በሰልፍ ስንንሳፈፍ. . .

Wednesday, 29 June 2016 12:36

ዝምድናችን እንኳን በውል አልታወቀ

እቴነሽ እያሉ አካላቴ አለቀ።

           (እንዲል ባለቅኔ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . እህሳ የሰሞኑ ሰልፍ እንዴት አገኛችሁት?. . . እኔ የምለው የኤርትራን መንግሥት ለማውገዝ ነው ብለው አደባባይ የወጡት ሰልፈኞች ይሄን ያህል ሰልፍ ናፍቋቸው ነበር እንዴ?. . . የምር ግን ሰልፉእኮ የፌስቲቫል እንጂ የተቃውሞ አይመስልም ነበር። (አለ አይደል “ክሬዚ ዴይ” ምናምን እንደሚሉት አይነት ማለት ነው). . . እግረመንገዳቸውን የኛ ሀገር ተቃዋሚዎችም ሰልፉን ቢደባለቁ ኖሮ ነፍስ- ይዘሩበት ነበር የሚል አሉባልታዎችን መስማቴን አልደብቃችሁም። . . . ግድ የላችሁም እኛ ሰልፍ ተከልክለን ለእነርሱ (ለኤርትራውያኑ) እንዴት ተፈቀደላቸው የምትሉ ሁሉ ለኛ ሰልፍ የዕለት ተግባራችን ሆኗል በሚል የተተው እንደሆነ ልብ አድርጉ። እውነቴን እኮ ነው፤ ደግሞ እንደኛ አመቱን በሙሉ የሚሰለፍ ህዝብ አለ እንዴ?. . . ሰልፍ ከእኛ በላይ ላሳር አለች አሉ ቂ-ቂ-ቂ ለዳቦው፣ ለታክሲው፣ ለሲኒማው፣ (ይሄ እንኳን ከቃና በፊትና ከቃና ቲቪ በኋላ ተብሎ በሁለት ይፈከላል) ጉዳይ ለማስፈፀም የምንሰለፈውና ወገባችን የሚንቀጠቀጥብን እያለ ተጨማሪ ሰልፍ ምን ያደርግልናል ጎበዝ (ቂ-ቂ-ቂ!)

ለማንኛውም ያለፈውን ሳምንት የሰልፍ ሁኔታ የታዘበው አንድ ወዳጄ ብሶት የወለደው፤ ቅናት የጋረደው አይነት አንድ ለናቱ አይነት የሆነች ግጥም ገጥሞ እንደሚከተለው አንብቦልኛል።

 

አንዳንዴ በስተቀኝ

አንዳንዴ በግራ፣

ሰልፍ እንደሆን ሞልቷል

በተራ -በተራ።

ለትራንስፖርቱ -ለታክሲ ለባሱ

ለእንጀራ ለዳቦ ሰልፍ አለ በስሱ

ለምደነዋል እኛ ይድላቸው “ለነሱ”።

“ጦርነቱ ይቀር -ፖለቲካው ይስመር!

በፍጥነት ይተግበር - መልካም አስተዳደር!

ፍትህ አይጓደል - መጠየቅም ይኑር!”

ብለን እንዳንፎክር

መሪ እንዳናማርር

የለንም መፈክር።

ብርቃችን አይደለም

ሰልፍ እንደሆን ሞልቷል፣

ተርታ ተሰልፈን ወይ ዘንድሮ እንድንል፣

ጦርነቱ ሳይሆን ኑሮ አስገድዶናል።

 

ኧረ ጎበዝ ብሶት ለካ ይሄን ያህል ሰውን ባለቅኔ ያደርጋል?. . .ይብላኝልን ኑሮ አስገድዶ በየዕለቱ አደባባይ ያለመፈክር ለሚያሰልፈን። . . . እኔ የምለው የሰልፍ ነገር ሲነሳ ከጲላጦስ “ጥበብ” መፅሐፍ ላይ የምትከተለዋን የምዕራባውያን ቀልድ እንካችሁ። . . . በምድር ላይ የነበረው የሰው ዘር ሁሉ ይሞትና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይሄዳል። ታዲያ በዚያ እግዚያብሔር ለሁሉም አንድ ትዕዛዝ ይሰጣል። ይህም ወንድን የበደሉ ሴቶች በግራ በኩል እንዲሰለፉና እንዲመዘገቡ ነበር። ሴቶች በሙሉ ይሰለፉና ይመዘገባሉ። ምዝገባው ሲያልቅ በሉ ወደገነት ሂዱ ይላቸዋል።

 

የወንዶች ተራ ይደርስና በሴት የተበደላችሁ ወንዶች በአንድ መስመር፤ ሴትን የበደላችሁ ደግሞ በሌላ መስመር ተሰለፉና ተመዝገቡ ይላል። በሴት የተበደሉት ሰልፍ በወንዶች ሲሞላ፤ ሴትን በበደሉት ሰልፍ ላይ የቆመው ግን አንድ ወንድ ብቻ ነበር። እግዚያብሔር ሰልፉን ሲመለከት በጣም ይቆጣና፣ “እናንተ በእኔ መልክና ምሳሌ ሰርቻችሁ በሴት ስትበደሉ  መኖራችሁ ሊያሳፍራችሁ ይገባል። በእርሱ ደስ የሚለኝ አንዱ ልጄን ተመልከቱት፤ ከእሱም ተማሩ። ልጄ ሆይ በአንተ ኮራሁ። እንዴት በእዚህ ሰልፍ እንደገባህ በል ለሌሎቹ ንገራቸው” በማለት እግዚያብሔር አዘዘው።

 

ሰውዬው ግን ግራ በተጋባ መንፈስ፣ “ጌታ ሆይ! በዚህ ሰልፍ ለብቻዬ መቆሜ ለእኔም ግራ የገባኝ ነገር ነው። ምክንያቱም በእዚህ በኩል እንድሰለፍ ያዘዘችኝ ሚስቴ ነበረች” በማለት መለሰለት። . . . ይህቺ ናት ጨዋታ ማለት ይሄኔ ነው።

 

ጎበዝ ተገዶ ሰልፍ ከመግባትና ሰልፍ ከመስራት ይሰውረን አቦ! . . . ለማንኛውም ወዳጄ እንዳለው መፈክርና ወረቀት ማቃጠል አንችልም እንጂ ደጋፊ ብቻ ሳይሆን ነቃፊ ሰልፍ ስንት በሆዳችን አለ መሰላችሁ። . . . በሰልፍ ስንንሳፈፍ ውለን ማደራችንን “ጌቶቻችን” ቢያዩልን ጥሩ ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል የኛ ሰልፍ ለዜናም ሆነ ለለውጥ የሚያበቃን አለመሆኑ ነው። እንጂማ “ምግብማ ሞልቷል” ሳይሆን ሰልፍማ ሞልቷል የሚያስብለን ነገር ጎበዝ እጅግ በዝቷል።. . . እናላችሁ . . . አለመሰለፋችንን፣ አለመፎከራችንን፣ አለማውገዛችንንና ድምጽ አለማውጣታችንን ብቻ ሳይሆን ዝምታችንንም የሚረዳ “አለቃ” ይመጣ ዘንድ እንመኛለን።. . . ቸር እንሰንብት።  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
486 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1037 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us