ነገር ጠበቅና ጨመቅ

Thursday, 07 July 2016 15:04

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . ለሙስሊም ወገኖቻችንም “ኢድሙባረክ” ብለናል!!! እነሆ በዛሬ የትዝብት ጨዋታችን መነሻ ትሆነን ዘንድ ከሙላህ ነስሩዲን ወጎች አንዷን እንካችሁ። ሙላህ ነስሩዲን እንደበሬም እንደገበሬም ሲለፋ ውሎ ቤቱ ገባ። በጣም ርቦት ስለነበርም ባለቤቱ ምግብ እንዳቀረበችለት ያለወትሮው በሁለት እጁ መጉረስ ጀመረ። በሁኔታው ግር የተሰኘችው ሚስት፣ “ነስሩዲን ምን ሆነህ ነው በሁለት እጅህ የምትበላው” ብትለው ርሃቡ የጠናበት ነስሩዲን ምን ቢመልስላት ጥሩ ነው? “ምክንያቱም ሶስት እጅ ስለሌለኝ ነው” ቂ-ቂ-ቂ

 

እንዲህ ነው እንግዲህ ነገር ሲጠናብን፤ ነገርም ልክ እንደርሃብ ሲጠናብን እንደዚህ ነው የሚያደርገን ፍቅርም ሲጠና እንዲሁ ነው። ልቤን ውሰጂው ቀልቤን መልሺው የሚል ሰው እንዳለ ሳታለም የተፈታ ነው። ለምሳሌ አንዳንዱ ከመሬት ተነስቶ “ልቤን ሰረቀችው'ኮ” ሲል፤ ሌላው አሽሟጣጭ ደግሞ፣ “አሁን ይህቺ ምኗ ነው ልብ የሚሰርቀው” ይላል። ያሽሟጠጣችሁት ሰውዬ ለካንስ ፍቅሩ ፀንቶበት ኖሮ የልቡ መሰረቅ ሲገርማችሁ ይባስ ብሎ፣ “ነፍሴን ላንቺ ሰጥቻለሁ” ሲል ልትሰሙት ትችላላችሁ። ይሄኔ ታዲያ እንዲህም ይባላል እንዴ? ትሉ ይሆናል።

 

አንዳንድ ሰው ነገሩ ይበልጥ ግራ ሲያጋባ ጨዋታ ይፈጥራል። ጠበቅና ጨመቅ አድርገው ሲጠይቁት የሚደንቅ ምላሽ ልክ እንደነስረዲን ይሰጥና ፈገግ ያሰኘናል። እዚህች'ጋ አንዲት ቆየት ያለች የፍርድ ቤት አጋጣሚ ላውጋችሁ። ነገርዬዋን ወዳጄ ነው በአይኔም አየሁ፤ በጆሮዬም ሰማሁ ብሎ ያጫወተኝ። ሰውዬው ሚስቴ ስትሰርቅ (ስትማግጥ) ይዣታለሁ፤ ሲል ክስ ይመሰርታል። ጉዳዩን የያዙት ዳኛውም ክሱን የሚያስረዳ ምስክር እንዲቀርብ ያዛሉ። በታዘዘው መሠረት የሰውዬው ሚስት ወስልታበታለች የተባለበት ሆቴል ጠባቂና በወቅቱም መልዕክተኛ የነበረ ሰው ለምስክርነት ችሎት ይቀርባል።

 

ዳኛ - ስራዋ ምንድው?

ምስክር - የሆቴል ጥበቃ

ዳኛ - ዛሬ ለምንድው የመጡት?

ምስክር - ያየሁትን ልመሰክር

ዳኛ - ተከሳሿን ያውቋቸዋል?

ምስክር - ከአንድ ቀን በቀር ፍፁም አይቻቸው አላውቅም ክቡር ፍርድ ቤት

ዳኛ - መቼ ነው እናንተ ሆቴል የመጡት?

ምስክር - በቅርቡ ነው። ገና ሲገቡ ጠርተውኝ እኔን የሚፈልግ ሰው ይመጣል። “እገሌ”   ይባላል። ሲጠይቅህ ያረፍኩበትን ክፍል አሳይልኝ ብለው ጉርሻም ሰጥተውኝ ነበር።

ዳኛ - ከዚያስ?

ምስክር- ከዚያም የተባለው ሰው መጣ። እኔም እሜቴ ያረፉበት ክፍል ድረስ መርቼ ወሰድኩት።

ዳኛ - ከዚያስ?

ምስክር - ከዚያማ ሰውዬው ወደውስጥ እንደገቡ በሩ ተዘጋ፡፤

ዳኛ - ከዚያስ?

ምስክር - (ይሄኔ ምስክሩ ከተቀመጠበት እንደመነሳትም፤ በችሎት ያለውን ሰው እዩኝ ፍረዱኝ እንደማለትም እየቃጣው) ክቡር ዳኛ ከዚያስ ይባላል እንዴ? . . . ሰውዬው እንደገባ በሩ ከውስጥ ተዘጋ አልኮዎት እኮ! ብሎ በችሎቱ የታደመውን ሰው ሁሉ ፈገግ አሰኝቷል።

አንዳንዴ “ከዚያስ ይባላል እንዴ?” የሚያስብለን ስንት ዓይነት ጉዳይ አለ መሰላችሁ። ይህቺን አጋጣሚ ስሰማ አንዲት ቅኔ ትዝ አለችኝ።

 

ጠጅ አማረኝ ስላት ማሩን ታስጭናለች

ራበኝም ስላት እህል ታስጭናለች

በረደኝም ስላት ሸማ ትልካለች

ሌባዬ ተይዛ ባልጋ ትሄዳለች።

 

እናላችሁ ነገር ሲከርና ነገር ሲጠና ይዞ የሚመጣው ምላሽ አይታወቅምና መረጋጋቱ ሳይሻለን አይቀርም። “አጥብቆ ጠያቂ የናቱን ሞት ይረዳል” እንዲሉ ነገርን ጠበቅና ጨመቅ ስናደርግ ወይ ፈገግ ወይም ደግሞ ትንግርት የሚያሰኘን ነገር አናጣም። . . . “ተቀምጠው የሰቀሉት ቆመው ለማውረድ ይከብዳል” ይሉን ተረት የሚያስታውሰን ይሆናል። አንዳንዴ በመሪዎች ደረጃ፣ በአለቆች ደረጃ፣ በህጻናት ደረጃ የማትጠብቁትን ነገር ስትሰሙ ወይም ስትጠየቁ “እንደዚህም ይባላል እንዴ?” ብላችሁ ነገር ሽው ሊላችሁ ይችላል። ለማንኛውም ከመሠነባበታችን በፊት ይህቺን ጨዋታ እንካችሁ።

 

ሰውዬው በጠና ታሞ በጣረ-ሞት እንደተያዘ ሚስቱን አስጠርቶ መናዘዝ ይጀምራል። “እንግዲህ እኔ መሞቴ ነው። አንቺ ግን ያለባል መቅረት የለብሽም፤ እንዲያውም ያንን በላቸውን አግብተሽ አብራችሁ ኑሩ” ይላታል። በዚህ በባሏ ኑዛዜ የተናደደችው ሚስት፣ “አንተን ይማርልኝ እንጂ እኔ አሁን ስለባል አላስብም።. . . ደግሞ ባገባስ ያንተ ዋነኛ ጠላት የሆነው በላቸውን እንዴት አግቢው ትለኛለህ?” ስትል ነገሩ ብክንክን እያደረጋት ጠየቀችው።

 

በዚህ ጊዜ በማጣጣር ላይ የሚገኘው ባል ምን ቢል ጥሩ ነው? “አንቺ ደግሞ አይገባሽም እንዴ? በላቸው ቀንደኛ ጠላቴ መሆኑን መቼ አጣሁት? ይልቅስ እሱን አግቢውና ልክ እንደኔ አንገብግበሽ ቶሎ ግደይልኝ” ብሎላችሁ እርፍ ቂ-ቂ-ቂ ይህቺ ናት ኑዛዜ ማለት ጎበዝ!

 

ለማንኛውም ነገር ሲከር ግርግር መፍጠሩ፤ ተናግሮ አናጋሪም መጥራቱ አይቀርምና ከጠበቀና ከከረረ ነገር ሁሉ አንድዬ ይጠብቀን አቦ!. . . ነገርን ጠበቅም ጨመቅም ማድረግ ውጤቱ እኛ ከጠበቅነው በተቃራኒ ሊሆን ይችላልና ጠንቀቅ እንበል። እናም “ ነገር ቢበዛ በአህያ አይጫንም” እንዲሉ ነገራችንን እዚህች'ጋ ብንቋጭስ ምን ይሉናል? ምንም። ቸር እንሰንብት!!!

  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
506 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1080 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us