የፖለቲከኞቻችን ነገር

Wednesday, 06 April 2016 12:28

 

 

ከጋዜጠኛ ወዳጄ ጋር ሻይ ቡና ቢጤ እየቀማመስን በነበረበት ሰዓት በድንገት ራሳችንን የፖለቲካ ወግ ጥረቃ “ጎላ” ውስጥ ጥደን አገኘነው። ያው ኑሮአችንም፣ ውሎአችንም ፖለቲካ ነውና ማውራታችን፣ መቦጨቃችን እንተወውም ብንል የሚተው አይደለም።

ከወዳጄ ጋር የጀመርነው ፍተላ እንደአጋጣሚ የአገር ቤት ተቃዋሚ ፖለቲከኞቻችንን የሚነካካ ነበር። በተለያዩ ምድቦች ሽንሽነን ቃኝተናቸዋል። የቀረ ምድብ ካለ እርስዎ ሊያክሉበት ይችላሉ።

የመጀመሪያዎቹ፡-

ይህ ምድብ የፖለቲካ ፓርቲን እንደቢዝነስ አይተውት የተጠጉትን የያዘ ነው። መነሻቸውም፣ ግባቸውም ቢዝነስ (ጥቅም) ብቻ ነው። ብዙውን ጊዜ የራሴ የሚሉት ቢሮ ወይም አድራሻ የላቸውም። ውስጣቸው ሲፈተሸም የሚገኙት አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ናቸው። ግን ቢዝነሳሞች ናቸውና መንገዱን ያውቁበታል። ለምሳሌ በአገር አቀፍ ምርጫ በቀረቡ ዕጩዎችና ሴት ዕጩዎች ብዛት የፋይናንስ ድጎማ እንደሚሰጥ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ በሚገርም ሁኔታ የተሻለ አደረጃጀት አለን ከሚሉት በላይ ዕጩዎችን በየመንደሩ እየዞሩ እንደሸቀጥ ገዝተው ምርጫ ቦርድ ወስደው ያስመዘግባሉ።

ገዥውን ፓርቲ ለማስደሰት እጣንና ከርቤ እያጤሱ ይዘው የሚቆሙ ዓይነቶች ናቸው። እንደ ዋንጫ ከወደአፋቸው ሰፋ ያሉ ናቸው። ምርጫው ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መልኩ እየሄደ መሆኑን በኋላም በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁን ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው፣በሕዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ ሲናገሩ ውስጣቸውን የማያውቅ የዋህን በሚገባ ይሸውዳሉ።

ሁለተኛዎቹ፡-

በአመዛኙ የሐብታም ጡረተኞች፣ የትርፍ ሰዓት ፖለቲከኞችና ጥቂት ምሁራን መሰባሰቢያ ናቸው። ሰዎቹ አንዳንዴ ፖለቲካውን እንደጊዜ ማሳለፊያ የሚጠቀሙበት በመሆኑ ከገዥው ፓርቲ ጋር ያላቸው ግንኙነት በከባድ ጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ ነው። ብዙዎቹ ተቃዋሚዎች ቢሆኑም ዋጋ የሚያስከፍል ነገር ውስጥ ላለመግባት ይጠነቀቃሉ፤እንዲህ ዓይነት ነገር ከመጣም ቶሎ የመውጪያ ስትራቴጂ ነድፈው የሚተገብሩ ናቸው።

ሥልጣን የሙጢኝ የሚሉ ዓይነት በመሆናቸው ብዙም ወጣት ተከታዮችን ሲያፈሩና ሥልጣን ሲያጋሩ አይታዩም። የእነዚህኛዎቹ የዘወትር መፈክር “እጅህን ባህር ውስጥ ክተት፤ ብታገኝ ዓሳ ይዘህ ትወጣለህ፤ ባታገኝ ታጥበህ ትወጣለህ” እንደሚባለው ጥቅማቸውን ያሰላ ጨዋታን የሚያበረታቱ ናቸው። ሐብታሞቹ ፖለቲከኞች ለፓርቲያቸው ድጎማ ለመስጠት ኣይናቸውን አያሹም። ግን ካፈሰሱት ገንዘብ ጋር ያልተመጣጠነ ጥቅምን መጋራት የሚሹ ናቸው። ለፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ ገንዘብ ሲሰጡ ጉባዔው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥረው፣ ያሹትን ተናግረው፣ ያሹትን ሾመውና ሽረው፣ ያለምንም ማቅማማት ይመረጡበታል። የስልጣን ጥማታቸው የፓርቲ ወንበር ላይ እስከመጣበቅ እንዳደረሳቸው የተረዱ ወገኖች “ሰዎቹ የምር ሥልጣን ቢይዙ ምን ይውጠናል” ሲሉ ይሰጋሉ።    

ሦስተኛዎቹ፡-

በቁጥር እጅግ ጥቂት ቢሆኑም ከምሥረታቸው ጀምሮ እውነተኛ አገራዊ ስሜትና ቁጭት የሚታይባቸው ናቸው። በሰላማዊ ትግል፣በምርጫ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለው ትግል የጀመሩ ናቸው። አንጻራዊ በሆነ መልኩ የእኔ የሚሏቸው አባላት ያሏቸው ናቸው። የሚያሳዝነው በተራ ቁጥር አንድና ሁለት በተጠቀሱት ፓርቲዎች የሚጠሉና ሁሌም የሚወገዙ መሆናቸው ነው።

የአገሪቱ ችግርም ይህ ነው። አስመሳዩ እና ጉልበተኛው እውነተኛውን መደፍጠጡ። እንደዚህ አይነቱን ሳይሆን ይቀራል ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ፡-

“ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ

የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” ሲል የተቀኘው።

እኔና ወዳጄንም በሻይ ቡና ተጀምሮ ወደ ፖለቲካ ፍተላ የወሰደን ጉዳይ ይህ ነው። አንድዬ በማያልቀው ቸርነቱ ከአስመሳዮች፣ ከሆድ አምላኪዎች፣ ከወንበር ወዳጆች…. ይሰውረን አቦ!... ቸር እንሰንብት!!n

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
604 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1068 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us