“ደህና ሲታጣ. . .”

Thursday, 14 July 2016 16:04

በአሸናፊ ደምሴ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

የዘመኑ ፀሎት

እባክህ አምላኬ ልለምንህ ስማኝ

የሰው አውራ ጠፍቶ እኔን ንጉስ አርገኝ

ዘቅዝቄ ልያቸው አሻቅበው ያዩኝ።

      (ከእርቅይሁን በላይነህ “እርቃንሽን ቅሪ” የግጥም መድብል የተወሰደ)

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . እነሆ ሰሞኑን “የተማረ ይግደለኝ” ለሚለው ማህበረሰባችን በርካታ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተመርቀውለታልና እንኳን ደስ ያለን።. . . እኔ የምለው ምርቃቱስ ሸጋ ነው ይሄ የክብር ዶክትሬት የሚሉት ነገር ግን እንዴት ነው ከመደበኛ ተመራቂዎች በላይ የተጋነነ አልመሰላችሁም? ግድ የለም ጎበዝ እኛም ትከሻችንንና አንገታችን ላይ የሚያጠልቅልን የብርም ይሁን የክብር ማዕረግ አይጠፋምና ተግቶ መጠበቅ ነው። የምር ግን በዚህ ፉክክራችን ድንገት ሳናስበው የሚያጠልቅልን ዩኒቨርስቲ የሚጠፋ አይመስለኝም። ለማንኛውም “የበላና የተማረ ወድቆ አይወድቅም” ሲባል ሰምተን መማሩን ትተን መብላቱ ላይ ብቻ በርትተን ቦርጭና ጉንጭ ያትረፈረፍን ሰዎች በዝተናል መሰለኝ። ሀሳባችን ሁሉ ከዕውቀት ይልቅ ውፍረት ላይ ያተኮረ ሆኗል።

 

ለማንኛውም ተመራቂዎችን የሰው ውራ ሳይሆን የሰው አውራ ያድርግልን።. . . ገጣሚው እንዳለው አውራ ሰው ጠፍቶ “ዘቅዝቄ ልያቸው” ከሚል ስብእናም ይጠብቀን።. . . እዚህች'ጋ አንዲት ሰሞነኛ ጨዋታ እንካችሁ። (መቼም የአውሮፓ ዋንጫ በፖርቹጋል አሸናፊነት ተጠናቀቀም አይደል? እንግዲህ አሁንስ ምን ቀረ የሚል ካለ የቀረን “ወሬው” ነው መልሳችን። ከዚህ በኋላ የዝውውር መስኮቶች ተከፍተው ወሬው ሁሉ እገሌ ከዚህ መስኮት ወደዚህ መስኮት እገሌ ከዚህ ክለብ ወደዚያኛው ክለብ ተዘዋወረ ይሉትን “ወሬ” ስናመነዥክ መክረም ነው)

 

እናላችሁ ተጫዋቹ በሞቀ ግጥሚያ መካከል ጉዳት ይደርስበትና ሜዳ ላይ ይወድቃል። ይሄን ጊዜ የራሱ ቡድን ተጫዋች የሆነ ሌላ ልጅ ወደ ወደቀው ተጫዋች ጎንበስ ብሎ ምን ቢለው ጥሩ ነው? “ስማ ህመምህን ዋጥ አድርገህ ቶሎ ብትነሳ ይሻልሃል፤ ቡድናችን እንደው “ስኳዱ” (ስብስቡ) ብዙ ነው ይህንን ቦታ ድጋሚ ላታገኘው ትችላለህ”፤ የቦታውን መነጠቅና የተቀያሪ ወንበር ደንበኛ መሆን ስጋት የፈጠረበት ተጫዋች ምንም ጉዳት እንዳልደረሰበት ሆኖ ጥርሱን ነክሶ ተነሳ። ጨዋታው ቀጥሎ የተፈጠረው ነገር ቡድኑን ዋጋ የሚያስከፍል ነበር። ድንገት በተጎዳው ተጫዋች በኩል የመጣች ኳስ ጎል ሆና ትቆጠርና ቡድኑ ተሸነፈ። እናም የሚቀየር ጤነኛ ተጫዋች የሞላው ቡድን “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” በሚል ስግብግብ ተጫዋች ምክንያት ሸንፈትን ቀመሰ። ገጣሚው እንዳለው በሆነ ባልሆነው ነገር ሁሉ “የሰው አውራ ጠፍቶ እኔን ንጉስ አርገኝ” የሚሉ ዘመነኞች በበዙበት በዚህ ጊዜ የቡድን ነገር፣ የቤተሰብ ነገር፣ የተቋም ነገር፣ የፓርቲ ነገር፣ የሃይማኖት ነገር፣ የሀገር ነገር ግድ ሳይላቸው ራሳቸውን ብቻ የበቁ የነቁ ሲያደርጉ መዘዙ ለኛም መድረሱ አይቀርም። ለምን ቢባል፣ “ለአጣን የመጣ ለፃድቃን ይተርፋል” ነውና።

 

እናላችሁ በብዙ መስኮች ለሚገጥመን ችግር፤ ለመልካም አስተዳደር እጦትና ለሙስና ከሚያጋልጡን አብይ ምክንያቶች ዋነኛው ትክክለኛው ሰው ጠፍቶ በጎደለ ሙላ “ንጉስ ነኝ” የሚል ወንበርተኛ ለመብዛቱ ነው። እናም “ደህና ሲታጣ ይመለመላል ጎባጣ” እንዲሉ ደህና ስናጣ የተመለመሉ የስራ ጎባጣዎች፣ የአመለካከት ጎባጣዎች፣ የአፈፃፀም ጎባጣዎች፣ የአመራር ጎባጣዎች ሁሉ የኃላፊነት ወንበሩን ይዘው ሲያበቁ በልባቸው ግን፣ “ዘቅዝቄ ልያቸው፣ አሻቅበው ይዩኝ!” የሚሉ አይነት ሆነዋል።

 

እነዚህን መሰል የዘመናችን ፀሎተኞች አምላካቸውን የሚለምኑት እነርሱ በርትተውና እነርሱ ተሸለው የተሻለ ቦታ እንዲያገኙ ሳይሆን፤ የተሻለ የሚሉት ሰው ጠፍቶ እነርሱ እንዲነግሱ ብቻ ነው። እናም እውቀታቸው፣ ስልጣናቸውና ኃላፊነታቸው ሁሉ እንኳንስ ለሌላው ይቅርና ለራሳቸውም አይሆናቸውም። ነገራቸው ሁሉ “የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም” እንዲሉ ናቸው።

 

እስቲ ደግሞ ለራሳቸውም ስለማይሆኑ የዘመናችን አዋቂዎች ናይጄሪያዊው ቀልደኛ የተሳለቀበትን ወግ እንካችሁ።. . . አምስት ሰዎችን ጭና ስትጓዝ የነበረች የሀገር ውስጥ መለስተኛ አውሮፕላን የሞተር ብልሽት ይገጥማትና የመከስከስ አደጋ እንደሚገጥማት እውን ይሆናል። በአውሮፕላኗ ውስጥ የነበረው የአደጋ ጊዜ ጃኬት (ፓራሹት) ደግሞ አራት ብቻ ስለነበር ማን ቀርቶ ማን እንደሚተርፍ አምስቱ ሰዎች ጭንቅ አላቸው። ድንገት ግን አንደኛው ተነስቶ እወቅ የእግር ኳስ ተጫዋች መሆኑን እና ለሀገሩ የሚገባውን ሳያደርግ ገና በወጣትነቱ መሞት እንደሌለበት ተናግሮ አንዱን ፓራሹት ይዞ ይወርዳል።

 

ሁለተኛውም በአፍሪካ ካሉ ሀብታሞች አንዱ  መሆኑን ተናግሮ፤ ገና የምሰራው ብዙ ነገር አለ በሚል አስቦ አንዱን ፓራሹት ይዞ ይወጣል። ሶስተኛው ሰው ደግሞ አዋቂ መሆናቸውንና እርሳቸው ከሌሉ ሀገራቸውም ሆነ የሀገራቸው ህዝብ ከዕውቀት መጓደል ምክንያት መኖር እንደማይችል በማስረዳት ከአደጋው ለመዳን ዘለው ይወርዳሉ።

 

በስተመጨረሻ የቀሩት አንድ ቄስና አንዲት ህጻን ልጅ ነበሩ። እናም ቄሱ፣ “በይ እንግዲህ ልጄ በቀረው አንድ “ፓራሹት” አንቺ ውረጂ። እኔ  መስዋት እሆናለሁ፤ ይህ አምላክ የሚወደው ተግባር ነውና” ይሏታል። ህጻኗም ፈጠን ብላ፤ “ለምን መስዋት ይሆናሉ? ሁለት የነፍስ አድን ጃኬቶች አሉን እኮ” ስትል ታስገርማቸዋለች። ቄሱም ቅድም ሲቆጠር አራት ብቻ የነበረ መሆኑን አስታውሰው አንዱ ከየት መጣ? ሲሉ ይጠይቃሉ። በዚህ ጊዜ ልጅቱ ፈገግ ብላ፤ “በአፍሪካ ምድር አዋቂና መሪ ነኝ ያሉት ሰውዬ ይዘውት የወረዱት ፓራሹት ሳይሆን የኔን የትምህርት ቤት ቦርሳ ነው” አለቻቸው ቂ-ቂ-ቂ ይህቺ ናት ጨዋታ ማለት ይሄኔ  ነው። አንድዬ ብቻ አውራ ሰው ጠፍቶ ከሚነግስና አዋቂ ጠፍቶ አውቃለሁ ከሚል አላዋቂ ይሰውረን አቦ . . . ደህና ሲታጣ ከሚመለመል አላዋቂ፣ ስግብግብና ውራ ሰውም አንድዬ ይጠብቀን። ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
547 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1024 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us