“በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ”

Wednesday, 20 April 2016 13:25

      አፌ አልተናገረ በጆሮዬ አልሰማሁ፣

እንዲያው ታሰርኩና በወሬ ተፈታሁ።

            (እንዲል ባለቅኔ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . እህሳ ሰሞኑን የገጠመን ሀዘን ቁጭቱ አንገብግቦ ሊገለንም አይደል?. . . እኔ የምለው በዚህ ጊዜ እንኳን ከዛቻና ማስፈራሪያ በዘለለ ከእኛ የተረፈ ዱላ ጠላት ላይ ማሳረፍ ያልተቻለው ስለምንድው? የሚል ጥያቄ አይመጣባችሁም እውነቴን እኮ ነው፤ “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” ይሉትን ተረት የሚያስተርት አጋጣሚ በጋምቤላ በሚኖሩ ዜጎቻችንን ላይ ተከስቷል። ምንም እንኳን ያጣናቸውን ነፍሶች ባንመልስ፤ እንባችንን የሚያብስና ቁጭታችንን የሚያስታግስ የአፀፋ ምላሽ እንደምንሰማ ተስፋ አለን። ለማንኛውም ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን አንድዬ ነፍሳቸውን ይማር ብለናል።

እናላችሁ ለዛሬ ትዝብት አዘል ጨዋታችን የተመረጠው ሃሳብ፣ “በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ” ይሉትን አገረኛ ተረት የሚያስታውሰን ነው። ባለቅኔው እንዳለው አንዳንዴ ሳንናገርም ሳንሰማም ታስረን በወራችን ልንፈታ የምንችልበት አጋጣሚ እየበዛ ነውና ለአጣሪው አካል ጥቆማ ይሆን ዘንድ በድጋሚ የምትከተለዋን ቅኔ እንቀኛለን።

አፌ አልተናገረ በጆሮዬ አልሰማሁ፣

እንዲያው ታሰርኩና በወሬ ተፈታሁ።

እንደው ግን አለ አይደል አንዳንድ ሰው ዝም ብሎ ሲቀደድ፣ “አፍ ሲያመልጥ፣ ራስ ሲመለጥ አይታወቅም” መባልን ያስታውሰናል። ታክሲ ውስጥ ምን የምትል ፅሁፍ አነበብኩ መሰላችሁ፣ “ምላስ አጥንት የለውም፤ ነገር ግን አጥንት ይሰብራል” ከባድ አባባል ናት። እውነቱን ለመናገር ሰው በንግግር ይድናል፣ በንግግር ደግሞ ይታመማል። ያም ሆኖ ይህ ምላስ ለክፉም ለደጉም መዋል የሚችል ጦር መሳሪያ እንደሆነ ልብ ይባልልን።

እስቲ ደግሞ ከምላስ መዳለጥ የተረፉ ሰዎችን ጨዋታ እንምዘዝ። . . . አመታዊ ትርፉ ያደገለት አንድ ኩባንያ ለሰራተኞቹ የሚሆን ትልቅ ድግስ ያዘጋጃል። በድግሱም ላይ አንድ ወጣት ደስ ካለችው መልከመልካም ሴት ጋር ዳንስ ይጀምራል። በዳንሳቸው መካከልም ወደጆሮዋ ጠጋ ብሎ፣ “በነገራችን ላይ ያ ደደብ አለቃችን እዚህ ባለመኖሩ ደስተኛ ነኝ። በህይወቴ እንደርሱ ያለ ክፉ እና አስቀያሚ ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም።” ይላታል። ይሄን ጊዜ በነገሩ የተገረመችው ሴት፣ ኮስተር እንደማለት እየቃጣት፤ “ለመሆኑ እኔ ማን እንደሆንኩ አውቀሃል?” ስትል ትጠይቀዋለች። “ኧረ በፍፁም አላወኩሽም” ወጣቱ ይመልሳል።

“እኔ ማለት የአለቃህ ሚስት ነኝ” ብላላችሁ እርፍ፤ ወጣቱ መሬት ተቀዳ ብትውጠው ደስ ባለው ፤ ዳሩ ግን አንድ መላ መጣለት። “አንቺስ እኔ ማን እንደሆንኩ አውቀሻል?” ሲል ጠየቃት። እንዳላወቀችው ስትመልስለት፤ ምን ቢላት ጥሩ ነው? “እድለኛ ነህ በይኛ በይ ደህና ሁኚ” ብሎላችሁ ከድግሱ ተሰወረ። (በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ ማለት እንዲህ ነው። ቂ-ቂ-ቂ!

አንዳንዴ ሳስበው “አፍ ዳገት የለውም” ማለት እውነት ነው። በአፍ ትንሹን ትልቅ፤ ትልቁን ደግሞ ትንሽ የሚያደርጉ ስንት ጉደኞች አለላችሁ እኮ። አንድዬ ብቻ ከክፉ ዘርጣጮች ይጠብቀን። አንዳንዱ ደግሞ አለላችሁ ከሜዳ ተነስቶ ተናግሮ የሚያናግር። ለማንኛውም “በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ” ተረትን ከሚያስታውሰን ታሪክ አንድ ልጨምር። ታሪኳን ያገኘኋት ማርቆስ የሻነው ካዘጋጃት በአጼ ቴዎድሮስ “የሺህ ዓመቱ ጀግና አጫጭር ታሪኮች” መፅሐፍ ነው። ነገሩ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን የሆነ ነው። ከእቴጌ መነን መማረክ በኋላ ልጃቸው ራስ አሊ ከጎጃሙ ገዢ ደጃዝማች ጎሹ ጋር በአንድነት ሆነው ካሳን ለመውጋት ወደ ደንቢያ ዘመቱ። ካሳም በአንድነት ተሰልፎ የመጣባቸውን ከፍተኛ ሰራዊት ነጣጥሎ ካልሆነ አንድ ላይ መውጋቱ አደጋ እንዳለው አመዛዘኑና ደንቢያን ለቀው ወደትውልድ ቦታቸው ቋራ ሸሹ። ራስ አሊም የካሳን መሸሽ እንዳዩ ደጃዝማች ጎሹን የደንቢያ ገዢ አድርገው ሾሟቸውና ወደጎንደር ተመለሱ።

ደጃዝማች ጎሹም በነበራቸው የጎጃም ግዛት ላይ ደንቢያ በመጨመሩ በጣም ተደሰቱ። ደንቢያ ሆነው ጦራቸውን በየአካባቢው አሰማሩ። የራስ አሊን ርቀው መሄድ ያወቁት ካሳ ደጃዝማች ጎሹን ለመውጋት ጉር አምባ ወደተባለ ቦታ ጉዞ ጀመሩ። ይህን የካሳን ጦር መንቀሳቀስ የሰሙት ደጃዝማች ጎሹም ጦራቸውን ከያለበት አሰባሰቡ። ጣፋጭ የሚባል የደጃዝማች ጎሹ አዝማሪም በተሰበሰበው ሰራዊት መካከል ገብቶ ፡-

አያችሁ የኛን እብድ

አምስት ጋሞች ሆኖ ጉርአምባ ሲወርድ።

ያንጓብባል እንጂ መች ይዋጋል ካሳ፣

ወርደህ ጥመድበት በሽንብራው ማሳ።

በማለት በካሳ ላይ በግጥም ተሳለቀ። የካሳና የደጃዝማች ጎሹ ሰራዊቶችም ውጊያ ጀመሩ። ደጃዝማች ጎሹም በፈረስ ላይ ሆነው እያዋጉ ሳለ በጥይት ተመቱና ወደቁ። ድሉም የካሳ ሆነ። በዚህ ጦርነት ካሳ ብዙ ሀብትና ምርኮ አገኙ። ጣፋጭ የሚባለው አዝማሪም ተማርኮ ነበርና ካሳ ፊት ቀረበ። ካሳም፣” ምን ብለህ ነው የሰደብከኝ?” ብለው ጠየቁት። አዝማሪውም አሳስቋቸው እንዲምሩት በመፈለግ፡-

አወይ የእግዜር ቁጣ፣ አወይ ያምላክ ቁጣ፣

አፍ ወዳጅን ያማል ስራ ሲያጣ፤

ብትር ይገባዋል የአዝማሪ ቀልባጣ።

በማለት ገጠመ ካሳም ቂም ይዘውበት ስለነበር አዝማሪው በራሱ ላይ የሰጠውን ፍርድ መሰረት አድርገው በዱላ ተደብድቦ እንዲገደል ፈረዱበት ይባላል።

እናላችሁ ወዳጆቼ በሆነ ባልሆነው ምላሳቸውን እየመዘዙ፤ በነገር መርዝ የሚናከሱ ሰዎች አንድዬ ይጠብቀን እንጂ ከመጡብንማ፤ “በአፍ ይጠፉን በለፈለፉ” ተረትን ዞር ማለት ነው። ቸር እንሰንብት።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
645 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 856 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us