“አባትና ጋሻ….”

Wednesday, 22 June 2016 12:08

 

አባት እና ልጅ

“ጎዳናው ድንግል ነው፣ አሻራም የለበት

ከቀደሙት ወገን ማንም አልሄደበት

ይላል አመንትቶ፣

አባቱ ባለክንፍ መሆኑን ዘንግቶ።”

(ከበዕውቀቱ ስዩም - “ስብስብ ግጥሞች” የተወሰደ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?... እነሆ የአባቶች ቀን ሰኔ 12 ቀን 2008 ዓ.ም ታስቦ ዋለ። እኛም “አባት ሳለ አጊጥ ጀንበር ሳለ ሩጥ” እንዲሁም “አባትና ጋሻ ምስክር አያሻ” በሚል ብሂል ዛሬን አባቶች ላይ አተኩረን እንጨዋወታለን። … ገጣሚው እንዳለው አባቶቻችን ከእኛ በእጅጉ የመጠቁና የረቀቁ ብቻ ሳይሆኑ፤ አንዳንዴም ቢሆን የፀደቁ አሉና ክብር ይገባቸዋል። እነሆ ለዛሬ ትዝብት አዘል ጨዋታችንን በአንዲት ዓለም አቀፍ ምርጥ ታሪክ እንጀምራለን።

ሰውዬው እውቅ አናጢ ነው። አባቱ ያለ እናት ያሳደጉት ብቸኛ ልጃቸው በመሆኑ የእርጅና ዘመናቸውንም አብረውት ያሳልፉ ነበር። በአናጢነቱ አገር ያወቀውና ገቢውም መልካም የሆነው ይህ ሰው፤ ለአባቱ አስፈላጊውን እንክብካቤም ሆነ በቂ ምግብ ባለመስጠቱ የተነሳ ሽማግሌ አባቱ በጣም ደካማ ሆነዋል። አቅም ያነሳቸው ከመሆኑ የተነሳ በሚገባ መራመድ እንኳን እየተሳናቸው ቤት መዋል የዘወትር ተግባራቸው ሆነ።

ዘወትር ስስ እና ትንሽ በሆነች የሸክላ ዝርግ ሰሀን ጥቂት የሩዝ ምግብ ይቀርብላቸዋል። እንዴት ተቸግረው እንዳሳደጉት አገር የሚያውቅላቸው እኚህ ሽማግሌ የልጃቸው እንዲህ ክፉ መሆን ከየት የመጣ እንደሆነ ሊገባቸው አልቻለም። ይባስ ብሎ ምሽት ላይ ጠጥቶና ሰክሮ ሲመጣ አባቱን ከፍ ዝቅ እያደረገ ይሰድባቸው ጀመር።

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን አናጢው ሰውዬ በቤቱ ነገሮችን አጥብቆ የሚታዘብ የአስር ዓመት ህፃን ልጅ ነበረው። በአባቱ ተግባር እያዘነ፤ በአያቱ ሁኔታ የመጠቃት ስሜት እየተሰማው ሁሉንም ነገር የሚታዘብ ባለ ብሩህ አእምሮ ህፃን ነው። ከወለደው አናጢ አባቱ በላይ አያቱን አጥብቆ ይወዳቸዋል።

ከዕለታት በአንዱ ቀን አናጢው ሰው እድሜ ለተጫጫናቸው አባቱ ጥቂት ምግብ በተሰነጣጠቀው የሸክላ ዝርግ ሰሃን ላይ ሰጣቸው። ያም ሆኖ የሸክላ ሰሃኑ ዕድሜው አልቆ ኖሮ ተሰባበረ። ለአዛውንቱ የተሰጣቸውም ጥቂት ምግብ መሬት ፈሰሰ። ከስራ ቦታው ሲመለስ የአባቱን የምግብ ሰሀን መሰበር የተመለከተው አናጢው ሰው፤ በሽማግሌው ላይ በቁጣ የተሞሉ መጥፎ ቃላትን አዘነበባቸው። በልጃቸው ንግግርና ሁኔታ በእጅጉ ቢያዝኑም፤ አንዳችም ክፉ ከመናገር ይልቅ ለእርሱ ጥፋት እርሳቸው “ይቅርታ” ጠየቁት።

ይህንን ሁሉ ነገር ይመለከት የነበረው የአስር ዓመቱ ልጅ፤ አባቱን ይበልጥ ጠላው። ቢሆንም አባቱን በይፋ ደፍሮ ፊት ለፊት መናገር አልቻለም። ያም ሆኖ በቀጣዩ ቀን ህፃኑ ልጅ ከአባቱ ጥቂት የአናጢ መሳሪያዎችንና እንጨቶችን በመውሰድ ምርጥ የሚባል የእንጨት ሰሃን ይሰራ ጀመር። ይህን ተግባሩን ያስተዋለው የልጁ አባት፣ “ምን እየሰራህ ነው ልጄ?” ሲል በመገረም ጠየቀው። “የእንጨት ሰሃን እየሰራሁ ነው” ልጅ መለሰ። “የእንጨት ሰሃን! ለማን?” አባት በልጁ ተግባር መደነቁ ጨምሯል።

“ይህን ጠንካራ የእንጨት ሰሃን የምሰራው ለአንተ ነው አባቴ፤ ለጊዜው ግን አያቴ ይመገብበታል። ወደፊት ምናልባት አንተም እንደ አያቴ ስትሸመግል የመመገቢያ ሰሃን ያስፈልግሃል። አያቴ ለአባቱ የሸክላ ሰሃን በመስራቱ ነው ዛሬ እርሱም በሸክላ ሰሃን ለመብላት የተገደደው። ይህንን ታሪክ የነገረኝ ራሱ አያቴ ነው። እናም እንደ አያቴ አይነት የሸክላ ሰሃን ብሰራ ምናልባትም በአንተ የሽምግልና ዕድሜ በቀላሉ ሊሰበር ይችላል። ከተሰበረ ደግሞ አንተ አያቴን እንደሰደብከው እኔም አንተን በቁጣ ተሞልቼ ልሰድብህ እችላለሁ። አሁን ግን ለአያቴ የምሰራው ጠንካራ የእንጨት ሰሃን እግረ-መንገዱንም ለአንተ የሚሰራ በመሆኑ በቀላሉ አይሰበርም።” ሲል አስረዳው።

አባት የልጁ ንግግር ከሚቋቋመው በላይ ሆነበት። …. እርሱ ከዚህ ቀደም በአባቱ ላይ የፈፀማቸው ስህተቶች ሁሉ ወለል ብለው ታዩት። ልጅ እያለ አባቱ ምን ያህል ይንከባከበው እንደነበር እያሰበ፤ አሁን በአዛውንት አባቱ ላይ በፈፀመው ተግባር ሊፀፀት እንደሚገባው በራሱ ልጅ በኩል ተገለፀለት።… እናም ራሱን ለመቀየርና መልካም ሰው ለመሆን ተነሳ። የእርሱን አባት፤ የልጁን አያት በሚገባ መንከባከብና መጦር ጀመረ። “ሰው የዘራውን ያጭዳል” እንዲል መፅሐፉ።

ይህ ታሪክ “የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ” ሲል ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ያቀነቀናትን ዘፈን ያስታውሰናል፤ አባቶቻችንን ማክበርና መንከባከብ ካልቻልን፤ የእኛም ዕጣ ፈንታ በልጆቻችን እንዲሁ ነው።… አባት ቤቱ እንዳይጐድል፤ እኛ እንዳንከፋ፤ ከሰው እንዳናንስ፤ ላቡን የሚያፈስና ለእኛም ሲል ክብሩን የሚያዋርድ ታላቅ ምሰሶ ነው።…. አባት ጋሻና መከታም ጭምር ነው። በቅርብ የማይታይ ነገር ግን ከሩቅ የሚያብረቀርቅ ተግባር ያላቸው በርካታ አባቶች በዙሪያችን አሉና “መልካም የአባቶች ቀን” ሊባሉ ግድ ነው።…. ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
534 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 949 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us