ግፍን እንደአማራጭ እና እንደአቋራጭ

Wednesday, 27 July 2016 13:42

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?..... እኔ የምለው ማንም እየተነሳ እርሱ በማይበላውና ትርፍ በሚያግበሰብስበት፤ በእኛ እንጀራ ላይ ሚጥሚጣ ሲነሰንስበት ስንቃጠል፤ በርበሬ ከሸክላ ጋር በመቀየጡ ስንቃጠል፣ ርጋፊ ሲደባልቅበት ስንማረር ሰንብተን ይኸውና ደግሞ ዘንድሮ ጀሶን እንደ በሶ፣ ሰጋቱራን እንደ እንጀራ የሚያበላን መጣ አይደል?

 

ኧረ ተው ጐበዝ እንተዛዘን?! እንደው ቢቀሸብ ቢቀሸብ እንጀራ ላይ ይቀሸባል? የምሬን እኮ ነው። ፍግ እየጋገሩ ማብላት ግፍ ነው። በርበሬ ውስጥ ቀይ የሸክላ አፈር ገባ ሲባል ጉድ እንዳላልን፤ በቅቤ ውስጥ ሙዝ ተገኘ ስንባል ወይ ጉድ እንዳላልን ይኸውና ደግሞ እንጀራችን ውስጥ ሰጋቱራና ጀሶ የሚደባልቅ መጣ።…. ይሄን የመደባለቅ ነገር አንስተን ከአንድ አዋቂ ወዳጄ ጋር እያወጋን ነበር። ታዲያ የእንጀራውም፣ የቅቤውም ሆነ የበርበሬው ከሌላ ባዕድ ነገር ጋር መደባለቅን አስመልክቶ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? “ይህ የዘመናችን የኢኮኖሚ ውጤት ነው። ከሁሉም ከሁሉም ደግሞ (Mixed Economy) ወይም “ቅይጥ ኢኮኖሚ” የሚለውን ፅንሰ ሀሳብ በተሳሳተ መንገድ የተረዱ ራስ ወዳድ ሰዎች ናቸው እንዲህ የሚያደርጉት” ብሎ ፈገግ አሰኝቶኛል። (እንዲህ ናትና በ“ቅይጥ ኢኮኖሚ” ስም ማጭበርበር፤ ይህቺ ናት ጨዋታ አትሉልኝም።)

 

እናላችሁ ከታች እስከላይ በማኅበራዊውም፣ በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካዊ ንዝረታችን ውስጥ አብሮን የማይሄድ ነገር እየደባለቅን ነገራችን ሁሉ “ቅይጥ ኢኮኖሚ” አይነት መሳለቂያ ፈጥሯል። ወገንን ማታለል ራስን ማታለል ነው። ወገንን ማማረር እየቆየም ቢሆን ራስን ማማረር ነው። ወገንን ማጭበርበር ራስን እንደማጭበርበር ነው። ምክንያቱም ቀኑ ሲደርስ በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርምና… ጐበዝ አማራጭ ነው እያሉ በሌላው ጉሮሮ ላይ አቋራጭ መንገድን መስራት በሰማይም በምድርም የሚያስጠይቅ ግፍ ነው።  

 

በየመስኩ፣ በየተቋሙ፣ በየፓርቲውም ሆነ በእምነት ተቋማቱ ጭምር “ያለ እኔ” ባዩና “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ባዩ በእጅጉ በርክቷል። እናም ለሌላው ማሰብ ለራስ እንደማሰብ መሆኑ ተዘንግቷል። ለሌላው ደግ መሆን ለራስ ደግ መዋል መሆኑን ረስተነዋል። (ለድሃ የሰጠ ለእግዜር አበደረ እንዲሉ አበው)፤ ለሌላው ይቅርታ ማድረግ ለራስ ሰላም መስጠት መሆኑን የሚያስተውል ጠፍቷል። ለህዝብ በጐ መስራት መንግስትን እንደሚያፀና ማወቅ ተስኖናል።

 

እናላችሁ የራሱን ገቢ ለማሳደግ፤ የራሱን ቢዝነስ ለማስመንጠቅ፣ የራሱን እንጀራ ለመጋገር ሲል በሰው ኪሳራ፣ በሰው ጤንነትና በሰው ህይወት ላይ ቁማር የሚጫወት ሰው የበረከተበት ዘመን ላይ ተከስተናል። የሰውን ሀቅ ለመንጠቅ ሲል የራሱን ጊዜ የሚሰርቅም ሰው እንዲሁ በዝቷል። እናም ግፍን እንደአማራጭና እንደአቋራጭ መጠቀም “ፌር” አይደለም።

መምህሩ በክፍል ተገኝተው ለተማሪዎቻቸው ከብዙ ማብራሪያ በኋላ የክፍል ስራ ይሰጣሉ። ይሄን ጊዜ አንድ አርፋጅ ተማሪ እየተጐተተ ይገባል። መምህሩ አንዴ የእጅ ሰዓታቸውን ሌላ ጊዜ አርፍዶ የገባውን ተማሪ እያስተዋሉ፤ “ለመሆኑ ምን ስትሰራ ነው እስካሁን ያረፈድከው?” ሲሉ ይጠይቁታል። “አንድ ሰውዬ መቶ ብር ጠፍቶበት ነው” ሲል ይመልሳል። “ታዲያ አንተ ብሩን ስታፋልገው ነው የቆየኸው? እሺ የጠፋውስ ብር ተገኘ?” ብለው በድጋሚ ሲጠይቁት ተማሪው ምን ቢመልስላቸው ጥሩ ነው? “አይ ቲቸር ብሩ አልተገኘም፤ ምክንያቱም ብሩ ላይ በእግሬ ቆሜበት ስለነበር” ብሎላችሁ እርፍ ቂ… ቂ… ቂ…! ይሄኔ ታዲያ መምህሩ ምርር ብሏቸውና በልጁ ነገር አዝነው ከክፍል ካስወጡት በኋላ ለተማሪዎቻቸው፣ “ይህ የክፍል ስራ ከ100% ውጤት የሚያዝበት ስለሆነ በደንብ ስሩት” ብለው አረፉት። ለ100 ብር ብሎ 100% ውጤት ማጣትም እንዳለ ለማስታወስ ያህል ነው ቂ… ቂ… ቂ….!

 

ከሌላው ሰርቀን ለራሳችን እያተረፍን ከመሰለን በእጅጉ ተሳስተናል። ይህን ያህል ስለምን እንደተጨካከንን፣ ድንበር እንዳጠርን፣ ዘር እንደቆጠርን፣ ወገን እንደለየን፣ በር እንደቀረቀርን ሳስበው … ሳስበው ከክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል የቅኔ ውበት ጥቂት ስንኞች ትዝ ይሉኛል። እንደመሰናበቻ እነሆ፡-

 

ደጉንም ክፉንም ጨርሶ ያላየ፣

ከኢምንት ያልወጣ ካለም የተለየ፣

በያንዳንዱ ሀገር በያንዳንዱ ጐራ፣

በያንዳንዱ ንብረት በያንዳንዱ ስፍራ፣

እንደምን ያለግፍ፣ እንዴት ያለበደል፣

እንዴት ያለ ውርደት ሰው እንደሚቀበል፣

ስንቱን መጥፎ ነገር ቆሻሻ የገማ፣

በዓይኖቹ ያላየ በጆሮው ያልሰማ፣

የሰዎችን ሀዘን የሰዎችን ለቅሶ፣

ተካፋይ ያልሆነ በፍፁም ጨርሶ፣

የመፈጠር ዕጣ-ፅዋ ያልደረሰው፣

ምንኛ ታደለ ያልተወለደ ሰው!

 

ሰላማችንን በነውጥ ከሚቀይጡ፤ ፍቅራችንን በጥላቻ ከሚቀይጡ፤ መከባበራችንን በመናናቅ ከሚቀይጡ፤ አንድነታችንን በልዩነታችን ከሚቀይጡ፤ በርበሬያችንን በቀይ አፈር ከሚቀይጡ፤ ቅቤያችንን በሙዝ ከሚቀይጡ፤ እንጀራችንን በጀሶና በሰጋቱራ ከሚቀይጡ፤ እንዲሁም ግፍን እንደአማራጭና እንደአቋራጭ ተጠቅመው ከሚፈልጡና ከሚቆርጡ አላዋቂዎች አንድዬ ይጠብቀን። ቸር እንሰንብት!!!¾   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
469 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1139 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us