አፍሳሽና ቀማሽ. . .

Wednesday, 03 August 2016 14:29

 

እንደምን ሰነበታችሁ ወዳጆቼ!?. . . እኔ የምለው የናንተ የሆነን ነገር ለመቀማት ሲሉ ብቻ የሚጣደፉ ሰዎች ሲገጥሟችሁ ምን ትላላችሁ?. . . በስልጣም ከእልቅናውም፣ በትምህርቱም ሆነ በጉልበቱ ትንሽ ከእኛ በለጥ ያሉ ሰዎች ይጠቅመናል ላሉት ነገር ቀደም ቀደም ሲሉ ሳይ ምን ትዝ ይለኛል መሰላችሁ “የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል” ይሉት ተረት።

 

አደም. . .

አትበል ቀደም-ቀደም

ትሆናለህ ደም -በደም

 

እነሆ እዚህች'ጋ አንዲት አስተዛዛቢ ጨዋታ እንካችሁ፤ ሰውዬው አመሻሽ ላይ ከስራ ወደቤቱ ይመለሳል። ህጻን ልጇ በእጇ ዳቦ ይዛ ያስተውልና፣ “ጎሽ የኔ ልጅ ዳቦ እየበላሽልኝ ነው?” ይላታል። ህጻኗ ግን ፈጠን ብላ፣ “አይ አባባ ዳቦውን መብላት አልፈልግም” ስትል መለሰችለት። በዚህ ጊዜ የራበው አባት “እንግዲያውስ አንቺ ካልበላሽው እኔ እበላዋለሁ” ብሎ ተቀበላትና የርሃቡን ያህል ዳቦውን እየገመጠ፤ በልቶ ጨረሰው። ከረሃቡ ፋታ ያገኘው አባት፣ “ለመሆኑ ዳቦውን ያልበላሽው ጠግበሽ ነው እንዴ የኔ ልጅ?” ሲል ጠየቃት፡፤ ይሄኔ ልጅቱ ምን ብትመልስላት ጥሩ ነው? “አይ አባባ እኔ ዳቦውን መብላት አምሮኝ ነበር ግን ልበላው ያልቻልኩበት ምክንያት ውሻችን ከእጄ ቀምቶ ቆሻሻ ላይ ስለጣለብኝ ነው” ስትለው የበላው ዳቦ ልውጣ ልውጣ እያለ ተናነቀው።

 

“የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል” ማለት እንግዲህ እንዲህ ነው። ሰው ሁሉ እኛን የጎዳ እየመሰለው፤ ራሱን የጠቀመ እየመሰለው አንዳንዴ የሚፈጽመው ተግባር አስተዛዛቢ ነው። አንድ ነገር ሲሆን፤ ለምን ሆነ፣ እንዴት ሆነ ብሎ ችግራችንን አጣርቶ መፍትሄ እንደመስጠት ከመጠየቅ ይልቅ መንጠቅ የሚያበዛ ከሆነ ዋጋውን ማግኘቱ አይቀርም።

 

በተለይ “የአንዳንድ” የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ነገር ዘንድሮ አልተቻለም።. . . ይህው እንኳን ከሰሞኑ መንግስት የደሞዝ ግብር ማሻሻያ አደረገ ምናምን ሲባል ጊዜ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ምን ቢሉ ጥሩ ነው? “መንግስት እግዜር ይስጠው ኑሯችንን ከስሩ ለወጠው፤ ኪሳችንን በብር ወጠረው፤ ተመስገን ነው መቼም የቤተሰባችንን ችግር የሚቀርፍ መፍትሄ ነው ወዘተ” አሉ -አሉ፣ ቂ-ቂ-ቂ እኛ የሰጠነውን መልስ የሰጠን መንግስት እንዴት ነው እግዜር ይስጠው ማለት?. . . አሁን እስቲ ማን ይሙት የሁለትና የሶስት መቶ ብር ግብር ቅነሳ ይሄን ያህል “ኑሮዬን ከስሩ ለወጠው” የሚያስብል ነው?. . . (ግድ የላችሁም ግን እነዚህ “አንዳንድ” የሚባሉት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በደንብ ይጣሩልን። ልክ ነዋ! እንደውም አንዳንዴ ሳስበው እየተከፈላቸው ነው እንዴ ቃለ-ምልልስ (ኢንተርቪው) የሚያደርጉት ሁሉ ብዬ እጠራጠራለሁ)

ለማንኛውም የደሞዝ ግብር እንደቀነሰ ሁሉ ብዙ እንዲቀነስልን የምንፈልጋቸው ነገሮች እንዳሉ ይስመርልን። ለምሳሌ ውሸት ይቀነስልን፣ የማይፈፀሙ ቃሎች ይቀነሱልን፣ የማይፈፀሙ እቅዶች ይቀነሱልን፤ የማይወረዱ ወንበሮች ይቀነሱልን፤ ለኛ ያዘኑ መስለው ዳቧችንን የሚበሉልን ስራ አስፈፃሚዎች ይቀነሱልን፤ ትምህርት ቤት ብቻ በሚል ስም የተከፈቱ በዋጋቸው እሪሪ የሚያስብሉ ት/ቤቶች ይቀነሱልን፤ በህክምና ተቋም ስም በየቦታው የተከፈቱ ፈውስ አልባ ክሊኒኮች ይቀነሱልን። አለበለዚያ እነሱ ያለበቂ ምክንያት ሃብት እየፈሰሱ፤ እኛን ደግሞ ምሬት እየሳፈሱ መቀጠል የለባቸውም። ጎበዝ ዘንድሮ እኮ ለእነእገሌ በግፍ ሲያፈሱ እኛን ደግሞ አፈር ሲያሳፍሱ ደስ አይልም።

 

እናላችሁ ዘንድሮ ለኛ ያዘኑ መስሎ የኛን ዳቦ ተቀብሎ የሚያነክተው በዝቷል። ዳሩ ግን ሁሏም በስተመጨረሻ ዋጋዋን ማግኘቷ አይቀርም።. . . ሰውዬው ወደአንድ መጠጥ ቤት ገብቶ የሚጠጣ ነገር ያዛል። ያዘዘው ነገር መጥቶለት ፊቱ እንደተቀመጠ ለብዙ ሰዓታት አፍጦ እያየው በሃሳብ ነጎደ። ይሄኔ በአካባቢው “ማን አለኝ ከልካይ -ያሻኝን ባዶ” የሚል ተደባዳቢ ጉልበተኛ ሰው ወደመጠጥ ቤቱ ይገባል። እናም ወደመጠጥ ቤቱ እንደገባ ባዘዘው መጠጥ ላይ ወደፈዘዘው ሰውዬ በመጠጋት መጠጡን ጭልጥ አድርጎ ይጠጣበታል።

 

“አንተም እንደሌሎቹ ቀኔን አበላሸህብኝ ማለት ነው?”ሲል በቁጭት ይጠይቀዋል። ጉልበተኛው ሰውዬውም፣ “የምን መነጫነጭ ነው። ከፈለክ ከአንድ በላይ መጠጥ ልጋብዝህ እችላለሁ። እኔ ያዘዝኩት እስኪመጣ ስለጠማኝ ነው ያንተን የጠጣሁት” አለው።

 

መጠጡ የተጨለጠበት ሰውዬም፣ “እኔ የምነጫነጨው ለመጠጡ ብዬ አይደለም። ዛሬ ለኔ የመጨረሻ መጥፎ ቀን ነው። ጠዋት ላይ አርፍጄ ከእንቅልፌ ነቃሁ። አለቃዬ እንዳይቆጣኝ ብዬ መኪናዬን አስነስቼ ስቸኩል፤ መንገድ ላይ መኪናዬ ተበላሸች። እንደምንም ብዬ ቢሮዬ ደረስኩ ግን አርፍጄ ነበር። እንደገባው ፀሐፊዬ አንድ ደብዳቤ ሰጠችኝ። ደብዳቤው ልክ እንዳነበብኩት ከቢሮ መሰናበቴን የሚገልፅ ነበር። ቀኔን እያማረርኩ ታክሲ ይዤ ወደቤቴ ስመለስ ሚስቴን ከሌላ ሰው ጋር ተኝታ አገኘኋት። በዚህ ጊዜ ተስፋ ቆርጬ መርዝ ገዝቼ ወደዚህ መጠጥ ቤት መጣሁ። መርዙን የምጠጣበት ብርጭቆ ውስጥ ጨምሬ ትንሽ እያሰብኩ እያለ ነው አንተ ብድግ አድርገህ የጨለጥከው” ብሎላችሁ እርፍ። ቂ-ቂ-ቂ ይህቺ ናት እንግዲህ ጨዋታ!

 

ጎበዝ የበለጥን እየመሰለን፣ የቀማን እየመሰለን፣ ታዛቢ የሌለ እየመሰለን፣ የሚቀጣን የሌለ እየመሰለን ለራሳችን ብቻ ስንጣደፍ የሌሎችን ክፉ ዕጣ ለምንወስድ ሰዎች ይህቺ ወግ ጥሩ ማስተማሪያ ትመስለኛለች። አንዳንዶች በግፍ ያፈሰሱትን፤ እኛ በስስት የምንቀምስ ሰዎች ነን እና ብንተዛዘን ምን ይለናል? . . . ቸር እንሰንብት!!!

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
459 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1082 guests and no members online

Archive

« September 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
          1 2
3 4 5 6 7 8 9
10 11 12 13 14 15 16
17 18 19 20 21 22 23
24 25 26 27 28 29 30

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us