“አንድ ዓይን ያለው. . .”

Wednesday, 01 June 2016 11:47

 

በአሸናፊ ደምሴ

አርሶ መራብና ተኩሶ መሳት

እያደር ይፋጃል እንደእግር እሳት

           (የአገራችን አዝማሪ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . እኛማ አለነው መኖር ከተባለ። እኔ የምለው ግንቦት 20 ከራሱም በልጦ 25 ዓመታት አለፈው ማለት ነው አይደል?. . . ለማንኛውም ከሁሉም ከሁሉም በስታዲየም በታዩት ባቡሮችና ኮንዶሚኒየሞች የሞተው ተስፋችን በጥቂቱም ቢሆን ማንሰራራቱን አንድ ሰው ለጌቶቻችን ይንገርልን አቦ!. . . እግረ መንገዴን የአየር ሞገዳችንን እና የእግር መንገዳችንን ሞልተን ያከበረነው ግንቦት 20 እኛንም ከጉልበተኛ ኑሮና ከመልካም አስተዳደር እጦት የሚያስከብረን ቀን እንዲናፈቀን ይታወቅልን።

 

እናላችሁ “አንድ አይን ያለው በአፈር አይጫወትም” እንዲሉ አንበላም፣ አንጠጣም ብለን ያጠራቀምናት የኮንዶሚኒየም ገንዘብን በተመለከተ እያንዳንዷን ነገር እየመነዘርን መስማት መጀመራችንን ግልጽ ማድረግ እንወዳለን። እኔ የምለው 88 የኮንዶሚኒየም “ብሎኮች” ጠፉ መባሉን “ኧረ ውሸት!” ተባልንም አይደል?. . . የምሬን እኮ ነው 88 ብሎክ ጠፋ ብለን ስናካብድ የሰሙ የስራ ኃላፊ ምን እንዳሉ አልሰማችሁም እንዴ?. . . ኮራ ጀነን ብለው “88 ብሎክ ጠፋ ምንምን የምትሉት ፍጹም ውሸት ነው። ይልቅስ ያልሰራናቸው 500 ብሎኮች አሉ” ብለውን እርፍ ቂ-ቂ-ቂ ኧረ ተው በስቃያችን ላይ አትሳለቁብን። አለመስራት ከማጥፋት በምን ይተናነሳል ጎበዝ?

 

ለማንኛውም በዚህች አጋጣሚ የታዘብናትን ሰሞነኛ ጉዳይ ጠቆም ብናደርግ ምን ይለናል?. . . የድል ቀንንም ሆነ የትግል ቀንን ማክበር መልካም ነገር ነው። ዳሩ ግን ሁሉ ነገር ለበዓሉ ድምቀት እየተባለ ነገር ባይደበላለቅ ምን ይመስላችኋል? ለማንኛውም ግንቦት 20 ምን ይደረግ የዚህ የቤት ነገር እኮ በሆነው ባልሆነው እያስጨነቀ፣ “አንድ ዓይን ያላት እንቅልፍ የላትን” ያስተርትብን ይዟል ጎበዝ።  ስናከብር የፈረሰውን የኛንም ቤት /የጠፋውንም ጭምር/ እየሰራን ቢሆን ደግ ነው።

 

አንድ ዓይናችን ቤታችንና እንጀራችን ነውና ግድ የላችሁም የምንለፋበት እንጀራና የምናርፍበት መኖሪያ አታሳጡን።. . . በካርቱን እና በስዕል ቤት እየሳላችሁ በስንት በዓል ማድመቂያ ምራቃችንን እንዳስዋጣችሁን አንድዬ ይቁጠረው። . . . የስዕል ነገር ሲነሳ አንዲት ጨዋታ ትዝ አለችኝ፣ ሰውዬው ሰዓሊ ነኝ እያለ አገር ይያዝልኝ የሚል አይነት ነው። እናላችሁ አንድ ለሰርግ የሚበቃ የተወጠረ ሸራ ላይ የሳለውን ስዕል በአንድ ሆቴል ግድግዳ ተሰቅሎ ያየ አንድ ሰው የሆቴሉን ባለቤት ያስጠራና፣ “ለመሆኑ ይሄ ስዕል ምን የሚሉት ስዕል ሆኖ ነው እዚህ እንግዶች ፊት የለጠፋችሁት?” ሲል ይጠይቃል።

 

የሆቴሉ ባለቤትም የረሱት ጉንፋን እንደተነሳባቸው ሁሉ ነገሩ ትን አስብሏቸው ካሳሉ በኋላ፣ “መጀመሪያ ላይ የሰቀልነው ሰዓሊው” አብስትራክት ስራዬ ነው ብሎ አታሎን ነው። እየቆየ ግን መሸወዳችን ሲገባን ቢያንስ የተጠቀመበት ሸራ ትልቅ ስለሆነ፤ ከስዕሉ ይልቅ ለሸራው ክብር ስንል ነው ከዚህ ግድግዳ ላይ ያላነሳነው” ሲሉ መለሱለት። ይህን የተመለከተ አንድ ሌላ የሆቴሉ ደንበኛ፣ “ይሄ ስዕል ተብሎ እዚህ ፊት ለፊት መስቀል አልነበረበትም” ከማለቱ ሌላኛው ከአፉ ቀበል አድርጎ ምን ቢለው ጥሩ ነው? ሰዓሊውን እዚህ ግድግዳ ላይ መስቀል በሰማይም በምድርም የሚያስቀጣ ሆኖባቸው እንጂ እርግጠኛ ነኝ ከስዕሉ ይልቅ ሰዓሊውን መስቀል ቢችሉ ያደርጉት ነበር።” ብሎላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ! ይህቺ ናት ጨዋታ አትሉልኝም?

እናላችሁ አንዳንድ ነገራችን ስዕሉን ሳይሆን ሰዓሊውን ስቀሉልን የሚያሰኘን ነው። . . . ሌላው ደግሞ “አንድ ዓይን ያለው በአፈር አይጫወትም” ይሉትን ተረት የሚያስታውሰን የእግር ኳሳችን ነገር ነው። ልክ እንደቤት ፈላጊውና የቤት ግንባታው ፍጥነት አለመጣጣም ሁሉ፤ የእግር ኳሳችን ደረጃና የደጋፊዎቻችን ስሜት በምንም ተአምር የሚገናኝ አይደለም። “ይህቺም እንጀራ ሆና ሚጥሚጣ በዛባት” አሉ፤ እስቲ አሁን ይሄም እግር ኳስ ደረጃውን የጠበቀ ፕሪሚየር ሊግ ይመስል ሰው ደሙን እያዘራ፤ አጥንቱን እየከሰከሰ ሲራኮት አያሳዝንም?. . . የምሬን እኮ ነው፤ ደጋፊ ሲፈነካከት ዝም ስንል፤ ተጫዋቾች ሲፈነካከቱ ዝም ስንል፤ “ብለን- ብለን ዳኛ የሚፈነከትበት፤ አጥንት የሚከተከትበት ጊዜ ላይ ደርሰን?. . . ኧረ ጎበዝ እየተስተዋለ።

 

ሁሉም ነገር ካለፈ በኋላ አዝማሪው እንዳለው እግር ኳስን ብለን የእግር እሳት የሚሆነንን ፀፀት ባናተርፍ መልካም ነው።

 

አርሶ መራብና ተኩሶ መሳት፣

እያደር ይፋጃል እንደእግር እሳት።

 

ይህቺ እፎይ የምንልባት፣ ሞለል የምናገኝባት፣ አፍሪካ ደጃፍ የምንደርስበት ነው ብለን ተስፋ የጣልንበት እግር ኳሳችን እግር የሚያሳብርና አናት የሚያስቀረቅር አይነት ከሆነች ደግ አይሆንም። . . . ምንድን ነበር የተባለው ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ባደረጉት ጨዋታ ላይ ያ ሁሉ ሰው ተሰብሮና ተፈንክቶ፤ ስፖርታዊ ጨዋነት የሚባለው ነገር አፈር ከበላውማ ምን ዋጋ አለው። “ፋሲል ሲፈርስ፣ ጎንደር ይታረስ” ይሉትን ተረት ማስታወስ መልካም ይመስለኛል። ስፖርታዊ ጨዋነትም ሲፈርስ እንዲሁ የአገራችን ኳስ መታረሱ አይቀርምና ልብ ያለው ልብ ይበል።

 

እናላችሁ “አንድ ዓይን ያለው. . .” እንዲሉ እንደዓይን በምንሳሳለት አካላችን፣ ህይወታችን እና ስሜታችን ላይ አፈር እየበተንን መጫወት አንፈልግም። አሊያ ግን የበራ የመሰለን የኮንዶሚኒየም አይናችን፣ የበራ የመሰለን የእግር ኳስ አይናችን የበራለ የመሰለን፣ የመልካም አስተዳደር አይናችን የበራ የመሰለን፤ የነፃነት አይናችን የበራ የመሰለን፣ የዴሞክራሲ አይናችን ሁሉ አፈር ይገባበትና ጉድ እንሆናለን።

 

ለማንኛውም ሲከበር እልልታው ላይ፤ ሲሰራ ዕቅዱ ላይ ብቻ የምንገኝ ሰዎች በእልልታውም በዋይታው፤ በዕቅዱም በተግባሩም ላይ የምንታይ ቢሆን መልካም ነው። ለዛሬ ትዝብት አዘል ወጋችንን ከመቋጨታችን በፊት በቅርቡ ከወጣው የዮሀንስ ሞላ “የብርሃን ሰበዞች” ስብስብ ግጥሞች መካከል የምትከተለዋን እንካችሁ፤

 

ድግስ አዳኝ

እንባ ሲጠራረግ

እንዳ ‘ያ’ለፈ፣

ሙገሳ ሲታደል

ከፊት ተሰለፈ፤

ሲቃ ሲንቆረቆር

‘አልሰማሁም’ ያለ፤

ሳቅ ሲደሰፋ ባገር፣

ደምቆ ከፊት ዋለ።

            ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
624 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 961 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us