“መሬት መሬት ስናይ. . .”

Wednesday, 25 May 2016 12:46

 

በአሸናፊ ደምሴ

አህያ ሁን አለኝ - አህያ ሆንኩለት

አሰሱን ገሰሱን እንድሸከምለት

ውሻዬም ሁን ብሎ ሆንኩኝ ላስደስተው

ጭራ እየቆላሁኝ እንዳጨዋወተው

ፈረስም ሁን ብሎ ፈረሱ አደረገኝ

በየዳገቱ ነው ወስዶ ’ሚጋልበኝ

እንጃ ግን ሰሞኑን “በግ ነህ” ተብያለሁ

ሊያርደኝ ነው መሰለኝ አሁን ፈርቻለሁ።

      (ከገጣሚ ሰለሞን ሞገስ “ፅሞና እና ጩኸት” የግጥም መድብል የተወሰደ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!? . . . “በለው- በለው” እያለ የሚገፋፋና “ሆይ - ሆይ” እያለ በሌለን ነገር ደረት የሚያስነፋ አባዜ የበዛ አልመሰላችሁም?. . . እኛማ ዘንድሮ ሁሉም ነገር ያልፋል ብለን አንገታችንን ስንደፋ፤ ማጅራታችንን ሊደፋ የሚቃጣው በቅቶብናል።. . . ኧረ ጎበዝ አውቀን እንዳላወቅን፤ አይተን እንዳላየን፣ ሰምተን እንዳልሰማን፤ ሽቶን እንዳልገማን፤ አጥተን እንዳላጣን ሆነን የምናልፈው ለናንተው (ለቦሶቻችን) “ሼም” ይዞን እንደሆነ ይታወቅልን።

 

መሬት መሬት ስናይ

መሬት መሰልናቸው፣

ያጣ ሰው አያገኝ

እየመሰላቸው። (እንዲል የሀገራችን አዝማሪ)

 

ለማንኛውም ሳያውቅ ታውቃለህ እንደተባለ ሰው፤ ሳይማር ተምረሃል እንደተባለ ምሁር፤ ሳይሰለጥን መኪና አሽከርክር እንደተባለ ሾፌር፤ ዶክተር ሳይሆን በድፍረት በሽተኛን እንደሚመረምር ደፋር ሰው ከመሆን ይሰውረን አቦ!. . . እኛማ ዘንድሮ መሞከሪያ ሆነናቸዋል መሰለኝ ሁሉም እንደአቅሚቲ ጡንቻውን ይለካብን ይዟል። አለቆቻችን በስልጣናቸው ጡንቻ፤ ነጋዴዎቻችን በገበያቸው ጡንቻ፤ የስራ ሂደት ኃላፊዎቻችን በማህተማቸው ጡንቻ ሁሉም እንደየአቅሙ ከፍ ዝቅ ያደርገናል። እናላችሁ መሬት መሬት ስናይ ላቀለላችሁን ሁሉ አንድዬ ብቻ ልብ ይስጥልን አቦ!. . .

እንካችሁ እስቲ ደግሞ ወጋችንን የምናሳምርበት ጨዋታ፤ ሰውዬው የመጀመሪያ እርዳታ ህክምና አሰጣጥን በተመለከተ ስልጠና እየተሰጠው ነው። እናም ወደስልጠናው ማብቂያ መምህሩ ሊፈትነው ይጠራዋል።

 

“ለመሆኑ የሆነ ሰው ራሱን ስቶ ብታገኘው ምን ታደርጋለህ?”

“አረቄ እሰጠዋለሁ” መለስ ሰልጣኙ

“አረቄ ካጣህስ?” አሰልጣኙ በመገረም ድጋሚ ጠየቀው።

“ሳገኝ እንደምሰጠው ቃል እገባለታለሁ!” ብሎላችሁ እርፍ። ቂ-ቂ-ቂ. . . ይህቺ ናት ጨዋታ አትሉልኝም እንደው ቢሆንም ባይሆንም በባዶ ቃል እየገቡ የሚያስጠብቁን ሰዎች በርክተዋል መሰለኝ። (እዚህች’ጋ “አወቅሽ -አወቅሽ ሲሏት የባሏን መፅሐፍ አጠበች” ይሏትን ተረት ማስገባት ተገቢ ሳይሆን አይቀርም)

 

መብራት ካጣን ሰነባብተን ብላችሁ በመብራት ኃይል አለቆች አቤት ስትሉ የሚሰጣችሁ መልስ፤ “በቅርቡ ሙሉ በሙሉ የመብራት ሃይል አገልግሎት እንደምታገኙ” የሚል ቃል ይገቡላችኋል።.. . የስልክና የኔትዎርክ መቆራረጥ አጋጥሟችሁ ወደቴሌኮም መስሪያቤት ጎራ ስትሉ የምትገኙት መልስ፤ “በቅርቡ ተስተካክሎ የተሳካ ግንኙነት እንደምታገኙ ቃል እንገባለን” የሚል ነው። . . . ውሃ ልማት ዘንድ ጎራ ብላችሁ፤ “ኧረ የውሃ ጠብታ ናፈቀን” ስትሉ የምታገኙት መልስ፤ “በቅርቡ አባይን በበራችሁ እንድፈስ እናደርገዋለን” አይነት ቃል ይገባላችኋል”. . . የመንገድ ነገር ቢቸግራችሁ የመንገድ ባለስልጣን፤ “ግድ የላችሁም በቅርቡ ውሃ የሚያሳልፍ፤ ጎርፍ የማያስተርፍ አይነት መንገድ ይገነባላችኋል” የሚል ቃል ይሰጡዋችኋል። እናላችሁ በየመስኩ በችግራችሁ ጊዜ ቃል የሚገባላችሁ እንጂ በችግራችሁ የሚደርስላችሁ ሰው ማግኘት ከባድ የሆነ ይመስላል።

 

እናላችሁ ዘንድሮ ከተማ ላይ የዝናብ ጎርፍ ገጠሩ ላይ ጎርፉና ድርቁ ወጥረውን ባለበት ሁኔታ በፍጥነት ተግባራዊ መሆን የማይችል ቃል መግባት ትርፉ ሃጢያት ነው። . . . አንድዬ ከተፈጥሮ የጎርፍ አደጋ ይጠብቀን። እኛን ከጎርፍ አደጋው ባልተናነሰ በድንገት በአንድ ንጋት የሀብት ማማ ላይ የሚገኙት ጎርፎች ናቸው የሚደንቁን። . . .ለማንኛውም ከዜሮ ተነስቶ በልኩ ሃብት አፍርቶ የሚበለፅግ ሰው፤ ለራሱም ለወገኑም የሚደርስ ልበ ሰፊ ነው።

 

እዚህች’ጋ አንዲት የጋብሮቮ ጨዋታን እንካችሁ፤ ከጋብሮቮ የመጡ ወዳጆች ቡና እየጠጡ ቢጫወቱ ከመካከላቸው ሀብታም የሆነውን ከምን ተነስቶ እንዴት እዚህ ሊደርስ እንደቻለ ይጠይቁታል። “ለአብነት ያህል፤ ሚስቶቻችሁ ሹርባ ሲሰሩ ምን ያክል ሩዝ እንደሚጭሩ ታውቃላችሁ?” ሲል መልሶ እነርሱን ይጠይቃቸዋል።

 

“የሚያስፈልገውን ያህል ነዋ!” በጋራ ይመልሳሉ።

“ባለቤቴም የምትጨምረው ልክ የሚያስፈልገውን ያህል ነው። ሩዙን ወደድስቱ ከመጨመሯ በፊት ግን አንድ አስራ ሁለት ያህል ፍሬ ትቀንስለታለች። ዛሬ አንድ ደርዘን ፍሬ፤ ነገም አንድ ደርዘን ፍሬ አስቡት እንግዲህ” አላቸው ይባላል። (ይሄ ግን ቁጠባ ነው? ቂ-ቂ-ቂ) ለማንኛውም ያጣም ሰው ያገኛል፤ የደከመውም ይበረታል፤ ያልገባውም ያውቅበታልና መሬት -መሬት ስናይ፣ አናት አናታችንን አትበሉን እሺ. . . ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
640 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 950 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us