የእሳት እቁብ

Wednesday, 13 April 2016 12:26

 

እንደምን ከረማችሁ ወዳጆቼ!?. . . አንዲት አባቶች የሚተርቷት ተረት ሁሌ ፈገግ ታሰኘኛለች። “የሰራ የእጁን የተቀመጠ የመቀመጫውን ያገኛል” ይሉናል። እውነት ነው በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም። እስቲ ደግሞ የዛሬውን ትዝብት አዘል ጨዋታ ከክብር ዶክተር ከበደ ሚካኤል “የቅኔ ውበት” የምትከተለው ቅንጫቢ የግጥም አንጓ እንደርድርባት፤

ባለም ላለው ሁሉ በድምር በሞላ

አንድም ነገር ሳይቀር ፍጡር በጠቅላላ

ለነፍስ ለእንስሳ ለዕፅዋት ለድንጋይ

ለውሃ ለኮከብ ላየርም ለሰማይ

ለምናየው ሁሉ በዚች በመሬት ላይ

የሰው ልጅ ጌታ ነው ባለቤት ነው መሪ

እሱ ነው አላፊ ህግጋትን ሰሪ።

አንድዬ በዚህች ምድር ላይ የሰውን ልጅ ጌታ አድርጎ ሾሞታል። አንዳንዶች ግን ጌትነታቸውን ከበጎነት ይልቅ ለክፋት፤ ከአጉራሽነት ይልቅ ለመብላት፤ ከታማኝነት ይልቅ ለክህደት፤ ከታጋሽነት ይልቅ ለቁጡነት፤ ከፅድቅ ተግባር ይልቅ ለኩነኔ እየተጠቀሙበት ለላይኛው ቤታቸው እሳት ያጠራቅሙበታል። ድምፃዊ ይሁኔ በላይም በአንድ እንጉርጉሮው ውስጥ ይህንኑ ሃሳብ ለመግለፅ፤ በምድር የሰራነው ስራ በሰማይ ፍርድ እንደሚያሰጠን ሲጠቁም እንዲህ ይላል፡-

ማን ይጎዳ ብለሽ በኔ ወድቆ መቅረት

የታቹን አይቶ ነው የላይ ቤቱ ምህረት።

የላይ ቤታችን እና በምድር ጌትነታችን ሲታሰብ አንድ የመካከለኛው ምስራቅ ታሪክ ትውስ ይለኛል። ይህን ታሪክ ያገኘሁት ጲላጦስ ከፃፈው “ጥበብ አንድ” መፅሐፍ ላይ ነው።

ጠቢቡ ሞኝ ባህሉል በመንገድ ላይ ከሀሩን አል-ራቪድ ጋር ይገናኝና ከየት እንደሚመጣ ይጠይቁታል። ባህሉልም፣ “ገሃነም ደርሼ እየተመለስኩ ነው” አላቸው።

በባህሉል መልስ የተገረሙት ሀሩን፣ “ገሃነም የሚወስድ ምን ጉዳይ አጋጥሞህ ነው?” አሉት። ባህሉልም፣ “እሳት አስፈልጎኝ ትንሽ ለመጠየቅ ብሔድ የገሀንም አለቃ እዚህ እሳት የለም በማለት መለሰኝ” አላቸው። ሀሩንም በመገረም፣ “ቦታ ተሳስተህ ካልሆነ በቀር እንዴት ገሃነም ሄደህ እሳት የለም ትባላለህ?” አሉት። ባህሉልም፣ “እርግጠኛ ነኝ ጌታዬ! በገሃነም እሳት የለም። ነገር ግን ወደዚያ የሚሄድ እያንዳንዱ ሰው የራሱን እሳት እየያዘ ነው የሚገባው” አላቸው ይባላል።

እናላችሁ እዚህ በቤታችን፣ በመንደራችን፣ በቀበሌያች፣ በወረዳችን፣ በክፍለከተማችን በዞናችን፣ በክልላችንና በአገራችን የምንሰራት እያንዳንዷ መጥፎ ተግባር ለገሃነም የእሳት ዕቁብ ተቀማጭ እንደምትሆን ልብ እንበል። በምድር የምንሰራው ክፉ ተግባር ሁሉ ለገሃነም የምንጥለው የእሣት እቁብ እንደሆነ እና ከህይወት ስናልፍ የምናገኘው መንገብገብ መሆኑን ስናስብ መልካምነት ምን ይለናል? ያስብለናል። ወይም ደግሞ ባለቅኔው ከበደ ሚካኤል እንዳሉት፡-

ጽድቅና ከኑኔ ቢኖርም ባይኖርም

ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም።

በግልም ቢሆን በአንድዬ ከክፋት ደግነትን የሚሰራ ልቦና ይስጠኝ አቦ! . . . ወዳጅ በወዳጁ ላይ፤ ሚስት በባሏ ላይ፣ ባልም በሚስቱ ላይ፤ ሀኪም በበሽተኛው ላይ፤ ጉዳይ አስፈፃሚው በባለጉዳዩ ላይ፤ መሪ በሚመራው ላይ፤ አለቃ በሎሌው ላይ የሚፈፅመውን ግፍ ሁሉ እየተጠራቀመ ለገሃነም እሳት እቁብ እየጣሉ ነው ማለት ትችላላችሁ።

እናላችሁ አንዳንዴ ለሌላ ሰው የታዘዘ የመሰለን መድሃኒት ለኛ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ችግር ፈጣሪው ሌላ ነው ብለን ባሰብንበት ሰዓት ማን ያውቃል ችግር ፈጣሪዎቹ እኛው ሆነን ብንገኝስ?. . . እንካችሁ እስቲ አንዲት ጨዋታ፤ በሚስቱ ጭቅጭቅ በእጅጉ የተማረረው ባል የቤተሰቡ ሀኪም ዘንድ ሄዶ መፍትሔ ይጠይቃል። ሰውየው ተመራማሪ፣ አንባቢና ፀሐፊ መሆኑን በሚገባ የሚያውቀው ሀኪሙ አንድ ዘዴ መጣለትና በሚከተለው ቀን ወደሰውዬው ሚስት ስልክ ደውሎ እንድትመጣ ቀጠሮ ሰጣት። ሚስትም የቤተሰቡ ሀኪም እንዲህ የፈለጋት ለምን እንደሆነ ባይገባትም በተሰጣት ቀጠሮ ሀኪሙ ቢሮ ተገኘች። እንደገባችም ብዙ ነገር መጠየቅና ብዙ ነገር መለፍለፍ ጀመረች። ይሄኔ ሀኪሙ የትዳሩ ችግርና የባልየው ጭንቀት የሴትየዋ ለፍላፊነት መሆኑን ተረድቶ ነበርና እንዲህ አላት፣ “ባለቤትሽ ፍፁም የሆነ ፀጥታ ስለሚያስፈልገው እነዚህን የእንቅልፍ ኪኒኖች ይዘሽ መሄድ አለብሽ”። ሀኪሙ ተናግሮ እንደጨረሰ ሚስት ፈጠን ብላ፣ “ዶክተር መድሃኒቱን በምን ሰዓት ላይ ነው የምሰጠው?” ስትል ጠየቀችው። ይሄኔ ሀኪሙ ምን ቢላት ጥሩ ነው? “ኪኒኖቹን የምትወስጂው አንቺ ነሽ እኮ እመቤቴ!” ብሎላችሁ እርፍ።

“ለሆዳም በሬ ጭድ ያዝለታል” ይሉትን ተረት አስታውሳችሁ አይደል?. . . ስለሌሎች ያሰብነው መድሃኒት ለኛም እንደሚያስፈልገን ብናውቅ ኖሮ ለክፋት የምናቆየውን የገሃነም እሳት እንቀንሰው ነበር። አንድዬ ብቻ ከክፋታችን ብዛት ለሰማይ ቤታችን የእሳት እቁብ ከማግባት ይሰውረን አቦ! ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
778 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1084 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us