጠብቅ ሰውኛ ባህሪያችንና ተምረን ህዝብን ለማገልገል የጨበጥውን ወንበር ሁሉ ልክ እንደ “ጆተኒ” ሳንቲም መንከሻ ካደረግነው ምን ዋጋ አለው? . . . ጎበዝ በመነሻችን እንደጠቀስነው ተረት፤ “አፋችን ዝም ብሎ በእጃችን የሚጎራረሱ” ከበዙ ምሬቱና መዘዙ ብዙ ነውና ብንከባበር ምን ይለናል? ምንም። አንድዬን ብቻ ጉዳይ ገዳይ እንጂ እኛን ገዳይ ወንበርተኞች እንዳይበረክቱ ያደርግልን ዘንድ በፆም በፀሎት እንማፀነዋለን። ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
725 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 892 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us