ያልበላንን ማከክ. . .

Wednesday, 20 July 2016 13:51

 

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . .  ክረምት በየፈርጁ እንዴት ይዟችኋል?. . . “የባሰ አለ ሀገርህን አትልቀቅ” ማለት መቼም ዘንድሮ ነው። ይልቅዬ ከሰሞኑ አከራረማችን ጋር የሰመረችውን የአበው ጥቅስ እዚህች'ጋ ብንጠቅስ ምን ይለናል? ምንም።

 

ያልበላኝን ቦታ ስፎክተው ኖሬ፣

የበላኝ ሲመጣ አለቀብኝ ጥፍሬ።

 

አንዳንድ ነገራችን ያልበላንን የሚያሳክከን ነው። አንዳንድ ነገራችን ቅቤ አንጣሪዋ እያለች፤ ጎመን ቀንጣሿን ምች መታኝ አለች የሚያሰኝ ነው። አንዳንድ ነገራችን ደግሞ የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣን የሚያስተርትልን ነው። ያልበላን ቦታ ስለማክክ ስጽፍ አንዲት ከዚህ ቀደም የነገርኳችሁ የሙላህ ነስረዲን ዋዘኛ ጨዋታ ትዝ አለችኝ።

 

ሙላህ ነስረዲን አመሻሽ ላይ ቤቱ ውስጥ ሳለ ድንገት የጣት ቀለበቱ ይጠፋበታል። ቀለበቱ በመጥፋቱ ምክንያት ሀገር ይያዝልኝ ሲል ፍለጋውን ማጧጧፍ ጀመረ። ድንገት ግን ከቤቱ ፊት ለፊት ከሚገኘው አውራ መንገድ ዳር የጠፋበትን ቀለበት በትኩረት ሲፈልግ ታየ። አንድ የመንደሩ ሰው የሙላህ ነስረዲንን አንዳች ነገር ፍለጋ ተመልክቶ ጠጋ አለውና፣ “ወዳጄ ነስሩዲን ምን ጠፍቶህ ነው እንዲህ በተመስጦ በመፈለግ ላይ ያለኸው?” ሲል ይጠይቀዋል። ሙላህ ነስረዲንም በመንገዱ የመብራት ቋሚ እንጨት ስር ፍለጋውን ሳያቋርጥ፣ “እባህክ ለብዙ አመታት ከጣቴ ወልቆ የማያውቀው የወርቅ ቀለበቴ በመጥፋቱ ፍለጋ ላይ ነኝ” ይለዋል፣ ይሄን ጊዜ የመንደሩ ሰውዬ የጠፋው ነገር ቀለበት መሆኑን በማወቁ ደንገጥ ብሎ ፍለጋውን ይቀላቀላል።

 

ብዙ የመንደሩ ሰዎች ተቀላቅለው ጠፋ የተባለውን የጣት ቀለበት በመንገድ መብራት አካባቢ ፍለጋቸውን ቀጠሉ። ቀስ በቀስ ግን የመንደሩ ሰው ተስፋ ቆርጦ ወደቤቱ በመግባቱ የፈላጊው ቁጥር እየቀነሰ መጣ። ፍለጋው ውጤት አልባ መሆኑን የተረዳው የመጀመሪያው ሰውዬ ወደነስረዲን ጠጋ ብሎ፣ “ለመሆኑ እርግጠኛ ነህ ቀለበትህ የጠፋው እዚህ አካባቢ ነው?” ሲል የማጣሪያ ጥያቄ አቀረበለት። በዚህ ጊዜ ሙላህ ነስረዲን ምን ቢመልስለት ጥሩ ነው? “ነገሩማ ቀለበቴ የጠፋብኝ ቤቴ ውስጥ ነው” አለው። ሰውዬውም በነገሩ በመገርም “ታዲያ ቤትህ ውስጥ የጠፋብህን ቀለበት እንዴት ነው ከመንገድ ዳር የምትፈልገው?” ሲል ይጠይቀዋል፤ ሙላህ ነስረዲንም ሲመልስ፣ “ወዳጄ ቤቴ ውስጥ ምንም አይነት መብራት ባለመኖሩ ምክንያት ዝም ብዬ ከመቀመጥ በመንገዱ መብራት ብፈልገው ብዬ ነው። ቤቴ ውስጥ የጠፋብኝን ቀለበት እዚህ መብራት ስር የምፈልገው” ብሎላችሁ እርፍ። ቂ-ቂ-ቂ! ይህም አይደል ያልበላህን ማከክ ማለት? . . . ወይም ደግሞ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ልትሉትም ትችላላችሁ።

 

በማያገባው የሚገባ ሰው፣ በማያሳስብ ነገር  የሚብሰለሰል ሰው፣ በማያስቅ ነገር የሚስቅ ሰው፣ በማያስለቅሰው ነገር የሚያለቅስ ሰው፣ በማያስነጥስ ነገር የሚያስነጥሰው ሰው አልበዛባችሁም?. . . ከቤቱ  ይልቅ በጎረቤቱ  ጉዳይ አያገባው ገብቶ የሚፈተፍት ሰው ሲገጥማችሁ ምን ይባላል። የራሱ ሀገር ስፖርት፣ የራሱ ሀገር ሩጫ፣ የራሱ ሀገር እግርኳስ እንክት፣ ስብርብር እያለበት በጃማይካ ሯጮች መጎዳትና በሮናልዶ ስብራት እንቅልፉን የሚያጣ ሰው ሲገጥማችሁ ነገሩ እንዴት ነው ማለታችሁ አይቀርም።

 

አንድን ጉዳይ ከባለቤቱ በላይ ላያስጮህ የሚፈልግ ሰው ስታዩ፣ ከባለቤቱ በላይ ሲሟገት ስታዩ፣ ከባለቤቱ በላይ ሲሟሟት ስታዩ፣ ይሄሰው እንዴት ነው “የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ” ይሉትን ተረት አስታውሰኝሳ ልትሉ ትችላላችሁ። የሚያስጮህ የራስ ጉዳይ ላይ አፉን ለጉሞ በሰው ነገር ላይ አፉንም ጉልበቱንም ሊያሳየን የሚሞክር ሰው በጣም ያሳዝነኛል።. . . የራሱን ጉዳይ ትቶ የሌሎችን አማስሎና ፈትፍቶ እንደሚኖር ሰው ማንም አያሳዝንም። እዚህች'ጋ ከናይጄሪያዊው ቀልድ አዋቂ ማስታወሻ ላይ ያገኘዋትን ጨዋታ እንካችሁ።

 

በአንድ ወቅት ሁለት ሚስቶቻቸው የጠፉባቸው ጉልማሶች እየተዘዋወሩ ሚስቶቻቸውን በመፈለግ ላይ ሳሉ ድንገት ሳይታሰብ በመንገድ ትከሻ ለትከሻ ይጋጫሉ። በመጋጨታቸው አንደኛው ሌላኛውን ይቅርታ ይጠይቃል፣ “ይቅርታ ወንድሜ ሚስቴ ጠፍታብኝ እርሷን ፍለጋ ተቻኩዬ ነው ሳላውቅ የገፋውህ” ይለዋል። ሁለተኛውም ከአፉ ቀምቶ፣ “ምን አይነት የሚገርም አጋጣሚ ነው። እኔም እኮ ሚስቴ ጠፍታብኝ እየፈለኳት ነው” በማለት ይነግረዋል። በዚህም አብረው ለመፈለግ ይስማሙና ፍለጋቸውን ከመጀመራቸው በፊት አንደኛው “ሚስትህ ምን አይነት ነች?” ሲል ሌላኛውን ይጠይቃል። በዚህ ጊዜ ተጠያቂው፣ “ቆንጆ፣ ጥቁር ፀጉር ያላትና ረጅም፤ እግሮቿ የሚያምሩና ከኋላዋ በጣም የሚያምር ቅርፅ ያላት ናት። ያንተስ ምን ትመስላለች ምናልባት ቀድሜ ካየኋት እንድነግርህ ይረዳኛል” ሲል መልሶ ይጠይቀዋል። የመጀመሪያው ጠያቂ ፈጠን ብሎ “ተወው ወንድሜ አትልፋ ያንተን ብቻ እንፈልጋት” ብሎት እርፍ ቂ-ቂ-ቂ! ይሄ ነው እንግዲህ ያልበላንን ማከክ ማለት። . . . የራስን ሚስት ከመፈለግ የሰውን ሚስት ወደማፈላለግ በፍጥነት ዘው የሚባልበት ጊዜ መጥቷል።

 

አንዳንዶችም ከሰሞኑ ስንት የሚታይና የሚወራ ነገር እዚሁ እኛ ዘንድ እያለ ደርሶ “ልዑላዊነት” አቀንቃኝ ሲሆኑ ታይተዋል። እዚህ ስንት ጉዳይ እያለ የቱርክ መፈንቅለ መንግስትና የኤርዱጋን ነገር፤ የኢትዮጵያን ድርቅ ረስቶ የካሊፎርኒያን በረሃማነትና ንዳድ፤ የአዳማን የጎርፍ አደጋ ትቶ የቻይናን በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የኛን ክልላዊነት የራሱ መስሎ የእንግሊዝን ከአውሮፓ ህብረት መነጠል እያጋነኑ ማውራት እንደኔ - እንደኔ ያልበላንን እንደማከክ ይቆጠራል።

 

ለማንኛውም በስራውም፣ በትምህርቱም፣ በፖለቲካውም ሆነ በማህበራዊ ኑሮው ያልበላንን አካኪ ከመሆን፣ ከምጣዱ በላይ ያለን የእንቅብ ከመሆን፣ ቅቤ ስናነጥር በጎመን ምች የሚመታን ከመሆን አንድዬ ይጠብቀን አቦ፤ ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
539 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1065 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us