“ያባቴ ቤት መች ጠፋኝ?”

Wednesday, 18 May 2016 13:20

ዋርካ

ቅርንጫፍ አብዝቶ ስሩን አንፈራጥጦ

ዋርካ ልሁን ብሎ ከዛፍ ሁሉ በልጦ

ከዝናብ ከፀሐይ ህዝብን ካላዳነ

እንቧጮ ነው እንጂ ምኑን ዋርካ ሆነ?

(ከታለጌታ ይመር፤ “ማን ነበረ መሪው?”

 የግጥም ሰብስብ የተወሰደ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?... ዋርካ ይሆነናል፣ ከዝናብ ከፀሐዩ ይከላከለናል ያልነው ሁሉ እላያችን ላይ እየወደቀና ዕዳ ውስጥ እየዘፈቀን ዜናው ብቻ ከተረፈን ምን ዋጋ አለን ጐበዝ?..... እንደው እንዲህ እንደዘመኑ ተሰራ የተባለው ፎቅ ሲገነደስ የሰማ፤ ስራው ተጠናቋል የሚባልለት ስኳር ኮርፖሬሽን በ77 ቢሊዮን ብር ጉዳይ ሲታመስ ያየ ሰው ምን የሚል ይመስለኛል መሰላችሁ?.... ከቅኔ አፎቱ የምትከተለዋን መዘዝ ያደርግና፡-

 

በጣም ሰፋ ብሎ ይሠራ ቤታችን

ማዘኑ እንደሆነ ሞልቷል ባገራችን።

 

 

እውነት ግን የሚያሳዝነን ነገር እየበረከተ አልመሰላችሁም?.... እንደውም አሁን አሁንማ በጣም ከመብዛቱ የተነሳ “መርዝም ይለመዳል ቀስ-በቀስ” አይነት ሆኖብናል መሰለኝ። የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለ እኛም መንግስትም እናውቃለን፤ የሙስና ችግር እንደተበራከተ እኛም መንግስትም እናውቃለን፤ የስነ-ምግባርና የተጠያቂነት ችግር በየዘርፉ እንደተንሰራፋ እኛም መንግስትም እናውቃለን፤ የኮንሰትራክሽን ችግር መሠረቱን እንደጣለብን እኛም የሚመለከተው አካልም እናውቃለን፤ ስኳር ኮርፖሬሽን ከተሠራው በላይ ሜቴክ ለራሱ የሰራው ነገር እንደበለጠ እኛም መንግስትም እናውቃለን… እናም ዋርካ ይሆነናል ያልነው ተቋም፣ ግለሰብና መንግስት ቆይቶ-ቆይቶ እንቧጮ ከሆነብን የአገራችንን ሰው ቅኔ ተውሰን በድጋሚ እንዲህ እንላለን፤

 

በጣም ሰፋ ብሎ ይሠራ ቤታችን

ማዘኑ እንደሆነ ሞልቷል ባገራችን።

የአገራችንን ተደጋጋሚ ችግሮችና የመፍትሄ ስልበት በተመለከተ ከአንድ ወዳጄ ጋር ወግ ስንጠርቅ የስኳር ኮርፖሬሽንን ዜና ተመልክቶ ሲያበቃ ምን አለኝ መሠላችሁ? ተቋማቱ ከውል ይልቅ ልቅ የስራ ግንኙነት ለዚህ ሁሉ ብክነት እንዳደረጋቸው ጠቁመዋል፤ እኔም እላለሁ ጐበዝ ልቅ ወሲባዊ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ልቅ የስራ ግንኙነትም የስኳር ኮርፖሬሽን አይነት የከሰረ ፕሮጀክት ውጤት ሊያስገኝ ይችላልና ጠንቀቅ እንበል።

 

የምር ግን የእኛ ነገር “ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” ያሉትን ጥንታዊ ብሂል የሚተገብርብን አልበዛም እንዴ?... የምሬን እኮ ነው፤ ከእቅድ በታች መስራትና ከአቅም በላይ ማቀድ ትክክል እየሆነ የመጣ ዘመንኛ ሱስ አይመስላችሁም?.... አንዳንድ ሹመኞቻችን ኮራ፣ ጀነን ብለው “የያዝነው የተለጠጠ ዕቅድ ነው” ሲሉም እየሰማናቸው ነው። የማይተገብረውን ማን ለጥጠህ አቅድ እንዳለው የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው። ለዛም ሳይሆን አይቀርም ማታ ታይቶ ጠዋት ተደፍቶ የሚያድር ህንፃና ሰው የተበራከተው።… እናላችሁ ይህ ሁሉ የምንሰማው ችግር እንደው ለትዝብት እንደጋግመው እንጂ… የሚስቱን የውሽማ ብዛት ድንገት ስለሰማው አባወራ ምን ተባለ መሰላችሁ? “ብለነው ብለነው የተውነውን ነገር፣ ባሏ ትናንት ሰምቶ ታንቆ ሊሞት ነበር” ይሉትን ተረት የሚያስተርት ነው።

 

እስቲ ደግሞ ወጋችንን በጨዋታ ለማዋዛት ያህል የምትከተለዋን እንካችሁ።… ሰውዬው ለጥቂት ዘመናት ወደከተማ ሰነባብቶ ዘመዶቹን ለመጠየቅ ወደ አባቱ ቤት ይሄዳል። ዘመድ ተሰብስቦ በሰላም ስለመምጣቱም ምስጋና ቀርቦ ቡና ከተጠጣ በኋላ፤ የቀድሞ ወዳጁን ቤት ፍለጋ ወጣ ብሎ መዞር ይጀምራል። እናም የወዳጄ ቤት ይጠፋውና ወደ አንድ መንገደኛ ጠጋ ብሎ፣ “ይቅርታ ጌታዬ የአቶ አክሌን ቤት ፈልጌ ነበር፤ ተሰውረኝ የትኛው ይሆን?” ብሎ ይጠይቃል። ተጠያቂው መንገደኛም፤ አላውቅም ማለት ያሳፍረውና እንደመጣለት ከርቀት የሚያየውን ቤት እያመለከተ “ያ ቤት የምትፈልገው ሰው መኖሪያ ነው” ሲል ይመልስለታል። የተጠቆመው ቤት እርሱ ያደገበትና ቤተሰቡ የሚኖርበት፤ የአባቱ ቤት መሆኑን ያወቀው ፈላጊው ሰው የጠቋሚውን አላዋቂነት ተረድቶ ምን ቢለው ጥሩ ነው?.... “አይ ጌታዬ የአባቴ ቤትማ መች ጠፋኝ ብለው ነው” አለ ይባላል።

 

እናላችሁ አላውቅምን አፍረው፤ አልችልምን ጠልተው በድፍረት ህንፃም፣ ቤትም፣ ድርጅትም፣ ፋብሪካም ከሚገነቡ ደፋር ሰዎች አንድዬ ይሰውረን።… በሌላም በኩል የምናውቀውን ነገር እየደጋገሙ፤ ከእኛው ጋር ከሚጮሁ የስራ አስፈፃሚዎችና ለመፍትሄ አልባ መፍትሄ አፈላላጊዎች እንዲህ እንላለን “የአባታችን ቤትማ መች ጠፋን”… አንድዬ ብቻ ዋርካ ይሆኑናል ብለን እንቧጮ ከሚሆኑ ሰዎች ይሰውረን አቦ!

 

ጎበዝ!... ጠፍተዋል የተባሉት 88 የኮንደሚኒየም ቤቶች ጉዳይ ምን አዲስ ወሬ አለ? እኛማ ‘ገራገሩ’ መንግሥታችን ‘አፋልጉኝ’ ቢለን በየሄድንበት ጎዳና ድንጋይ እየፈነቀልን ፍለጋውን ተያይዘነዋል። ምን ይደረግ! ህንፃ ከነነፍሱ የሚወስድ አውሬ መጥቶብን!... በቀጣይ ግን የሚያስከፍለን ዋጋ ብዙ ነውና ጐበዝ ብንተሳሰብ ምን ይለናል?... አልያ ግን ራሳችንን እያታለልን እንድንኖር አትፍረዱብን። ራስን የማታለል ነገር ሲነሳ አረፋይኔ ሀጐስ ከፃፈልን የጋብሮቮ ቀልዶች መካከል የምትከተለዋ ትዝ አለችኝ። ሁለት የጋብሮቮ ተማሪዎች ባርኔጣ ገዝተው ከፎቅ ሲወጡ ኃይለኛ ዝናብ መጣል ይጀመራል። በረንዳ ላይ ቆመው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሲወያዩም አንድ ሀሳብ ይመጣላቸዋል፤ ባርኔጣ መለዋወጥ። በአዲሱ ሀሳብ መሠረት አንዱ ጋብሮቮ የሌለውን ባርኔጣ ያደርግና በመበስበስ ላይ ያለው ባርኔጣ የእሱ አለመሆኑን እያሰበ ተፅናንቶ በሰላም ይጓዛል።… ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ማለት ይሄኔ ነው። ለማንኛውም በትልልቅ ፕሮጀክቶች ስም፤ ትልልቅ ገንዘብ እየዘገናችሁ ዜና የሆናችሁ ተቋማት የምትከተለዋን የአዝማሪ ግጥም ተጋብዛችኋል።

 

መገን ያራዳ ልጅ አይፈራም ኪሳራ፣

በቀን የሚያጠፋው ይቅር አይወራ።

 

ቸር እንሰንብት።n

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
634 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1011 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us