“አነሰ ሲሉት ቀነሰ”

Wednesday, 08 June 2016 12:14

          ጅማሬ ሰበብ

የሰው ልጅ፣

ጥፋቱን በሰው ላይ ሊያሳብብ ሲሞክር

በውሸት ማጭበርበር ማታለል ሲጀምር

የቆመውን ድንጋይ በካልቾ ነርቶ

“እንቅፋት መቶኝ ነው” ይላል አፉን ሞልቶ።

(“በዝናብ ቅጠሪኝ” ከተሠኘው

የአንዷለም ኪዳኔ የግጥም ስብስቦች የተወሰደ)

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?..... እኔ የምለው ምነውሳ የዘንድሮ ነገር ሁሉ “ወይኔ ጉዴ ፈላ!” የሚያሰኘን አይነት ሆነ።… የምሬን እኮ ነው። ከአምና ከካቻምናው ነገር እየባሰ “አነሰ ሲሉት ቀነሰ” ይሉትን ተረት የሚያስተርተን አልመሰላችሁም?... ለስንቱ ነገራችን ሰበብ ሰጥተን እንደምንዘልቀው እንጃ እንጂ ባዶ ምክንያታችንማ የ11 በመቶ እድገታችንን አረጋግጧል። መንግስትም፣ ፓርቲም፣ ተቋምም፣ አሠሪም፣ ሰራተኛም ብቻ ምን አለፋችሁ ሁሉም ለውድቀቱ የምክንያት አይነቱን ከወዴት እንደሚያመጣው አንድዬ ይወቀው። “የናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ…” ባዩ በዝቷል።

ሰበብና ምክንያት እየፈለጉ የሌላውን ሐጢያት አጉልተው የራሳቸውን ለመደበቅ እንደሚታትሩ ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች የሚታዘንለት ሰው ያለ አይመስለኝም። (ወዳጆቼ በነገራችን ላይ የሙስሊም ወገኖቻችን ታላቁ የረመዳን የጾም ወር በዚህ ሳምንት ተጀምሯል።… “ረመዳን ከሪም!” ማለት ያስፈልጋል)… የረመዳንን ጾምና ፀሎት ስናነሳ አንዲት ወግ ትዝ አለችኝ። … በአንድ ወቅት ነብዩ መሐመድ በተራራው ላይ ሳሉ አንደኛው ተከታያቸው ተጠጋቸውና የራሱን ዋጋ ከፍ፤ የሌሎቹን ደግሞ ዝቅ ለማድረግ አስቦ፣ “ነብያችን ይኸውልዎት ሦስቱ ወንድሞቼ ሌቱን ሙሉ እንቅልፋቸውን ሲለጥጡ እኔ ግን እስካሁን በትጋት ለአላህ ፀሎት እያደረስኩ ነው” አላቸው።

ነብዩ መሐመድም የሰውዬው ነገር ገብቷቸው ኖሮ፣ “አንተም እንደወንድሞችህ ብትተኛ ይሻልህ ነበር” አሉት። “አነሰ ሲሉት ቀነሰ” እንዲሉ አመሰግናለሁ ብሎ ሲያስብ ወቀሳ የገጠመው ይህ ሰው ዓይኑን እንዳፈጠጠ ነብዩ ንግግራቸውን ቀጠል አድርገው፤ “ምክንያቱም ፀሎትህ በሙሉ ሦስቱ ወንድሞችህ ላይ የሚቀርብ ወቀሳ ስለሆነ እርባና የለውም” አሉት ይባላል።

በሆነ-ባልሆነው እኛ ላይ ድንጋይ ለመወርወርና እኛን ለማስጠቆር ከሚተጋ ወዳጅ አንድዬ ይጠብቀን አቦ! በድካማችሁ ነጥብ ማስቆጠር ከሚፈልግ፤ በእንቅልፋችሁ ምስጋናን ከሚፈልግ፤ በድህነታችሁ ከሚሳለቅ ሰው አንድዬ ይጠብቃችሁ። አለልኝ ስትሉት የሚከዳ ወዳጅ ሲገጥማችሁ ወይም በሆነ ባልሆነው እናንተን ላለማግኘትና ላለመርዳት ሰበቡ ከበዛ የሚከተለውን የአርቲስት ታምራት ሞላን (ነፍሱን ይማረውና) ዘፈን አንድ አንጓ እንጋብዘዋለን።

ሰበቡ ነጠላ ለብሼው

ሰበቡ ነጠላ ለብሰሽ፣

ሰበቡ አሁን ከምን ጊዜው

ሰበቡ ድርብ አማረሽ።

ለማንኛውም ለፈተናው መሠረቅም ሰበቡ ብዙ ሆኗል አይደል?... በቃ እኛ ዘንድ ለተፈጠረው ችግር ሁሉ ሰበብ እየፈለጉ መለጠፍ እንጂ ኃላፊነት ወስዶ ከስልጣን ማማ ላይ መርገፍ በፍፁም የማይታሰብ ነገር ነው አይደል?... ኧረ የትምህርት ጥራት፣ ኧረ የመምህራን ነገር፣ ኧረ የት/ቤቶች ዋጋ መናር ምናምን ስንል ቆይተን፤ ይባስ ብሎ ሀገር አቀፍ ፈተናችንን ተሰርቀን አረፍነው። …. ይሄኔ ነው “አነሰ ሲሉት ቀነሰ” ማለት ወዳጄ!

ለነገሩማ ዘንድሮ ያልተሰረቅነው ነገር ምን አለ?.... ለስንትና ስንት ፕሮጀክት የመደብነው ገንዘብ የመሰረቅ ያህል ጠፍቷል። በጋምቤላ ያሉ ወገኖቻችን (ህፃናት) በሙርሌ ጎሳ አባላት ተሰርቀዋል (ከብቶቹ እንደሉ ሆኖ) ይኸው ደግሞ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናችን ተሰረቀ። ግድ የላችሁም ቀልባችንም በሆነ ነገር ሳይሰረቅ አልቀረምና ይፈተሽልን።

የፈተና ስርቆት ነገር ከተወሳ እስቲ ደግሞ አንዲት ጨዋታ እዚህች’ጋ እናንሳ።… እናት የልጇን የፈተና ወረቀት ስትመለከት በውጤቱ በጣም አዘነች። “ለመሆኑ በዚህ ፈተና እንዴት ይህን ዝቅተኛ ውጤት ልታመጣ ቻልክ?” እናት በቁጣ ልጇ ላይ አፈጠጠች።

“ውጤቴ ዝቅተኛ የሆነው ቀሪ በመመዝገቡ ነው” በልጇ መልስ የተገረመችው  እናት “በፈተናው ቀን ቀርቼ ነበር እያልከኝ ነው እንዴ?” ስትል በጥያቄ አፋጠጠችው። ይሄን ጊዜ ልጁ ምን ቢመልስላት ጥሩ ነው? “ኸረ እኔ አልቀረሁም፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ፈተና የሚያስኮርጀን የክፍላችን ጐበዝ ተማሪ በዕለቱ ቀርቶ ነበር” ብሎላችሁ እርፍ። (ቂ….ቂ…ቂ!) ይህቺ ናት ጨዋታ ማለት ይሄኔ ነው። ወዳጆቼ “አነሰ ሲሉት ቀነሰ” ማለት’ኮ የባሰ አለና አገርህን አትልቀቅ እንደማለት ነው።

ለማንኛውም ወዳጄ ሰበብ ፈጣሪም፤ ሰበብ ፈላጊም ከመሆን ይሰውረን። ለጠፋውም ጉድለት፣ ለመጣውም ውጤት ደፈር ብሎ ኃላፊነቱን የሚወስድ አያሳጣን አቦ!…. አልያ ግን ምክንያት እየደረደሩ መኖር በጣም ነው የሚደብረው። ቸር እንሰንብት!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1133 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 833 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us