ግንዱን ፍለጋ

Wednesday, 30 March 2016 12:05

 

እነሆ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ቀራፊው ፊሽካ ተነፍቷል ተብለናል። እሰይ እንኳንም ተነፋ!.. ቢያንስ የጠገበው ጅብ ሄዶ የራበው እስኪመጣ ተንፈስ እንል ይሆናል!... የፊሽካውን መነፋት ተከትሎ የከተማ አስተዳደሮች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎች፣ መ/ቤቶች በግምገማ ተወጥረዋል፣ ተወጣጥረዋልም። ግምገማ በአንዳንድ የኢህአዴግ ሰዎች አጠራር አውጫጪኝ በጎም፣ መጥፎም ጎን አለው። ጥሩ ጎኑ፣ ጥሩ ያልሆኑ፣ በኃላፊነታቸው የነቀዙ ሰዎችን እየመዘዙ ማስወገድ መቻሉ ነው። ድክመቱ ደግሞ ግምገማው በብልጣብልጦች ሀይጃክ ተደርጎ ንጹሃንን ለመጉጃነት የሚውልበት የሚታወቅ አሠራር መኖሩ ነው። በዚህ መሠረት በግምገማ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጣሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ተዋጊዎችም የመባረር ዕጣ ፈንታ ሊደርሳቸው የሚችልበት ዕድል ዝግ አይደለም። ለምን ሲባል ግምገማ ማለት በዚህም በዚያም ብሎ የተሰብሳቢውን ድጋፍ ማግኘት መቻል ነውና!..በቃ በኢህአዴግ ግምገማ ሰዎች ተደራጅተው ገብተው፣ ያልተደራጁ ንጹሃንን ሲያራግፉ ኖረዋል። ምን መኖር ብቻ ብልጣብልጦቹ ንጹሃንን እያሸማቀቁ ኪሳቸውን አደልበዋል። እናም ጎርፉ ንጹሃንንም ይዞ እንደሚነጉድ ሳይታለም የተፈታ ነው። በአንጻሩ አሁንም ሌቦቹ ወንበሩን፣ መድረኩን ይዘው ስለመልካም አስተዳደር ጎጂነት ይሰብካሉ። ምዕመናኑም ይህን ሁሉ እያየ፣ እየታዘበ ዝም ብሏል። ሰባኪዎቹ ቀጥለዋል፣ «የመልካም አስተዳደር ችግር የስርዓታችን አደጋ ነው፣ ችግሩ ያለው ውስጣችን ነው….» የሚሉ የተሰለቹ ዜማዎች እዚህም እዚያም እየተሰሙ ነው።

 

«ምንም ጠንካራ ብትሆን የምትሸነፍበትን ጦርነት አትጀምር» ይላል ህንዳዊው ፈላስፋ ሮቢንዶ። እውነቱን ነው፤ ኢህአዴግ እስከአንገቱ ድረስ የተዘፈቀበትን የመልካም አስተዳደር ችግር እቀርፋለሁ ብሎ ያሳየው ጅምር የቆሰለን አካል ከማከም ይልቅ መነካካት ይመስላል። “ግንዱንም ቅርንጫፉንም እኩል ገንድሶ የመጣል አቅም አለው ወይ?” የሚለውን ተደጋጋሚ ጥያቄ በተግባር መመለስ የሚችል አይመስልም። የታችኞቹ አመራሮች ሕዝብ ማንገላታትን፣ የአገልጋይነት መንፈስ ማጣትን፣ ሌብነት ውስጥ መዘፈቅን (ክሊፕቶክራት) ከየት አመጡት ብሎ እየጠየቀ አይደለም። እንዴት የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሥርዓት ችግር ሆኖ ገዝፎ ሊቀመጥ ቻለ ብሎ ሲጠይቅም አልተሰማም። ያባረርኩዋቸው ሰዎች ሐረጋቸው ተጥመልምሎ የት ይደርሳል? ሥር መሠረታቸው ከየት ይመዘዛል? ብሎ ለመጠየቅ፣ ለመፈተሽ መድከም አልፈለገም። እናም ይህን ሳይመልስ ሰዶ ማሳደድ ውስጥ ገባ። «እያስመዘገብኩኝ ነው» እንዳለው ደራሲ እየተሯሯጠም በየዕለቱ 100፣ 200፣ 300… ሰዎች ተባረሩ የሚሉ ቁጥሮችን ማስመዝገብ ላይ የሙጢኝ ብሏል። አሁንም ሕዝቡ የሚሆነውን ዝም ብሎ እየታዘበ፣ እየተመለከተ ነው። ሕዝብ ዝም ሲል ኦሜርታ ይባላል። ኦ… ኦሜርታ!!

 

የአዲስአበባ አስተዳዳር ባለፉት 12 ዓመታት የገነባቸው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ቁጥራቸውን በትክክል አያውቀውም ስንባል ተገርመን ነበር። ቤቶቹን ማን እንዴት እንደሚኖርባቸውም አያውቀውም በመባሉም ምንተእፍረቱን ቆጠራ ላካሂድ ብሎ ተነሳ። የቆጠራው ውጤት ከ1 ሺ 200 በላይ ቤቶች ተዘግተው መገኘታቸውን አሳየ። ከ96 በላይ ቤቶች በህገወጥ መንገድ ተይዘው ተደረሰባቸው። ይሄኔ አስተዳደሩ «በህገወጥ መንገድ ቤቶቹን ሲጠቀሙ የነበሩ ግለሰቦች እየያዝኩኝ ነው» ብሎ ቴሌቪዥን መስኮት ላይ ወጣ። መቼም እየቀለደ መሆን አለበት። ማን ይሙት!.. የሚያስተዳድረውን መኖሪያ ቤት ወይንም የተሰጠውን ኃላፊነት በትክክል አውቆ መሥራት የተሳነው አመራር እግሩን ቢሮው ውስጥ አንፈራጦ፣ እሱ በፈጠረው ክፍተት ለመጠቀም የሞከሩ ግለሰቦችን ሰዶ ማሳደዱ ኮሚክ ነገር አለው። በሰለጠኑት ሀገሮች ቢሆን የከተማውም ከንቲባ ጭምር ከሥራ የሚያስባርር ወይንም በራሱ ፈቃድ ከኃላፊነት የሚያስለቅቅ ከባድ ኃላፊነትን የመሳት ችግር ነው። ምን ይህ ብቻ፤  በመንግሥታችን ቋንቋ ግልጽ ኪራይ ሰብሳቢነትም ነው። ግን ሀገሩ ኢትዮጵያ ነውና ሕገወጥ አሠራርን የፈቀዱ፣ ችግሩንም በወቅቱ ያልታገሉ አመራሮች ዛሬ አንገታቸውን ቀና አድርገው ገምጋሚና አስገምጋሚ፣ ቀጪና አስቀጪ ሆነው እያየናቸው ነው። የጉድ ሀገር!

 

ገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቶች ሂድና ተመልከት። ሰዎች ገንዘብ ይዘው ግብር ለመክፈል መንገላታት ብቻ ሳይሆን የያዙትንም ገንዘብ በጥቃቅን ሰበብ አስባብ ይዘው እንዲመለሱ ሲገደዱ ታያለህ። ግብር ልክፈል ባሉ ወንበር በያዙ ጋጠወጦች መንጓጠጥ፣ መዘለፍ ይደርስባቸዋል። ይህ አሠራር ያልቆረቆረው፣ ይህን ቤቱ ውስጥ ያለ ችግር ያልፈታ አመራር በየዕለቱ ህዝብ ግብር በሚከፍልበት መገናኛ ብዙሃን የአየር ሰዓት ጭምር እየወጣ «ችግራችን የመልካም አስተዳደር ነው…» ይልሃል። አቦ!... እንዲህ ዓይነት ቅጥፈት እንዴት ይሰለቻል?!

 

ከመልካም አስተዳደር ዋና ዋና መገለጫዎች መካከል ጉቦ (Bribery)፣ ምዝበራ (Embezzlement)፣ ማጭበርበር (Fraud)፣ በዝምድናና በትውውቅ አድልኦ መፈጸም (Favoritism, Nepotism) በአጠቃላይ ሙስና ጣራ የነካበት ወቅት ላይ እንገኛለን። አዩኝ አላዩኝ ተብሎ የሚሰረቅበት ዘመን አልፎ ዓይን ያወጣው ዘመን ከገባ ቆይቷል። ዛሬ ሌቦቹ «ባለሀብት» የሚል የወግ ማእረግ ካባ ለራሳቸው ደርበው በአደባባይ ውለዋል። ሕዝብ ዝም ብሎ እያየ፣ እየታዘበ ነው። መንግሥትስ?! እንጃ ማን ያውቃል!... አንድ ቀን!... ቢያንስ ለራሱ ሲል ወደግንዱ የመጠጋት አቅም ይፈጥር ይሆናል። አዎ!... ማን ያውቃል!!n

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
623 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 941 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us