“የዘፈን ዳር-ዳሩ ……”

Wednesday, 11 May 2016 12:25

                ይተርፈኛል

በእግረ ሙቅ ስታስሩኝ፣

የሰው ምርጫ ስጡኝ፣

ከራስ ወዳዱ ጋር፣

አንድ ላይ ጠፍሩኝ፣

እሱ ይሻለኛል፤

ራሱን ሊያድን ሲል፣

ለእኔም ይተርፈኛል።

 

(“ምልክት” ከተሰኘው የሳምሶን ይርሳው ጌትነት

የግጥም ስብስብ የተወሰደ)

 

እንደምን ሰንብታችኋል ወዳጆቼ!?. . . እንግዲህ ዘንድሮ እንዲህ ከክፉም ከደጉም ጠጋ-ጠጋ እያሉ የራስን “ላይፍ” ማመቻቸት ዋነኛው የኑሮ ዘይቤ ሆኗል።. . . የአንድን ሰው ስህተት በመሸፋፈን ሌላኛው ከተሟገተ የጥቅም ትስስር አለ ማለት ነው። የአንድን ተቋም ስህተት ለመሸፋፈን የሆነ ኃላፊ ሽንጡን ገትሮ “አይኔን ግንባር ያርገው” አይነት ሙግት ውስጥ ከገባ የሆነ የጥቅም ትስስር አለ ማለት ነው። የአንድን ፓርቲ ስልጡንነትና ዴሞክራሲያዊነት አጋንኖ የሚሞግት ደረቅ ሰው ካለ ይህሰው የጥቅም ትስስር አለው ማለት ነው። . . . ታዲያ ይህን ሁሉ ታዝቦ ሲያበቃ ሀበሻ ምን ብሎ ይተርታል መሰላችሁ? “ውሻ በበላበት ይጮሃል” ደስ አትልም? ኧረ ሌላም ሊባል ይችላል. . . “እንቁራሪት የምትኖርበትን ውሃ አትጠጣም!”. . . ቂ-ቂ-ቂ

 

እናላችሁ ገጣሚው እንዳለው ከራስ ወደዱ ጋር ተጠግተን ማምለጫ መንገድ የምንማለድ ስንት ዜጎች አለን መሰላችሁ፤. . . ክፉን ስናሞግስ፤ ለሌባ ስንደንስ፣ ለሙሰኛ ስንደግስ፣ ለእንብላው ስናጎነብስ ከተገኘን እኛም የጥቅም ተጋሪው ተደርገን መደመራችን ግልፅ ነው። እናም “የዘፈን ዳር ዳሩ እስክስታ ነው” ይሉት ተረት ይተረትብናል። ለምሳሌ አንድ ነጋዴ ደጋግሞ ስለአንድ እቃ መጥፋት፣ ስለአንድ እቃ መወደድና ቀበሌ አለመኖር ከነገራችሁ እርግጠኛ ሁኑ ይህ ዕቃ በቅርቡ ውድ ሆኖ ታገኙታላችሁ። የነገራችሁ ነገር ሁሉ የነገር ዳር ዳሩን ነው። 

 

እስቲ ደግሞ የዘፈን ዳር-ዳሩን የምታስታውስ እና ከነገሩ አነጋገሩ የምታሰኝ የሙላህ ነስሩዲንን አንድ ጨዋታ ወዲህ ግድም ጣል እናድርግ። . . . ኑሮውን በሩቅ ከተማ ያደረገው የነስሩዲን አጎት አለኝ ከሚላቸው ነገሮች መካከል መርጦ በአደራ መልክ ለነስሩዲን ያስረክበዋል። ነስሩዲን ከአጎቱ ከተቀበላቸው ውድ ነገሮች መካከል አንዲት የምታምር ድመት ትሞታለች። ይሄኔ ነስሩዲን ለአጎቱ “ውድ አጎቴ ድመትህ ሞታለች” ሲል መልክተኛ ይልክበታል።

 

ይህን አሳዛኝ ዜና የሰማው የሙላህ ነስሩዲን አጎት በጣም ተበሳጭቶ የሚከተለውን የመልስ ደብዳቤ ይፅፋል። “ስማ ነስሩዲን በእኛ ባህልና ወግ መሠረት ሞትን እንዲህ በቀላሉ ማርዳት ነውር ነው። ምን አለበት “ድመትህ ሞተች” የሚል መልዕክት ከምትልክብኝ ቀስ በቀስ እንድረዳ ብታደርግ። ለምሳሌ “ድመትህ ያልተለመደ ባህሪይ እያሳየች ነበር” ብትለኝ፤ ቀጥለህ ደግሞ “ድመትህ ከአቅም በላይ ስትዘል ነበር” ብትለኝ፤ ቀጥለህ ደግሞ “ድመትህ ተሰወረችኝ” ብትለኝ፤ ከዚያም “በስተመጨረሻ ሞታ አገኘናት” ብትለኝ መልካም ይሆን ነበር” ሲል መልዕክት ላከበት።

 

ሙላህ ነስሩዲን ይህን ደብዳቤ ካነበበ ከወር በኋላ አንድ ደብደቤ ለአጎቱ ፃፈለት። አጎትዬው የደረሰውን መልዕክት ገልጦ ማንበብ ሲጀምር እንዲህ ይል ነበር፤ “እናትህ ያልተለመደ ባህሪይ ማሳየት ጀምራ ነበር። . . .” የደብዳቤውን አጀማመር የነስሩዲን አጎት ሳይረዱት የሚቀሩ አይመስለኝም። እናም እንዲህ ማለታቸው አይቀርም። “የዘፈን ዳር ዳሩ እስክስታ ነው።”. . .

እንዲህ አጀማመሩን አሳየን እንጂ አጨራረሱንማ እኛም እናውቅበታለን ጎበዝ!. . . አጨራረሱን ሲል አንዲት ያነበብኳት የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ ትዝ አለችኝ። የአፄው ዘመነ ንግስና ፍፃሜ በተቃረበበት ጊዜ የሆነ ክስተት ነው። በስተመጨረሻ የእንግሊዝን ጦር ለመግጠም መቅደላ የከተመው የአፄ ቴዎድሮስ ጦርን የሚከዳው በረከተ። ከመቅደላ ተራራ መውጫ በር ላይ ቀንና ሌሊት ታማኝ የሆኑ ወታደሮች መጠበቅ ስለጀመሩም ለሚከዱ ሰዎች በጣም አስቸጋሪ ሆነባቸው። ለማምለጥም ብዙ ዘዴና ችሎታ አስፈላጊ ሆነ። አንድ ቀን ማታ አንዲት ሴት ትልቅ እንቅብ በራሷ ላይ አድርጋና አይኖቿ እንባ አቅርረው ወደ በሩ ዘበኞች መጣችና ወንድሟ ከአጥር ውጪ ራቅ ባለ ቦታ ላይ ቆስሎ ህይወቱ በአደጋ ላይ በመሆኑ እንጀራና ውሃ ልትወስድለት መፈለጓን ገለፀችላቸው። ዘበኞቹም አዝነው እንድታልፍ ፈቀዱላት።

 

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አንድ ወታደር በፍጥነት እየተራመደ ወደበሩ መጣ። የሴቲቱን መልክና ቁመና ገልፃ፤ በበሩ አልፋ ሄዳ እንደሆነ ሲጠይቃቸው መሄዷን አረጋገጡ። ወታደሩም በቁጣና በብስጭት ሴትየዋ ሚስቱ መሆኗን እና ከአንድ ውሽማዋ ጋር ተገኝታ አብረው ለመጥፋት መሄዷን ገለፀላቸው። የተፈጠረውንም ሁኔታ ለአፄ ቴዎድሮስ እናገራለሁ በማለት ዘበኞቹን አስፈራራቸው። ዘበኞቹም ሴትየዋ ከወጣች ረጅም ጊዜ ስላልሆነ ቶሎ ብሎ እንዲደርስባትና እንዲመልሳት አሳለፋት። ብልጦቹ ባልና ሚስትም እንደወጡ በዚያው ቀሩ ይላል።. . . ሚስቱን ተጠግቶ ያመለጠ ባል ማለት ነው። እንግዲህ ለማንኛውም በነገሮች ሁሉ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ “የዘንዶን ጉድጓድ በሌላ ሰው ክንድ እንለካ” ከሚሉ ብልጣብልጦች አንድዬ ይጠብቀን. . . እናም “የዘፈን ዳር- ዳሩ እስክስታ ነውና” የነገር ዘርን ሲዘፈን፤ የሙስና ዘፈን ሲዘፈን፤   የወንጀል ዘፈን ሲዘፈን፤ የአቋራጭ ዘፈን ሲዘፈን እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አይነት ዘፈን ሲዘፈን ዳር ዳሩ ላይ እስክስታ ከመምታት ይልቅ ኧረ በሕግ አምላክ የሚል ልቦና ይስጠን፤ ቸር እንሰንብት።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
583 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1141 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us