ሰነፍ ጌታ ሲኖር. . .

Wednesday, 15 June 2016 12:40

 

በአሸናፊ ደምሴ

የዳኛ ምቀኛ፣ የስረኛ ንጹህ

የመኳንንት ቂል፣ የድሃ ብልህ

ያዋቂ ገልጃጃ፣ የሞኝ ብልሃተኛ

ያረመኔ መልካም፣ የቄስ አመፀኛ

የችግረኛ ቸር፣ የሃብታም ንፉግ

የወዳጅ ከሀዲ፣ የባላንጣ ደግ

መኖሩን አስተውለን በዚህ ዓለም ላይ

ጠልቀን ስናስበው መርምረን ስናይ

በጣም የሚያስቸግር ምስጢር አለበት።

ብልህ ሰው ይራባል ሲተርፈው ደንቆሮ

ጎበዝ ሰራተኛ ሲሞት ተቸግሮ

ሰነፍ ይጨፍራል በጌትነት ሰክሮ።

      (ከክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል፤ “የቅኔ ውበት” መፅሐፍ የተቀነጨበ)

 

እንዴት ሰነበታችሁ ወዳጆቼ? . . . እኔ የምለው ይህቺም እግር ኳሳችን የቱን ያህል አድጋ ነው እንዲህ ለተመልካቹ ሁሉ አደጋ የሆነችው?. . . የምሬን እኮ ነው ገና ለአቅመ ውጤት ያልበቃ እግር ኳስ ይዘን ዱላ ስንማዘዝ በጣም “ሼም” ነው። እስቲ እንደው ማን ይሙት ድብድብ ፍለጋ ሀገር -ለሀገር እያዞሩ ድንጋይ መወራወርን ምን ይሉታል?. . . ምን ታዘብክ አትሉኝም? ደጋፊው በውጤት ከስሮ፤ በድብድብ ምክንያት ታስሮ ስንቱን ይችለዋል? እግረ -መንገዳችንን ምክር አለን እግር ኳሳችንን “የጨበራ ተስካር” እያስመሰላችሁ፤ የስፖርት ዘገባውን ሁሉ የትራፊክ አደጋ ሪፖርት እንዳታስመስሉት ጎበዝ! . . . ለማንኛውም ባለቅኔው እንዳሉት እኛም በአፅንኦት እንላለን፡-

 

ብልህ ሰው ይራባል ሲተርፈው ደንቆሮ

ጎበዝ ሰራተኛ ሲሞት ተቸግሮ

ሰነፍ ይጨፍራል በጌትነት ሰክሮ።

 

እናላችሁ ምንም በሌለበት ከንቱ ጌትነት እያሰከረን በረባ ባረባው ድንጋይ የምንወራወር፤ ቃላት የምንወራወር፤ ዱላ የምንወራወር በስልጣን ጉልበት የምንወራወር፣ በእንጀራ ገመድ የምንጓተት በዝተናል።

 

እኔ የምለው ይህቺ ፌስ,ቡክ አካባቢ የነበረችን ሞቅ-ደመቅ ያለች ወግ በህግ ታሰረች እንዴ?. . . የምሬን ነው አዋጅ ወጣ ብሎ ሁሉም ከፌስ ቡክ ደጃፍ እልም ካለ ማርክዙከንበርግ ምን ሰርቶ ሊበላ ነው ጎበዝ? ቂ-ቂ-ቂ- የምር ግን ሕጉ፣ መመሪያው፣ ማስፈራሪያና ዛቻው የበዛ አልመሰላችሁም። ለማንኛውም እኛም በሕገመንግስቱ አንቀፅ 29 ጥላ ስር ሆነን፤ የመናገር መብታችንን ለማረጋገጥ ሽንጣችንን ገትረን እንሰራለን። (የምር ግን ዝንቤን እሽሽ ትልና ወየውልህ የሚለን በዛብን እኮ፤. . . እኛ ምን አገባን ከዝንቡ ጋር መቀመጥ ከፈለገ ግድ የለም እንተወዋለን ቂ-ቂ-ቂ)

 

የፌስ ቡክ ነገር ከተነሳ አይቀር የምትከተለዋን ጨዋታ እንካችሁ። ልጄ ልጅቷን በውስጥ መስመር “ሲጀነጅናት” ከርሟል። ታዲያ አንድ ቀን ያበጠው ይፈንዳ ብሎ “I got married” (አግብቻለሁ) የሚል ፅሁፍ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ለጠፈ። በርካታ ወዳጆቹ የእንኳን ደስ ያለህ መልክት ሲያደርሱት ያቺ ትጀነጀን የነበረችው ልጅ ግን የስድብ መአት አዘነበችበት ይሄን ጊዜ ብድግ አድርጎ ጥቁር መዝገቡ (Block list) ውስጥ ይከታታል። በዚህን ጊዜ እርር- ድብን ያለችው ወጣት በልጁ የግል ስልኩ ላይ ደወለች። ልጁም እስቲ ልስማት ብሎ ስልኩን ከማንሳቱ ከእሷ የማይጠበቅ፤ ለመፃፍ የሚከብድ የቃላት ጥይት ታወርድበት ጀመር። በመጨረሻ ልጁ ምን ቢላት ጥሩ ነው፤ “የኔ እህት ድሮም አንቺን ያልመረጥኩት ይሄን ምላስሽን ፈርቼው ነው” ብሎላችሁ እርፍ።. . . እኔ የምለው ዘንድሮ ሲዋደዱ ክንፍ፤ ሲጠላሉ ሰይፍ የሚማዘዙ ሰዎች አልበረከቱላችሁም?

 

እስቲ ደግሞ ከወደናይጄሪያ የተገኘችውን ፌስ-ቡክ ቀመስ ጨዋታ ልጨምርላችሁ። ሰውዬው ውሻውን ታቅፎ የተነሳውን ፎቶ በፌስ-ቡክ ገፁ ላይ ይለጥፋል። በዚህ ጊዜ ከዚህ ቀደም ፍቅረኛው የነበረች ወጣት በሆዷ ቂም ቋጥራ ኖሮ በአስተያየት ገፁ በኩል ገብታ “አንተ ግን የትኛው ነህ?” ስትል ጠየቀችው። ሰውየው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው? “አንቺን ያቀፍኩት ነኝ?” ቂ-ቂ-ቂ- ይህቺ ናት ጨዋታ ማለት ይሄኔ ነው።

 

ለማንኛውም በእግር ኳስ ሜዳውም፣ በማህበራዊ ሚዲያውም፣ ሆነ በየስብሰባው ላይ ድንጋይም ሆነ ነገር እንዲሁ እያነሳችሁ በመለጠፍ አገር እንዲረበሽ የምታደርጉ ሁሉ ታቀቡልን። ስፖርታዊም ሆነ ማህበራዊ ጨዋነታችንን ጠብቀን ሀሳብም አስተያየትም እንድናዋጣ ይፈቀድልን አቦ! . . .  አንድዬ ብቻ ከሰነፍ ጌታ ይጠብቀን ለማንኛውም በድጋሚ በባለቅኔው ስንኝ አፅንኦት በመስጠት እንሰናበታለን።

 

ብልህ ሰው ይራባል ሲተርፈው ደንቆሮ

ጎበዝ ሰራተኛ ሲሞት ተቸግሮ፣

ሰነፍ ይጨፍራል በጌትነት ሰክሮ።

                    ቸር እንሰንብት!!! 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
614 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1087 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us