“ይውጋህ ብሎ ይማርህ”

Wednesday, 16 March 2016 13:32

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?…. እኔ የምለው ያቺ የ28 ዓመት ወጣት መንግስትን ፍትህ አሳጣኝ በሚል ክስ መስርታበት በአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት በኩል የ150 ሺህ ዶላር የሞራል ካሳ አስቀጣችውም አይደል? . . . ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም እኮ! (እኔ የምለው መንግስታችን እንደው መቅጣት እንጂ መቀጣት አያወቅበትም፤ ፍርዱ እንዴት አድርጎት ይሆን. . . ቂ.ቂ.ቂ.! የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት ግን በነካ እጁ እኛም ብዙ ጊዜ በብዙ ነገር በመንግስታችን ተደፍረናልና ካሳ ያሰጠን አቦ)

እህሳ የፓርላማውን ይቅርታ እንዴት አያችሁት?. . . መንግስትችን ልብ ገዝቶ ይሁን ተውሶ በውል የታወቀ ነገር የለም፤ ብቻ በደፈናው ይቅርታ ብሎናል። ለማንኛውም ይቅርታው የይስሙላ ሆኖ እንዳይቀር ያስፈልጋል።. . .  አልያ ግን ነገሩ ሁሉ ለይስሙላ ብቻ ከሆነ ተዳፍኖ ይቆያል እንጂ መቆስቆሱ አይቀርም። ያኔ እንደሚከተለው አንቺም ባሻሽ ሂጂ የሚያሰኝ ቅኔን እንቀኛለን፡-

ዘወትር ፀጉርሽን ከምታቆነጂ

እኔ ባርኔጣ አለኝ አንችም በሻሽ ሂጂ።

(እንዲሉ ባለቅኔዎች)

ለማንኛውም ግን የልባችንን ከሰራን በኋላ አለ አይደል “ይውጋህ ብሎ ይማርህ” አይነት ነገር ባይለመድ ምን ይለናል? የምሬን እኮ ነው፤ የተመረዘ ምግብ አቅርቦ ብሉልኝ፤ የተመረዘ መጠጥ አቅርቦ ጠጡልኝ፣ የተቃጠለ አምፖል ሰጥቶ አብሩልኝ፤ የጎበዝን እግር ሰብሮ ድረሱልኝ፤ ያላስተማሩትን ልጅ መርቁልኝ፤ የማይፈጽሙትን ሕግ ፈፅሙልኝ እንደማለት ምን የሚደብር ነገር አለ?. . . ካለም ይውጋህ ብሎ ይማርህ እንደማለት ይቆጠራል። 

ዘንድሮ ወዳጄ ሰው ሁሉ የልቡን ሰርቶ፤ በሰው ቤት ገብቶ፤ በልቶና ጠጥቶ ወጭት ሰባሪ ከሆነ ቆይቷል።. . . እዚህች’ጋ ጨዋታ እናምጣ፤ ሰውዬው በወተት ንግድ ተሰማርቶ ኗሪ ነው። አዲስ ሰራተኛ ቀጥሮ ስያበቃ የታለበውን ትኩስ ወተት እና በውሃ የተሞላ እንስራ አስቀምጦ ትእዛዝ ይሰጥ ጀመር። “ዘወትር ማድረግ ያለብህ አንድ ነገር አለ። ይኸውም መጀመርያ ወተት የምትሸጥበትን እንስራ በውሃ ታጋምሰዋለህ፤ ከዚያም በውሃው ላይ ትኩሱን ወተት ጨምረህ ትቀላቅለውና ትሸጠዋለህ” በአለቃው ትእዛዝ የተገረመው አዲሱ ሰራተኛውም፤ “ጌታዬ ለምንድነው መጀመሪያ ውሃ ከዚያ ደግሞ ወተቱን የምጨምረው?” ሲል ጠየቀ። . . . አለቅዬው በየዋህ ጥያቄው ፈገግ እንደማለት እየቃጣው  ምን ቢለው ጥሩ ነው? “ለደንበኞቻችን በምንም አይነት ቢሆን በወተት ላይ ውሃ እንደማንጨምር ምለህ መናገር ስላለብህ ነዋ!” ብሎላችሁ እርፍ ቂቂቂ!!! ይህቺ ናት ጨዋታ አትሉልኝም?!

እንግዲህ ዘመናችን እንዲህ ነገር ማገላለጥ ሆኗል። “ይውጋህ ብሎ ይማርህ” ባዩ በዝቷል ጎበዝ! ጫት አቅራቢው “ይውጋህ ብሎ ይማርህ” ባይ ነው። ሲጋራ አቅራቢው “ይውጋህ ብሎ ይማርህ” ባይ ነው። ባለግሮሰሪው “ይውጋህ ብሎ ይማርህ” ባይ ነው። ከመድሃኒት ሻጩ አንፃር እንኳን “ይውጋህ ብሎ ይማርህ” ባዩ ብዙ ነው። እናም በፍየል ዘመን ስንቶቻችን በግ ሆነን በተኩላዎች ተበልተናል መሰላችሁ።

እናላችሁ የዘንድሮ ጉዳያችን ሁሉ “ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም” እየተባባልን ቤታችንንም ስንዘረፍ የምናይበት ጊዜ ላይ መጣን።. . . የምሬን እኮ ነው፤ አልሰማችሁም እንዴ? የአዲስ አበባ አስተዳደር የቤቶች ልማት ኤጀንሲ 60 የጋራ መኖርያ ቤቶች ቁልፋቸው ተገንጥሎ በግለሰቦች ቁጥጥር ስር መሰንበታቸውን እንደተናገረ። ከዚህ በላይ ድፍረት ከየት ይምጣ? (ማነህ ወዳጄ . . . “በራቸውን ከፍተው ሰውን ሌባ ነው ይላሉ” ያልካት ነገር ተመችታኛለች)

እኚያ ሰውዬ እኮ እንዲህ አይነት አይን ያወጣ ነገር ሲገጥማቸው ነው፤ “ጎበዝ ንቀውናል! ደፍረውናል፤ ብታምኑም ባታምኑም በቁማችን ቀብረውናል!” ያሉት። እናላችሁ እኛን መስለው ኮሜቴ መስለው፤ አስተናጋጅ መስለው፤ ደላላ መስለው ሲያበቁ አለ አይደል በልባቸው፤ “ይውጋህ!” እያሉ በአፋቸው “ይማርህ!” የሚሉን አስመሳዮች ከላይ እስከታች ወረውናል። አንድዬ ብቻ መገላገያውን ያምጣልን አቦ!

እስኪ አሁን ማን ይሙት ህዝቤ የምርጫ ካርዱን “በተስፋ ቤቱ” ተማምኖ ባወራረደበት “ኮንዶሚኒየም” ውስጥ፤ መንግስት አይዟችሁ በትእግስት ጠብቁ እያለ እንደህፃን በሚያባብለን “ኮንዶሚኒየም” ውስጥ እንዲህ ያለ ብልግና ሲፈፀም ኧረ ጎበዝ የት ደርሰናል? መባባል ያንሰናል። ለማንኛውም አንድዬ በልቡ “ይወጋህ” እያለ በአፉ “ይማርህ” ከሚል አስመሳይ ኮሜቴ፣ ጎረቤት፣ ጓደኛ እና አስተዳደር ይጠብቀን። ቸር እንስንብት!!! 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
708 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 920 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us