ምንጩ ያልታወቀ ቦርጭ

Wednesday, 04 May 2016 12:54

 

      ኀሰሳ ስጋ

      እልፍ ከሲታዎች ቀጥነው የሞገጉ

      “ስጋችን የትሄደ” ብለው ሲፈልጉ

      በየሸንተረሩ በየጥጋጥጉ

      አስሰው አስሰው በምድር በሰማይ

      አገኙት ቦርጭ ሆኖ ባንድ ሰው ገላ ላይ።

                        (ከገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም- የግጥም ስብስቦች የተወሰደ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ውዶቼ!?. . . በዓለ ትንሳኤ እንዴት አለፈ?. . . የዘንድሮ ፋሲካ ጌታ ለእኛ ዘላለማዊ ህይወት ከከፈለው ዋጋ በላይ እኛ ስለዶሮ የከፈልነው ዋጋ ክፉኛ መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱን ታዝቤ፤ የኑሯችን ግልቢያ መድረሻው የት ይሆን እያልኩ መተከዝ አብዝቻለሁ።. . . ለማንኛውም ከነገ ዛሬ በጣም የተሻለ ይመስላልና እንኳን አደረሰን ብቻ ሳይሆን እንኳን አሳለፈንም መባባሉ አይከፋም።

እኔ የምለው የአንዳንድ ነገራችን መጀመሪያ ብቻ እንጂ መጨረሻ ዝም ብቻ ነው እንዴ?. . . አንድዬ ብቻ መጨረሻውን ያሳየን እንዳለን መጨረሻ አልባ እየሆነ ተቸግረናል። እናም እንዲህ የምትል ኃይለ ቃል እንናገራለን. . .” የነገሮች መምጫ ብቻ ሳይሆን መውጫም ይታወቅ”. . . የምር - የምር እንነጋገር ከተባለ ብዙ ነገሮች መጀመሪያቸው እንጂ መጨረሻቸው የውሃ ሽታ ነው። . . . ምሳሌ ጥቀስ ካላችሁኝ እነሆ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ስንዘረዝር ከመክረማችን የተነሳ ልክ እንደአንድ ቋንቋ በመልካም አስተዳደር ብቻ አፉን የፈታ ልጅ ሳናገኝ አንቀርም። የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለ ታወቀ፤ ሙሰኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንዳሉ ታወቀ፤ ተጠያቂነት ሊኖር እንደሚገባ ተነገረ፤ ሙሰኞች ለፍርድ እንደሚቀርቡ ቃል ተገባ፤ ስልጣኑን ያለአግባብ የተገለገለ ሁሉ የእጁን እንደሚያገኝ ተዛተ ወዘተ ተብሎ -ተብሎ ወራትም ዓመታትም አለፉ። ዳሩግን አሁንም የመልካም አስተዳደር ችግር መጥፋት ሳይሆን መፋፋት ታይቶበታል። እኛ’ኮ አንናገረውም ብለን እንጂ ዘንድሮ ምንጩ ካልታወቀ ሀብት እኩል ምንጩ ያልታወቀ ቦርጭም ተበራክቷል። . . . እናም ችግሩን ማወቅ ግማሽ መፍትሄ ነው ቢባልም፤ በሽታውን ማወቅ ግማሽ ፈውስ ነው ቢባልም መድሃኒቱ እስካልተገኘ ድረስ በሽታው ወደሙሉ ሞትነት፤ ችግሩም ወደትልቅ ቀውስነት ማምራቱ አይቀርም።

በሽታችን ሌላ መድሃታችን ሌላ፤ ህክምና የሚያስፈልገው እንቅርታችን ሆኖ ሳለ የሚቀደደው ሆዳችን ከሆነ፤ ችግራችን መልካም አስተዳደር ሆኖ ሳለ የሚደረገው የቦታ ሽግሽግ ብቻ ከሆነ፤ የጠፋን ችግሩ ሳይሆን መፍትሄው ሆኖ ሳለ፤ የምንፈልገው የበሽታውን አይነት ሳይሆን የመድሃቱን ውጤት ሆኖ ሳለ፤ ግራ የገባን መግቢያው ሳይሆን መውጫው ሆኖ ሳለ በሆነ ባልሆነው የሚያዋክቡን ግለሰቦች፣ ባለስልጣኖች፤ ዶክተሮች፣ጋዜጠኞች፤ መምህራኖች፣ መስሪያ ቤቶችና ተቋማት ሁሉ እንዲያውቁት የምንፈልገው ልብ ያለው ልብ እንዲል ብቻ ነው።

አንዳንድ አጋጣሚዎችን ስንታዘብ እኮ አለ አይደል እኛ የማናውቀው ነገር አላቸው እንዴ? እኛ የማናውቀው ሀገር አላቸው እንዴ?. . . እኛ የማናውቀው አሠራር አለ እንዴ? እና የማናውቀው ስልጣን አላቸው እንዴ? እኛ የማናውቀው መውጫ አላቸው እንዴ? ሊያስብለን ይችላል። እዚህች ጋ ትዝብት አዘል ጨዋታችንን ታሳምርልን ዘንድ አንዲት ወግ እንካችሁ። ሰውዬው እኩለ-ሌሊት አካባቢ አንድ ሌባ በሩን ሰብሮ ለዝርፊያ ይገባል። ሌባው ወደውስጥ ከዘለቀ በኋላ የነቃው የቤቱ ባለቤት “እስቲ ጉዱን ልየው” በሚል አኳኋን በቤቱ ምንም ጠቃሚ ነገር እንደሌለ አውቆ የሌባውን ሁኔታ በድብቅ መከታተል ጀመረ። ሌባው አንዳች ነገር የደበቀ በሚመስል መልኩ ብርበራውን በጥንቃቄ ሲያደርግ የቤቱ ባለቤት ዝም ብሎ ይመለከተው ነበር። ትንሽ እየቆየ ግን የሌባው ፍለጋ በጥንቃቄና አንዳች ነገር እንዳለ በመተማመን መሆኑን የተገነዘበው የቤቱ ባለቤት፤ “ይሄ ሰውዬማ ቤቴ ውስጥ እኔ ያላየሁትን ነገር አስቀምጦ ወይም እንዳለ ሰምቶ ሊሆን ቢችል እንጂ እንዲህ አይፈልግም ነበር” ሲል አሰበና ፍለጋውን ከሌባው ጋር ተቀላቀለ። . . . ቂ-ቂ-ቂ!

አንዳንድ ፍተሻዎች፣ አንዳንድ ንግግሮች፣ አንዳንድ ድርጊቶች፣ አንዳንድ ህክምናዎች፣ አንዳንድ ባለስልጣናትና ተቋማት የሚያደርጉት ነገር ሁሉ እኛ የማናውቀው ነገር ያለ አስመስሎ ሊያደናብር እንደሚችል ማሳያ የምትሆን ታሪክ ናት።

ለማንኛውም ለገጠመን ግለሰባዊም ሆነ ማህበረሰባዊ ችግር፤ ለሚያራውጠን የኑሮ ውድነትም ሆነ የጤና ውድመት የሚሆነንን መግቢያውን ብቻ ሳይሆን መውጫውን፤ መምጫውን ብቻ ሳይሆን ማምለጫውን፤ ማረፊያውን ብቻ ሳይሆን ማለፊያውንም የሚያሳየን ሰው አንድዬ አይነሰን አቦ!. . . ዘንድሮ ሁሉም በእጅ እየመጣና እየሄደ ችግራችን ከመፍትሄ ይልቅ ችግሩ እየተባባሰ ስናይ የሚያስተዛዝበን የሰው ብር ብር ማየት ነውና የምትከተለዋን ቅኔ ተውሰን ማምለካችንን እናቀርባለን።

አንገት የለሽም ወይ አዙሮ የሚያይ፣

ሲመሽ ብር ብለሽ ትሄጃለሽ ወይ?

ትንሳኤያችን ለዚህ የዓለም ሃጢያት ማስተሰርያና መውጫ/ ማምለጫ ትልቁ ማሳያችን ሊሆን ይችላል። . . . አንድዬ ብቻ ምንጩ ካልታወቀ ሀብትም ሆነ ቦርጭ ይሰውረን አቦ!. . . መልካም የበዓል ሳምንት እንዲሆን ተመኘሁ። ቸር እንሰንብት!!

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
858 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 951 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us