“ሆድን በጐመን….”

Monday, 02 May 2016 16:16

 

እንዴት ስነበታችሁ ውዶቼ!..... እንኳን ለበዓለ ፋሲካው አደረሳችሁ!..... እነሆ ዘንድሮ ጾማችንን ሁሉ አንድዬን “ቁጣህን አብርደው፣ ምህረቱን አውርደው” የምንልበት ይሁንልን አቦ!.... እንዲያማ ካልሆነ የምትከተለዋን የባለቅኔ ሁለት ስንኝ መምዘዛችን ግድ ነው።

ደጉ አምላክ ነው እንጂ ሰጥቶ የሚቀድሰው

ርኩስ አይደለም ወይ ካጣማ ወዲያ ሰው።

አባቶች “ሆድን በጐመን ቢደልሉት፣ ጉልበት በዳገት ይለግማል” ይሉት ተረት አለቻቸው። ሌላም ተረት ይደገም፤ “ከማይረባ ጉልበት ልብ አድርጉልኝ ማለት”… እኔ የምለው የሆነውስ ሆነና ይህቺ ትናንት ገና ድክ-ድክ ማለት የጀመረችው ሚጢጢዬ ደቡብ ሱዳን እንዲህ እንደተዳፈረችን ቀረች አይደል?..... እውነቴን እኮ ነው፤ መከታችን ጋሻችን ነው ያልነው መከላከያችን አሁንም ድረስ ከበባ እና ወከባው መሀል እንዳለ ነው እንዴ?.... ግድ የላችሁም ጥላችን ነው፣ መከላከያችን ነው ያልነው ነገር ሁሉ ዘንድሮ እንጃለት “ከቀዳዳ ይሻላል ጨምዳዳ”ን የሚያስመርጥ ጊዜ መጥቷል። ይህንን ስል አንዲት የሙላህ ነስሩዲን ጨዋታ ትዝ አለችኝ። እንካችሁ እስቲ….

ሙላህ ነስሩዲን ከጓደኛው ጋር በመንገድ እየተጓዘ ሳለ፤ ድንገት ዝናብ ማካፋት ይጀምራል። ነስሩዲን ባንጠለጠለው የእጅ ቦርሳ ውስጥ ጃንጥላ መያዙን ያስተዋለ ጓደኛው ፈጠን ብሎ፣ “ወዳጄ ነስሩዲን ከዝናቡ ይከላከለን ዘንድ የያዝከውን ጃንጥላ ቶሎ ዘርጋው እንጂ፤ እንጠለልበት” አለው። ሙላህ ነስሩዲንም “ድንቄም ጃንጥላ” በሚል ስላቅ ተሞልቶ፤ “አይ ጃንጥላው እኮ ሙሉ በሙሉ በቀዳዳ የተሞላ ነው። ስለዚህ ብዘረጋውም ከዝናቡ የሚያስጥለን አይመስለኝም” ሲል ተናገረ።

በሁኔታው እንደመደነቅም እንደመሳቅም የሚቃጣው የሙላህ ወዳጅ ድምፁን ከፍ አድርጐ፤ “ታዲያ ስለምን ጃንጥላውን ያዝከው?” ሲል ጠየቀው። ነስሩዲንም ሲመልስ፤ “በርግጥ ይህን ቀዳዳ ጃንጥላ የያዝኩት ዛሬ ይዘንባል ብዬ ባለማሰቤ ነው” ብሎላችሁ እርፍ ቂ….ቂ…ቂ… ይህቺ ናት ጨዋታ ማለት ይሄኔ ነው።

የምር ግን እንደ ሙላህ ነስሩዲን ጃንጥላ “አለሽ መስሎሻል ተበልተሽ አልቀሻል”ን የሚያስተርተን ክስተት የበዛም አልመሰላችሁም?.... በቃ እኮ መደገፊያችን ነው፤ መተማመኛችን ነው፤ ፈጥኖ ደራሻችን ነው፤ መጠለያችን ነው ያልነው ግለሰብና ተቋም ሁሉ ቀዳዳ እየሆነ፤ አለ አይደል “ለታይታ” ብቻ አደባባይ የሚወጣ ከሆነ ምን ዋጋ አለው? …. ነገሩ ምን አስታወሰኝ መሰላችሁ፤ የሆነ ነገር ከተፈፀመ በኋላ ኃላፊነት መውሰድ የሚገባው አካል በመገናኛ ብዙሃን ፊት ቀርቦ ምን ይላል? “ይህ ይከሰታል ብለን አልገመትንም” ይለናል።

ተገቢውን ስራ ይሠራል ያልነው ተቋም፤ ጉዳያችንን ያሟላል ያልነው ድርጅት፤ በሕግ አግባብ ከሞገደኛ ሰው ይጠብቀናል ያልነው መስሪያ ቤት፤ የምድር አማራጭ ይሆናል ያልነው ፓርቲ፤ የትውልዱን ቀዳዳ ሁሉ ይደፍናል ያልነው ትምህርት ቤት እንደው ብቻ ሁሉም እንደ ሙላህ ነስሩዲን ለታይታ እንዳንጠለጠለው ጃንጥላ ቀዳዳ ከበዛባቸው ምን ይውጠን ይሆን ጐበዝ!?

እስቲ አስቡት ሰውዬው ሀገር አቋራጭ መኪና እያሽከረከረ ነው። ድንገት በረሃ ላይ የመኪናው ጐማ ተንፍሶ ይቆማል። እናም ጠጋ ብለው “ተቀያሪ (ስኮርት) ጐማ አልያዝክም ወይ?” ይሉታል። እርሱም ፈጠን ብሎ “ይዣለሁ ግን አየር አልተሞላም፤ የተነፈሰ ነው” ቢላችሁ ምን ትሉታላችሁ?.... እንደ ሙላህ ነስሩዲን ጃንጥላ ለታይታ ብቻ የተያዘ ቅያሪ ጐማ እንጂ ዋጋ የለውም።

እናላችሁ በሆነ ባልሆነው “የናቴ መቀነት አደናቀፈኝ” አይነት ምክንያት እየደረደሩ፤ ዛሬ የሚዘንብ አልመሰለኝም ከሚሉ ቀዳዳ ጃንጥላ ያዦች፤ ዛሬ ኔትዎርክ የሚሠራ አልመሰለኝም ከሚሉ ሂሳብ ከፋዮች፣ ዛሬ ዶክተሩ የሚገባ አልመሰለኝም ከሚሉ ሐኪም ቤቶች፤ ዛሬ መምህሩ የሚገባ አልመሰለኝም ከሚሉ ትምህርት ቤቶች፤ ዛሬ ከፍተኛ ጥቃት ይሰነዘራል የሚል ግምት አልነበረኝም ከሚል መሪ አንድዬ በጥበቡ ይሰውረን አቦ!

እናላችሁ ትዝብት አዘል ጨዋታም አይደል?.... ዘንድሮ በሆነ-ባልሆነው ሆድ እየባሰን “የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም” ይሉትን ተረት የሚያስተርት ክስተት በዝቶብናል። ለማንኛውም ግን ይዘነዋል ብለን የተማመንበት ነገር ከድቶን ጉድ እንዳንሆን መትጋት ነው። አልያ ግን እነርሱ ዝም ካሉ እኛ ደፍረን እንጠይቃለን። ጐበዝ መከላከያችን እኛን መከለያ ጥይት የለውም እንዴ?.....

ለማንኛውም አብይ-ጾሙን በሰላም አስጀምሮ ያስጨረሰንን እናመሰግነዋለን፣ እንኳንም ጾመ ልጎሙን ፈታልን። ዳሩ ግን በልባችን የብዙ ወገን ሰቆቃና የብዙ ወጣት ሐዘን አለና ደስታችን ሁሉ ግማሽ ነው። ያም ሆኖ እንደቀዳዳው ጃንጥላ ሁሉ የልባችን ተስፋ እንዳይሸነቆር ተግተን እርስ-በእርስ ብንበረታታ ሳይሻለን አይቀርም። አልያ ግን አባቶች እንዳሉት፤ ነገራችን ሁሉ የወረትና የታይታ ብቻ ከሆነ፤ “ሆድን በጐመን ቢደልሉት፤ ጉልበት በዳገት ይለግማል” አይነት መሆናችን አይቀርም።

የዘንድሮን የሐዘንና ደስታ መፈራረቅ ዝም ብለን ስንታዘበው ከክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል “የቅኔ ውበት” የተወሰዱ ጥቂት ስንኞች ትውስ ይሉኛል፤

ደስታና ሐዘን፣ ውርጭና ፀሐይ

ሆነው ይመጣሉ በሰውነት ላይ

ሰው ደስ ባለው ጊዜ ሐዘኑን ይረሳል

ሐዘንም ሲያገኘው መጨነቅ ያበዛል።

አስቦ ሁለቱም አላፊ መሆኑን

ሲከፋው ደስታን፤ ደስ ሲለው ሐዘኑን

አስቦ በመጠን ሁሉን የወሰነ

ብልህ ሰው ይባላል የተመሰገነ።

ቸር እንሰንብት!!!n

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
539 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1131 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us